ታሪካዊው የኪየቭ ካቴድራል በሩሲያ የአየር ድብደባ መጎዳቱ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ሩስያ ማክሰኞ ሰኔ 3/2017 ዓ. ም. በኪየቭ እና ኦዴሳ ላይ ባፈጸመችው መጠነ ሰፊ የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ሰባት ሰዎች ሲገደሉ፥ ወደ አሥራ ሦስት የሚደርሱ ሰዎች ቆስለዋል። ይህ ጥቃት ታሪካዊውን የቅዱስ ጥበብ ካቴድራልንም እንደጎዳው ታውቋል። “ሩሲያ ከ 315 በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የፈጸመችው የአምስት ሰዓት ጥቃት በሦስት ዓመት ጦርነት በዩክሬን ዋና ከተማ ላይ ከተፈጸሙት ጥቃቶች መካከል ትልቁ ነው” ሲሉ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ተናግረዋል።
የዩክሬን የባህል ሚኒስትር ማይኮላ ቶቺትስኪም በበኩላቸው፥ ፍንዳታው በካቴድራሉ ዋና ጫፍ ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸው፥ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት መመዝገቡን ከጥንት ጀምሮ ከሩስ የመጡ ካቶሊኮችን እና ኦርቶዶክሶችን ጨምሮ የሁሉም ክርስቲያኖች እናት ቤተ ክርስቲያን ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል።
የኪቫን ሩስ ታላቁ ልዑል ቮልዲሚር ክርስትናን በባይዛንታይን ሥርዓት በ10ኛው ክፍለ ዘመን የተቀበለ ሲሆን፥ የካቴድራሉ ግንባታ በ11ኛው ክፍለ ዘመን የተጀመረ መሆኑ ይታወሳል።
የዩክሬን የግሪክ ካቶሊካዊት የፊላዴልፊያ ሊቀ ጳጳስ ሜትሮፖሊታን ቦሪስ ጉዲዚያክ፥ “ማክሰኞ ምሽት የተፈጸመው ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት በዩክሬን እምብርት ባለው በቅድስት ጥበብ ካቴድራል ወይም ቅድስት ሶፊያ ካቴድራል ተብሎ በሚታወቅ ካቴድራል ላይ የደረሰ ግዙፍ ጥቃት እንደሆነ አስረድተዋል።
“ይህ የተቀደሰ ቦታ ለአንድ ሺህ ዓመታት ወረራዎችን እና የኮሚኒስቶችን ስደት ተቋቁሟል” ሲሉ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ሜትሮፖሊታን ቦሪስ ጉዲዚያክ፥ የቅድስት ሶፊያ ካቴድራል በፓሪስ እንደሚገኝ የኖትር ዴም ካቴድራል፣ በሮም እንደሚገኝ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ፣ በሜክሲኮ ሲቲ እንደሚገኝ የጓዳሉፕ ካቴድራል እና በኒውዮርክ ከተማ እንደሚገኘው የቅዱስ ፓትሪክ ካቴድራል፥ ለሀገር ልዩ የሆነ መንፈሳዊ ተምሳሌት እና የሞራል ጠቀሜታ ያለው እንደሆነ አስረድተዋል
“ሩስያ በዩክሬን ላይ ያካሄደችው ወረራ እና ሳያቋርጥ ዕለት ተዕለት የፈጸመቻቸው የቦምብ ጥቃቶች ምንም እና ማንንም ሳያስተርፍ ንጹሃን ዜጎችን የገደለ ነው” ሲሉ ተናግሯል። በዚህ ጦርነት ከ4,000 በላይ ትምህርት ቤቶች መውደማቸውን፣ ወደ 1,600 የሚጠጉ የሕክምና ተቋማት እና 236,000 የመኖሪያ ሕንፃዎች መጎዳታቸውን ወይም መውደማቸውን ዘግበዋል።
ጦርነቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በየካቲት 2022 ዓ. ም. ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ካቶሊካዊ የቅርብ ምሥራቅ የበጎ አድራጎት ማህበር፥ በዩክሬን ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ቡድኖች ጋር በመተባበር የዩክሬን ግሪክ ካቶሊካዊ ቤተ ክርስትያን፣ ካሪታስ ዩክሬን፣ የዩክሬን ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ እና የሃይማኖት ማኅበረሰቦችን ጨምሮ የምግብ፣ የሕክምና እንክብካቤ፣ የመጠለያ እና የስነ-ልቦና ድጋፍ በመስጠት ከ3.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዕርዳታ መስጠቱ ታውቋል።
