2018.09.14 Messa Santa Marta 2018.09.14 Messa Santa Marta  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሽንፈቶችን መፍራት እንደሌለብን ያስተምረናል”።

በየዓመቱ የምናስታውሰው ስቅለተ ዓርብ ሰይጣን የደረሰበትን ውድቀት ሳይገነዘብ ቀርቶ እጅግ የተደሰተበት እለት እንደነበር ነገር ግን በትልቅ ወጥመድ ውስጥ የወደቀበት ዕለት እንደነበር አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዛሬ ጠዋት በቅድስት ማርታ ጸሎት ቤታቸው፣ በላቲን ስርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር መሠረት ተከብሮ በዋለው የቅዱስ መስቀል ክብረ በዓል ዕለት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሽንፈቶችን መፍራት እንደሌለብን ያስተምረናል፣ ድልም የሚገኘው ከዚያ ነው ብለዋል። ቅዱስነታቸው እርሳቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ለገኙት ምዕመናን፣ ካህናትና ደናግል ባቀረቡት ቃለ ምዕዳን፣ ሽንፈት ያለ ቢሆንም የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የዓለምን ሁሉ ሐጢአት የሚያጠፋ ሃይል ያለው፣ ድልም የተገኘበት እንደሆነ አስረድተዋል። ሰይጣን በዙሪያችን እያጓራ እንደሆነና ከተጠጋነውም ሊያጠቃን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቃለ ምዕዳናቸው እንዳስገነዘቡት የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በሕይወታችን ውስጥ ሽንፈትም፣ ድልም እንዳለ ያስተምረናል ብለው አንዳንድ ክፉ ገጠመኞች ቢኖሩንም መፍራት እንደሌለብንና እነዚህ ክፉ ገጠመኞቻች በቅዱስ መስቀል ላይ በመገለጥ የእግዚአብሔር ሃይል በክፋት ላይ ድልን እንደተቀዳጀ የሚያመለክቱ ናቸው ብለዋል። ሰይጣን በዙሪያችን እየተመላለሰ ሊያጥቃን እንደሚሞክር፣ ከተጠጋነው ደግሞ ሊጎዳን እንደሚችል ዛሬ ተከብሮ በዋለው የቅዱስ መስቀል ክብረ በዓል ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን አስረድተዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ ሽንፈት የእኛን ክፉ ቀናትን ያስታውሳል፣

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በስብከታቸው እንደገለጹት የክርስቲያን ምልክት በሆነው ቅዱስ መስቀል ላይ የደረሰውን ሽንፈት እናስተነትናለን። ነገር ግን ይህ ቅዱስ መስቀል ድልም ያለበት እንደሆነ አስገንዝበዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወት ዘመኑ ያከናወናቸው ሥራዎች፣ እርሱን ይከተሉ የነበሩ ሰዎች ያደረጉት ተስፋም በሙሉ በመስቀል ላይ ሽንፈት እንዳጋጠመው ማሰብን መፍራት የለብንም ብለዋል። በዕለቱ የተነበበውን ሁለተኛውን ንባብ፣ የሐዋርያው የጳውሎስ መልዕክት ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች በምዕ. 2. 6-11 ላይ የተጠቀሰውን በማስታወስ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን መለኮታዊ ባሕርን አስመልክቶ ሐዋርያው ጳውሎስ በተናገረው መልዕክቱ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል የሚያደርገውን መለኮታዊ ባሕርውን እንደያዘ መቅረት አልፈለገም። ይልቁንም ያለውን ክብር በገዛ ፈቃዱ ትቶ አገልጋይ መሆንን መረጠ፤ በሰው ምሳሌም ተገለጠ። እንደሰው ሆኖ ራሱን ዝቅ አደረገ፤ እስከ ሞት ድረስ ያውም በመስቀል ላይ ተሰቅሎ እስከ መሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ” ማለቱን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው ስብከታቸውን በመቀጠል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለምን ሐጢአት በሙሉ ተሸከመ፣ ያንን ክብር ሁሉ ትቶ ተናቀ፤ ሐዋርያው ጳውሎስም የኢየሱስ ክርስቶስን ሽንፈት ሲናገር ምንም አላፈረም ካሉ በኋላ ይህ ንግግሩ የእኛንም ሽንፈት ግልጽ ያደርገዋል ብለው የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ለእኛ ለክርስቲያኖች የድል ምልክት ነው ብለዋል።            

