ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት  (ANSA)

ር.ሊ.ጳ ፍራንቸስኮስ “እግዚኣብሔር ያደረገልንን ነገሮች ሁሉ ማስታወስ ይኖርብናል”።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 28/2011 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅድስት ማርታ የጸሎት ቤት ቀሳውስት፣ ደናግላን እና ምዕመናን በተገኙበት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት እንደ ገለጹት “እግዚኣብሔር በደህንነት ታሪክ ውስጥ ያደረገልንን ነገሮች ማስታወስ ተገቢ” እንደ ሆነ ገልጸው “ልባችን ከጌታ መንገድ ወጣ ባለ መልኩ አቅጣጫ እንዲቀይር የምናደርግ ከሆንን ልባችን የአቅጣጫ መጠቆሚያ የሌለው በመሆኑ የተነሳ ወደ ያልተፈለገ ሥፍራ ሊወስደን ይችላል” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በእለቱ ያደረጉት ስብከት በወቅቱ ከኦሪት ዘዳግም (30፡15-20) ላይ ተወስዶ በተነበበው የመጀመሪያው ምንባብ ውስጥ በተጠቀሱት እና የእስራኤል ሕዝቦች ቃል ወደ ተገባላቸው ምድር በሚያደርጉት ጉዞ ላይ የሚገጥማቸውን ሦስት ቅልፍ የሆኑ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ እንደ ነበረ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን የእስራኤል ሕዝቦች ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመሄድ እንዲዘጋጁ እግዚኣብሔር ባዘዛቸው ወቅት ሙሴ በእስራኤል ሕዝቦች ፊት ከእግዚኣብሔር የተቀበለውን “ተመልከት፤ ዛሬ በፊትህ ሕይወትንና መልካምነትን፥ ሞትንና ክፋትን አኑሬአለሁ፣ በሕይወትም እንድትኖር እንድትባዛም፥ አምላክህም እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር እንዲባርክህ፥ አምላክህን እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ ትእዛዙንና ሥርዓቱን ፍርዱንም ትጠብቅ ዘንድ ዛሬ እኔ አዝዝሃለሁ” የሚለውን ተግዳሮት በእስራኤል ሕዝብ ፊት ማስቀመጡን የተመለከተ ስብከት እንደ ነበረ ከደረሰን መረጃ ለመረዳት ተችሉዋል።

“ነጻነታችንን እንጎናጸፍ ዘንድ የቀረበልን ጥሪ ነው” በማለት ስብከታቸው የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ሙሴ ተጠቅሟቸው የነበረውን ሦስት ቁልፍ የሆኑ አገላለጾች በድጋሚ በመጠቀም “ልብህ ቢስት፣ አንተም ባትሰማ፥ ብትታለልና ለሌሎችም አማልክት ብትሰግድ ብታመልካቸውም” የሚሉት ሦስት ቁልፍ የሆኑ አገላለጾችን ቅዱስነታቸው መጠቀማቸውን ለመረዳት ተችሉዋል። ይህንን በተመለከተ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል . .

ልብህ ከሳተ፣ ትክከለኛ ያለሆነ መንገድ የምትከተል ከሆነ- በተሳሳተ መንገድ ወይም በሌላ ዓይነት መንገድ ላይ የምትጓዝ ከሆነ እና በተክከለኛው መንገድ ላይ የማትጓዝ ከሆነ፣ አቅጣጫህን ትስታለህ፣ በትክክለኛው መንገድ ላይ ተመልሰህ መጓዝ እንድትችል ደግሞ የአቅጣጫ መጠቆሚያ መሳሪያ ያስፈልግሃል። የአቅጣጫ መጠቆሚያ የሌለው ልብ ለማኅበረሰቡ፣ ለግለሰቡ ራሱ እና ለሌሎችም ሳይቀር በጣም አደገኛ የሆነ ልብ ነው። አንድ ልብ ይህንን የመሰለ የተሳሳተ ጎዳና መከተል የሚጀምረው ማዳመጥ ሲያቆም፣ ራሱ በፈለገው ጎዳና ላይ መሄድ ሲፈልግ እና ራሱን ለጣዖታት ተገዢ ሲያደርግ ነው።