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጓድዚያክ፥ “ይህንን ሥቃይ የሚረዱት በሙሉ ለንጹሐን ሰዎች ደኅንነት፣ ለቤተ ክርስቲያናቸው ጥበቃ፣ ለማንነታቸው እና አኗኗራቸው፣ እንዲሁም በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የታፈኑ ሕጻናት ለሚመለሱበት ፍትሐዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲጸልዩ” በማለት ተማጽነዋል።
የዩክሬን አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት በካቴድራሉ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት በማውገዝ ባወጣው መግለጫ፥ “በሩስያ ፌዴሬሽን እየተፈጸመ ያለውን አረመኔያዊ ድርጊት ለማስቆም መላው የሰለጠነ ዓለም አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ” በማለት ጥሪውን አቅርቧል።
“ሩሲያ ጠቅላላ ወረራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ 670 አብያተ ክርስቲያናት እና የአምልኮ ሥፍራዎች ወድመዋል ወይም ተጎድተዋል” ያለው መግለጫው፥ “ከልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት እና የሃይማኖት ድርጅቶች የተውጣጡ 60 ቀሳውስት በሩሲያ ወራሪዎች መገደላቸውን ብዙ ቀሳውስት እና ፓስተሮች በሕገወጥ መንገድ ተይዘው በሩሲያ ግዞት ውስጥ ይገኛሉ” ሲል አክሏል።
የቦታው የመጀመሪያ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቫዲም ኪሪሌንኮ፥ ካቴድራሉ ፍተሻ ተደርጎለት እንደሚጠገን ተናግረዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2022 ዓ. ም. ሩስያ በዩክሬን ወረራ ከጀመረች ወዲህ ካቴድራሉን ጉዳት ሲደርሰው ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ተናግረዋል።
የሩስያ ጥቃት የፈጠረውን ስጋት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2023 ካቴድራሉን አደጋ ላይ ከሚገኙ የዓለም ቅርሶች መዝገብ ውስጥ ማስገባቱ ይታወሳል።
አንድ የማኅበራዊ ሚዲያ በ X ገጹ ላይ ቀደም ሲል ባሳየው የኦዴሳ ፎቶዎች በከተማው ውስጥ በሚገኝ በወሊድ ሆስፒታል እና የመኖሪያ ሕንፃዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።
ሩስያ ማክሰኞ ዕለት ከፈጸመችው ጥቃት አንድ ቀን በፊት ወደ 500 የሚጠጉ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና 20 ሚሳኤሎች በዋነኛነት በማዕከላዊ እና በምዕራብ ዩክሬን በሚገኙ ኢላማዎች ላይ ማስወንጨፏ ይታወሳል። ሩስያ ይህንን ጥቃት ዩክሬን ግንቦት 24/2017 ዓ. ም. በሰው አልባ አውሮፕላኖች ሩስያ ውስጥ በሚገኙ በርካታ የአየር ካምፖችን ላይ ለፈጸመችው ጥቃት የበቀል እርምጃ ነው ስትል ተናግራለች።
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ቦታ ጥበቃ ክፍል እንዳለው፥ ካቴድራሉ ጥንታዊ የውስጥ ክፍሎቹን ጠብቆ ያቆየው ሲሆን፥ በ11ኛው መቶ ዘመን የነበሩት የሙሴ ምስሎች እና የግርጌ ምስሎች ስብስብ በአቋማቸው ልዩ ናቸው” ሲል ገልጿል።