ስቅለተ አርብ ሰይጣን በትልቅ ወጥመድ የወደቀበት ዕለት ነው፣

ከኦሪት ዘዳግም የተነበበው የመጀመሪያ ንባብ፣ የእስራኤል ሕዝብ በስደት ላይ እያሉ ባጉረመረሙ ጊዜ በእባብ መነደፋቸው ሰይጣን ከጥንት ጀምሮ ጥቃቱን ይሰነዝር እንደነበር ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል። እስራኤላዊያንን ለሞት ይዳርግ የነበረ እባብ፣ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደተናገረው ለእስራኤላዊያን የመዳን ምክንያት ሆኗል ብለዋል። በተመሳሳይ መንገድ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደገለጹት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ሰይጣን ለጊዜው እንዲያሸንፍ ፈቀደ፤ ይሁን እንጂ በየዓመቱ የምናስታውሰው ስቅለተ ዓርብ ሰይጣን የደረሰበትን ውድቀት ሳይገነዘብ ቀርቶ እጅግ የተደሰተበት እለት እንደነበር ነገር ግን በትልቅ ወጥመድ ውስጥ  የወደቀበት ዕለት እንደነበር አስረድተዋል።

ሰይጣን በዙሪያህ ስለሚያገሳ አትጠጋው፣

ድላችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ነው ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል መጠጊያችን ስለሆነ ወደ እርሱ መመልከትን ማቋረጥ የለብንም፤ ምክንያቱም ለጉዞአችን ሃይል የምናገኘው ከእርሱ ነውና፤ ያ የተሸነፈው ሰይጣን አሁንም በዙሪያችን እያገሳ ነው፤ የተጠጉት እንደሆነ ሊያጠቃንም ይችላል ብለዋል።

በኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ሥር የሽንፈትና የድል ምልክቶች አሉ፤

ሞትን ድል ካደረገው፣ ከአሸናፊው ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በሕይወት እንድንጓዝ መንፈስ ቅዱስ ይጋብዘናል። የምንጓዘውም ሊያጠቃን ከተዘጋጀ ሰይጣን ጋር እንደሆነ መዘንጋት የለብንም ብለው ጠላታችን ወደ ሆነው ሰይጣን መቅረብ የለብንም፣ አለበለዚያ ሊውጠን ይችላል ብለዋል።

የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልም የሚያስተምረን ይህን ብለው በሕይወት መካከል ሽንፈትም ድልም እንዳለ አስረድተዋል። ስለዚህ ሽንፈትን ለመቋቋም ዝግጁዎች መሆን አለብን፤ ብንሸነፍም እንኳ፣ ሐጢአተኞች ብንሆንም እንኳ በትዕግስት መጽናት ያስፈልጋል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሐጢአታችን ሞቷልና፣ በመሆኑም ምህረትን መለመን እንጂ በሰይጣን ለመሸነፍ ራሳችንን አሳልፈን መስጠት የለብንም ብለዋል። በማከልም ጥቂት ደቂቃዎችን ወስደን እቤታችን ውስጥ ወይም በአንገታችን ያለውንና የሽንፈታችን ምልክት የሆነውን ቅዱስ መስቀል እንመልከት፤ እግዚአብሔር ድልን የተቀዳጀበትና ለእኛም የድል ምልክት የሆነው እርሱ ነውና፤ በማለት የዕለቱን ቃለ ምዕዳናቸውን አጠቃልለዋል። 

14 September 2018, 17:26
ሁሉንም ያንብቡ >