ፈልግ

2018.10.02 Messa Santa Marta 2018.10.02 Messa Santa Marta  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “ጠባቂ መላዕክት ወደ እግዚአብሔር ቤት የምንገባባቸው ዕለታዊ በሮቻችን ናቸው”።

ጠባቂያችን መልአክ ግንኙነቱ ከእኛ ጋር ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔርም ጋር ይገናኛል። በእግዚአብሔርና በእኛ መካከል ድልድይ በመሆን ከጠዋት እስከ ማታ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እኛን ይጠብቀናል

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ማክሰኞ ጠዋት መስከረም 22 ቀን 2011 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ፣ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ካህናት ደናግልና ምዕመናን በዕለቱ የተነበበውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት መሠረት በማድረግ ስብከታቸውን  አቅርበዋል። በአውሮጳውያኑን ዘመን አቆጣጠር ዛሬ ጥቅምት 2 ቀን 2018 ዓ. ም. የጠባቂ መልአክት ክብረ በዓል ዕለት አንደሆነ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው በኦሪት ዘጸዓት በምዕ. 23 ቁጥር 20 ላይ “እነሆ በጉዞ ላይ ስሳለህ የሚጠብቅህንና ወዳዘጋጀሁልህ ሥፍራ የሚያስገባህን መልአክ በፊትህ ልኬልሃለሁ” በሚለውን ጥቅስ ላይ በማስተንተን፣ እግዚአብሔር ለሕዝቡ፣ ለፍጥረቱ በሙሉ ልዩ እርዳታንና ጥበቃን ለመላክ ቃል እንደገባልን አስታውሰዋል።    

ቅዱስ መልአክ የመንገዳችን መሪ ነው፣

ሕይወት በራሱ አንድ ጉዞ ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን የሕይወት ጉዞን በትክክት መጓዝ እንድንችል ድጋፍ የሚሰጡን፣ ከለላ የሚሆኑን፣ ትክክለኛ አቅጣጫን የሚጠቁሙን ሰዎች ወይም የንጹሐን መናፍስት እገዛ ሊኖረን ይገባል። አለበለዚያ ጉዞአችንን ሊያደናቅፉ በሚችሉ ሦስት ዓይነት አደጋዎች ልንመታ እንችላለን ብለዋል። ቅዱስነታቸው የመጀመሪያውን አደጋ ምን እንደሚመስል ሲገልጹ፣ ፈጽሞ ጉዞን ላለመጀመር መወሰን እንደሆነ ገልጸው፣ ብዙ ሰዎች ለጉዞ ወጥተው መንገድ ላይ ቆመው የቀሩት፣ በሕይወታቸው ምንም ላለማድረግ የወሰኑ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል። ይህ ትልቅ አደጋ እንደሆነ ገልጸው ይህን የሚያደርጉበት ዋናው ምክንያት ምን እንደሆነ ሲያስረዱ በቅዱስ ወንጌልም የተጠቀሰውና እውቀቱን ወይም ጥበቡን ላለመጠቀም ፈልጎ ደብቆ ያስቀመጠው ሰው፣ ምክንያቱም እውቀቱን የተጠቀመ እንደሆነ ስለሚሳሳት በፍርሃት ስለተጨነቀ። ይህን ሰው የመሰሉ በርካታ ሰዎች በሕይወታቸው ምንም እንቅስቃሴን የማያደርጉ መኖራቸውን አስታውሰዋል። በሕይወቱ ምንም እንቅስቃሴን የማያሳይ ሰው ሕይወቱን እንደሚያበላሽ ከሕይወት ልምድ እንገነዘባለን። ልክ እንደ ኩሬ ውሃ መሆን ማለት ነው፣ ሳይፈስ በአንድ ቦታ ብቻ ረግቶ የሚቆይ ውሃ እስከሚሸትና የትንኞችም መራቢያ ስፍራ እስከሚሆን ይደርሳል ብለው ቅዱስ መልአክ ጉዞአችንን ጀምረን እንዳንቆም ብርታትን ይሰጠናል ብለዋል።

ሁለተኛው አደጋ የተጀመረውን መንገድ መሳት ወይም ወደ ገደል መጓዝ፣

በሕይወት ጉዞ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሌሎች ሁለቱ አደጋዎች፣ አንደኛው የተጀመረውን መንገድ በመሳት ወደ ገደል ወይም ወደ ጥፋት የሚወስደውን አቅጣጫ መከተል ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዚህን ጉዞ አደገኛነት ሲገልጹ፣ ምንም እንኳን ወደ መጀመሪያው ገደማ ከተሳሳቱበት አቅጣጫ ተመልሰው ትክክለኛውን አቅጣጫ መያዙ ቀላል ሊሆን ይችል ይሆናል ብለዋል። ሌላው አደጋ መጓዝ የነበረበትን መንገድ ወይም ትቶ መድረሻ ጠፍቶ ወደ ሚንከራተቱበት አቅጣጫን መሄድ ነው ብለዋል። ይህን ካሉ በኋላ መንገዳችንን በጽናት እንድንጓዝ፣ እንዳንሳሳትም የሚረዳንና ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እንድንጓዝ የሚመራን ቅዱስ መልአክ እንደሆነ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸው ይህን እገዛ ማግኘት እንድንችል መጸለይ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው በማያያዝም ቅዱስ መልአክ ፍጥረታትን እንዲጠብቅ፣ እንዲከላከል፣ መልካም አቅጣጫን እንዲመለክት ከፈጣሪው የተሰጠው ትዕዛዝ፣ የተቀበለውም አደራ አለበት። ስለዚህ እርሱ የሚለውን ማዳመጥ፣ ለእርሱ መታዘዝ ያስፈልጋል። የምናዳምጠውም በመልአክት በኩል የተላከልንን የመንፈስ ቅዱስን መልዕክት ነው ካሉ በኋላ ለመሆኑ መልአክህ ማን እንደሆነ በስም ታውቁታላችሁ? ከእርሱስ ጋር ትነጋገራላችሁ? ታዳምጡታላችሁ? በሕይወታጭሁ እርሱ እንዲመራችሁ እድል ትሰጡታላችሁ በማለት ጠይቀዋል።

መልአክ ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰንን መንገድ ያሳየናል፣

መላዕክት በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ሥፍራ አላቸው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍርንችስኮስ፣ መልአክት የሚያግዙን መራመድ እንድንችል ጉልበትን በመስጠትና ወደ የት አቅጣጫ ተራምደን ወዴት መድረስ  እንዳለብም ጭምር ነው ብለዋል። ዛሬ በተነበበው በሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌል በምዕ. 8 ቁ. 10 ላይ እንደተጠቀሰው፣ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱንም እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፣ በሰማይ ያሉት የእነርሱ መላዕክት በሰማይ ባለው ባባቴ ፊት ሁል ጊዜ ይገኛሉ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም ጠባቂያችን መልአክ ግንኙነቱ ከእኛ ጋር ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔርም ጋር ይገናኛል። በእግዚአብሔርና በእኛ መካከል ድልድይ በመሆን ከጠዋት እስከ ማታ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እኛን ይጠብቀናል፣ ከእርሱም ጋር ግንኙት እንዲኖረን ያደርጋል፤ እንዲሁም ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰን ትክክለኛው መንገድ የትኛው እንደሆነ ስለሚያመለክት በዘወትር ጉዞአችን ጠባቂና መሪያችን የሆነውን መልአክ መርሳት የለብንም በማለት ለዕለቱ ያቀረቡትን የቅዱሳት መጽሐፍት አስተንትኖ አጠቃልለዋል።                              

02 October 2018, 17:27
ሁሉንም ያንብቡ >