“ይሁን እንጂ ብዙን ጊዜ የማዳመጥ ችሎታ ይጎለናል” በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ብዙ ሰዎች ደንቆሮ የሆነ ነፍስ አላቸው እኛም  ራሳችን “ብዙን ጊዜ ነፍሳችን ደንቆሮ እንድትሆን እናደርጋታለን፣ ጌታን እንዳትሰማ እንከለክላታለን” ብለዋል። ብልጭልጭ በሆነ ሁኔታ እኛን ወደ ጣዖት አምልኮ  የሚጋብዙንን "ሐሰተኛ አማልክት" ማስወገድ እንደ ሚገባ በመግለጸ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እኛ ክርስቶስን ለመገናኘት እንችል ዘንድ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመሄድ በምናደርገው ጉዞ ላይ የሚያጋጥመን አንደኛው እና ዋነኛው ተግዳሮት ይህ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው ይህ አሁን የያዝነው የዐብይ ጾም ወቅት “በትክክለኛው ጎዳና ላይ መራመዳችንን እንቀጥል ዘንድ ይረዳናል” ብለዋል።

“ጌታን አለማዳመጥ” የሚለው አገላለጽ ደግሞ ሁለተኛው ቁልፍ የሆነ ሐሳብ መሆኑን በመግለጽ ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው እግዚኣብሔር የሚለንን ነገር የማናዳምጥ ከሆንን ቃል የተገባልንን የተስፋይቱን ምድር መውረስ አስቸጋሪ እንደ ሚሆን ገልጸው የማናዳምጥ ከሆንን ደግሞ ማሕደረ ትውስታችን ቀስ በቀስ እየቀነሰ እንደ ሚሄድ ቅዱስነታቸው ጨምረው ገልጸዋል። “እግዚኣብሔር ለሕይወታችን፣ ለቤተ ክርስቲያናችን፣ ለሕዝባችን ያደረገልንን ነገሮች ሁሉ የምንረሳ ከሆንን” እኛ ብቻችንን መጓዝ እንለማመዳለን፣ በራሳችን ኃይል እና ጉልበት መጓዝ እንጀምራለን፣ ራሴን እችላለው” በሚል ስሜት ውስጥ ሆነን መኖር እንጀምራለን ብለዋል።

በዚህ ምክንያት በዚህ አሁን በጀመርነው የዐብይ ጾም ወቅት “የማሕደረ ትውስታ ጸጋ” እንዲሰጠን የምንጠይቀበት ወቅት ሊሆን የገባል በማለት ስብከታቸውን የቀጠሉት ቅዱስነታቸው ሙሴ የእስራኤል ሕዝቦች እግዚኣብሔር ያደረገላቸውን ነገሮች ሁሉ እንዲያስታውሱ ሕዝቡን አደራ ያለበት በዚሁ ምክንያት እንደ ሆነ ጨምረው ገልጸው በሌላ በኩል ደግሞ እኛ ጤናማ ሆነን በምንኖርበት ወቅት፣ የእኛ መንፈስዊ ሕይወት የተስተካከለ በሚሆንበት ወቅት “ማሕደረ ትውስታችንን የመዘንጋት አደጋ ላይ የመውደቅ እድል ይገጥመናል” ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ስብከታቸውን በቀጠሉበት ወቅት ሦስተኛውን ቁልፍ የሆነ ጽንሰ ሐሳብ “ጣዖት ማምለክ የሚለው እንደ ሆነ” የገለጹ ሲሆን ጣዕት ማምለክ ማለት “ወደ አንድ የማምለኪያ ሥፍራ ሄደን አማልክቶችን ወይም ምስሎቻቸውን ማምለክ ብቻ ማለት እንዳልሆነ” ገልጸው ይህንን ሐሳባቸውን በሚገባ ለማብራራት በማሰብ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን ብለዋል . . .

ጣዖት ማምለክ ማለት አንድ ነገር ማድረግ ከፈለግን እና ያንን ማድረግ የፈለግነውን ነገር ደግሞ ከጌታ ይልቅ ለእኔ ምቾት የሚሰጠኝ ነገር ነው የሚል የልብ ባሕሪይ እና ዝንባሌ ነው፣ በአጭሩ ይህንን የምናደርግበት ምክንያት ጌታ ያደረገልንን ነገር ስለዘነጋን ነው። በዚህ በያዝነው የዐብይ ጾም ወቅት ሁላችንም ጌታ ማሕደረ ትውስታችንን መልሰን እንጎናጸፍ ዘንድ ጸጋውን እንዲሰጠን ልንጠይቀው የገባል፣ ጌታ በሕይወታችን ውስጥ ያደረገልንን ነገሮች ሁሉ መልስን ማሳታወስ እንችል ዘንድ እንዲረዳን ልንጠይቀው ይገባል፣ እንዴት እንደ ሚወደን ማስታወስ ያስፈልጋል። ከዚህ መልካም ከሆነ ማኅደረ ትውስታ በመነሳት ደግሞ ወደ ፊት መጓዝ ይኖርብናል።

07 March 2019, 16:07
ሁሉንም ያንብቡ >