ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት፣  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በመንፈስ መቀዝቀዝ ወደ ሞት የሚመራ መሆኑን አስታወቁ።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 15 ቀን 2012 ዓ. ም. በቫቲካን፣ ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ፣ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ካህናት፣ ደናግል እና ምዕመናን ባሰሙት ስብከተ ወንጌል፣ በመንፈስ መቀዝቀዝ ወደ ሞት ያመራል ብለው ጎደሎ ክርስቲያን ሆነን እንዳንቀር እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልን በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ፍሬን የማይሰጥ የውሸት ውስጣዊ ሰላም ሊኖረን አይገባም ካሉ በኋላ ራሳችንን ዛሬ እንድንለውጥ ከእግዚአብሔር የሚቀርብልንን ጥያቄ ወደ ነገ ማሸጋገር አያስፈልግም ማለታቸውን የቫቲካን ዜና ክፍል ባልደረባ አድሪያና ማሶቲ የላከችልን ዘገባ አመልክቷል። 

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ባሳረጉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ያቀረቡትን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተንትኖ፣ በዕለቱ በተነበበው የመጀመሪያ ንባብ ከሆነው ከትንቢተ ሐጌ 1:1-8 መሆኑ ታውቋል። በዚህ የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔር በነብዩ ሐጌ በኩል ሕዝቡ ባህሪውን እንዲያሰላስል እና የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ እንደገና ለመገንባት የሚያስችል መለወጥ እንዲያደርግ ማሰሰቡን ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

በራሱ የማይተማመን እና ችግርን የማይጋፈጥ ሕዝብ፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዳብራሩት እግዚአብሔር ነቢዩ ሐጌን ተሸንፈው የቀሩትን የሰነፍ ሰዎች ልብ ለመቀስቀስ እንደጠራው እና በጠላት የወደመውን ቤተመቅደስ መልሰው እንዲገነቡ ማነሳሳቱን ገልጸዋል። የእግዚአብሔርም ቃል በነቢዩ በሐጌ በኩል እንዲህ ሲል መጣ፤ “ይህ ቤት ፈርሶ ሳለ፣ እናንተ ራሳችሁ በተዋቡ ቤቶቻችሁ ውስጥ ለመኖር ጊዜው ነውን?” ስለዚህ እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “እስቲ መንገዳችሁን ልብ በሉ፤ 6ብዙ ዘራችሁ፤ ነገር ግን ያጨዳችሁት ጥቂት ነው፤ በላችሁ ግን አልጠገባችሁም፤ ጠጣችሁ ግን አልረካችሁም፤ ለበሳችሁ ግን አልሞቃችሁም፤ ደመወዝን ተቀበላችሁ፤ ግን በቀዳዳ ኰረጆ የማስቀመጥ ያህል ነው።” እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ “እስቲ መንገዳችሁን ልብ በሉ፤ ወደ ተራራ ውጡ፤ እንጨት አምጡ፤ ቤቱን ሥሩ፤ እኔም በእርሱ ደስ ይለኛል፤ እከብርበታለሁም” ይላል እግዚአብሔር (ሐጌ 1:3-8) ።

የፈረሰውን የእግዚብሔር ቤተመቅደስ መልሶ ለመገንባት፣ የተጠየቀውን ሥራ በጊዜው ለማከናወን ተነሳሽነትን በማጣት ቀጠሮን ወደ ፊት እያራዘመ የቆየውን ሕዝብ ስንፍናን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው ይህን የሚመስል ስንፍና፣ በመንፈስ መቀዝቀዝ፣ የሕይወት መዳከም በመካከላችንም ይታያል ብለው ዛሬ ማከናወን ያለብንን ተግባር ለነገ ወይም ለተነገ ወዲያ በማሸጋገር እንዘልቃለን ብለው ሕይወትን የሚቀይር የልብ መለወጥ ዛሬ እንጂ ለነገ ማደር የለበትም ብለዋል።

የመንፈስ መቀዝቀዝ ወደ ሞት ይመራል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብከታቸው እንዳስረዱት በክርስቲያናዊ ሕይወት ውስጥ ብዙ አገልግሎቶችን፣ በዕለታዊ ማሕበራዊ ሕይወትም ብዙ ሥራን ማከናወን የሚያስችል ትልቅ ሃይል በሰዎች ውስጥ ታምቆ እንደሚቀር ገልጸው በዚህም የተነሳ ብዙ ሰዎች በእድሜአቸው ምንም ሳያከናውኑ በከንቱ የሚያባክኑ መሆኑናቸውን ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም ለዚህ ዓይነት የመንፈስ ቅዝቃዜ ፈጣን ምላሽ ሳንሰጥ በቀጠሮ ብቻ የምናሳልፍ ከሆነ ሕይወታችንን በከንቱ እናጥፋለን ብለውል።  

የመለወጥ ቀን ዛሬ ነው፣

ስንፍና በሁላችን ላይ ሊታይብን ይችላል ያሉት ቅዱስነታቸው እግዚአብሔር ሕወታችን ተለውጦ ማየት የሚፈልገው ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤት ያቀረቡትን የቅዱሳት መጽሐፍት አስተንትኖን ባጠቃለሉበት ወቅት በስንፍና እንዳንወድቅ፣ የክርስትናን ሕይወት በሙላት እንድንኖር ከእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋውን ተማጽነው፣ ስንፍናን የምንዋጋበትን የመንፈስ ቅዱስ ሃይል ለምነዋል።

ይህን ዘገባ በድምጽ ለማዳመጥ ከዚህ ቀጥሎ የሚገኘውን “ተጫወት” የሚለውን ምልክት ይጫኑ!
26 September 2019, 16:52
ሁሉንም ያንብቡ >