በማይናማር የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ እንደሚያሳስባት ገለጸች
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
በማይናማር የማንዳላይ ሃገረ ስብከት ሃዋሪያዊ አስተዳዳሪ የሆኑት አባ ፒተር ሴይን የቫቲካን የዜና ወኪል ከሆነው ፊደስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሃገሪቷ በአጠቃላይ ጦርነቱ በሚካሄድባቸው ቦታዎች በሙሉ ሰላማዊ ሰዎች ግጭቱን በመሸሽ እንደሚፈናቀሉ እና ከባድ ስቃይን እያስተናገዱ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ በተለይ በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ የሚገኘው ሳጋይንግ መንደር በግጭቶች፣ በቦምብ ጥቃቶች እና በሰላማዊ ህዝብ ላይ በሚደርሰው ከፍተኛ ስቃይ የተጠቃ እንደሆነ ገልጸዋል።
የቤተ ክርስቲያን መሪዎቹ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እሑድ ሰኔ 8 ቀን 2017 ዓ.ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ባቀረቡት የመልአከ እግዚያብሄር ጸሎት ወቅት በማይናማር እየተካሄደ ያለውን ሁከት ማስታወሳቸውን አወድሰው፣ ይህ በችግሩ የተነሳ የተገለሉ ሆነው ለሚሰማቸው ማህበረሰቦች የሚያበረታታ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፥ አባ ፒተር ይሄን አስመልክተው “ብጹእነታቸው ማይናማርን በማስታወስ ለተናገሩት ነገር እና ለሰላማዊው ህዝብ ስቃይ ላሳዩት ትኩረት እናመሰግናቸዋለን” በማለት ገልጸዋል።
አባ ፒተር ከዚህም በተጨማሪ በደቡባዊ ማንዳላይ የምትገኘው ሳጋይንግ ከተማ በተከታታይ በሚደረጉ የቦንብ ጥቃቶች ምክንያት እየወደመ እና ወደ ፍርስራሽነት እየተቀየረ መሆኑን አስታውሰዋል።
በገዥው አካል እና በተቃዋሚዎች በተያዙ ግዛቶች የተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ካቶሊኮች መከራ እየደረሰባቸው እንደሆነ ያስታወሱት ካህኑ፥ እነዚህ ህዝቦች ምንም ዓይነት ረዳት እና ጥበቃ የሌላቸው ናቸው በማለት በአጽንዖት ገልጸዋል።
አከባቢው አደገኛ መሆኑ ቢታወቅም ካህናት፣ ገዳማዊያት እና ካታኪስቶች በተጎዱ አካባቢዎች እርዳታ እና መንፈሳዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የገለጹት አባ ፒተር፥ ካህናቶቹ በድፍረት በአከባቢው ለሚገኙ ሰዎች፣ በተለይም ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን ለመደገፍ የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች እንኳን ማግኘት የማይችሉትን አረጋውያን፣ ሴቶች እና ሕፃናትን እያገዙ እንደሆነ ጠቅሰው፥ ካህናቶቹ ከገዳማዊያት እና ካቴኪስቶች ጋር በመሆን በግጭቱ ምክንያት በተጎዱ በጣም አደገኛ በሆኑ አካባቢዎች ማህበራዊ አገልግሎቶችን እየሰጡ እንደሆነ አብራርተዋል።
ሃገረ ስብከቱም ቢሆን በአከባቢው እየተካሄደ ያለውን ቀውስ ያባባሰውን እና በቅርቡ ከተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ የእርዳታ ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉን የገለጹት ካህኑ፥ ለህዝቦቻቸው ሰላም እና ለሃገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የአምልኮ ሥርዓቶችን እና የጸሎት ዝግጅቶችን እንደሚያደርጉ እንዲሁም በየቀኑ ጸሎት ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ፣ ብሎም በዚህ አስከፊ ሁኔታ በእግዚአብሔር በመታመን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በያንጎን ከተማ የካቶሊክ ሃይማኖት ተከታይ እና የዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ጆሴፍ ኩንግ በበኩላቸው እየተባባሰ ያለው የሰብአዊ ሁኔታ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ፥ ቅድስት መንበር ለቀውሱ የሰጠችውን ትኩረት በአድናቆት እንደሚቀበሉት የገለጹ ሲሆን፥ ‘ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንደተናገሩት በመላ አገሪቱ የሲቪል መሰረተ ልማቶች በታጠቁ ሃይሎች መጠቃታቸው እና መውደማቸው ቀጥሏል’ ሲሉ ለፊደስ ኒውስ ተናግረዋል።
በጣም አሳዛኙ ነገር ትምህርታቸውን ለመማር ብለው ከቤት የወጡ ህፃናት ተማሪዎች የሚገኙበት ትምህርት ቤቶች ሲጠቁ እንደሆነ የገለጹት አቶ ጆሴፍ፥ በቅርቡ በሳጋንግ ከተማ ሥር ባለችው ክዊን መንደር ላይ በደረሰው የአየር ጥቃት 20 ተማሪዎች እና ሁለት መምህራን መሞታቸውን ጠቁመው ይህ ከባድ የሆነ ስቃይ እና ቁጣ ምንጭ ነው በማለት ገልጸውታል።
ግጭቱ በካቺን፣ ቻይን እና ራክሂን ግዛቶች ሰላማዊ ዜጎችን ማፈናቀሉን ቀጥሏል ያሉት አቶ ጆሴፍ፥ ከባማው እና ማይትኪና ሀገረ ስብከት የወጡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት በአከባቢው ከባድ ውድመት እንደደረሰ እና ነዋሪዎች ለመፈናቀል መገደዳቸውን ያመለክታሉ ብለዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሰላም ጥሪ ለብዙዎች የተስፋ ምንጭ እንደሚሆን እና ከአራት ዓመታት የእርስ በርስ ግጭት በኋላ እንደተረሱ ለሚሰማቸው ማህበረሰቦች የአብሮነት ስሜት እንደሚፈጥር የጠቆሙት አቶ ጆሴፍ በመጨረሻም፥ ምእመናን መከራቸውን ለእግዚአብሔር እና ለቅድስት ድንግል ማርያም አደራ በመስጠት በጸሎት ጸንተው እየኖሩ እንደሆነ አበክረው ተናግረዋል።