ፈልግ

የካሪታስ እየሩሳሌም ዳይሬክተር አንቶን አስፋር በዌስት ባንክ በሚገኘው ጄኒን የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የካሪታስ እየሩሳሌም ዳይሬክተር አንቶን አስፋር በዌስት ባንክ በሚገኘው ጄኒን የስደተኞች ካምፕ ውስጥ   (Caritas Jérusalem )

ካሪታስ እየሩሳሌም በጋዛ እና በዌስት ባንክ ከፍተኛ የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎቶች መኖሩን ገለጸ

በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ሁኔታ የበለጠ እየተባባሰ በሄደበት በአሁን ወቅት ካሪታስ እየሩሳሌም በጋዛ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ እና በዌስት ባንክ ደግሞ የምግብ እርዳታ እያደረገ እንደሚገኝ የተቋሙ ዳይሬክተር የሆኑት አንቶን አስፋር ተናግረዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ካሪታስ እየሩሳሌም በጋዛ እና በዌስት ባንክ በጦርነቱ ምክንያት ሁሉንም ነገራቸውን ካጡት ተጎጂዎች መካከል በመገኘት የህይወት አድን ሰብአዊ ስራ የሚሰሩ ቡድኖች እንዳሉት ተገልጿል።

ኢራን እያስወነጨፈችው የምትገኘው ሚሳኤል በእስራኤል አንዳንድ አከባቢዎች ላይ አደጋ እያደረሰ ቢገኝም፥ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅት የሆነው ካሪታስ ኢየሩሳሌም በአደገኛ እና አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳን ተልዕኮውን እንደቀጠለ የካሪታስ እየሩሳሌም ዳይሬክተር አንቶን አስፋር ተናግረዋል።

ሰኔ 6 ቀን 2017 ዓ.ም. አርብ ዕለት እስራኤል በኢራን ላይ የጀመረችውን ጥቃት ተከትሎ፣ የቤተክርስቲያኑ የእርዳታ ኤጀንሲ በዚህ አዲስ ግልጽ ጦርነት ውስጥ የሰብአዊ ጥረቱን መቀጠል ያለውን አደጋ ለመገምገም እንቅስቃሴውን ለአፍታ አቁሞ የነበረ መሆኑም የተናገሩት አቶ አስፋር፥ ሆኖም ግን “ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ እርዳታ ፍላጎቶች” ስለገጠማቸው በማግስቱ ድጋሚ ሥራውን እንዳስጀመሩ ገልጸው፥ በአሁኑ ወቅት ለህዝቡ እርዳታ ለመስጠት ግንባር ላይ እንደሆኑ፣ ብሎም እንደ የቤተክርስቲያን ዋና ድርጅት እና ማህበራዊ ክንድ ስራቸውን መቀጠል እንደነበረባቸው በአጽንዖት ገልጸዋል።

የመድሃኒት እጥረት
ካሪታስ እየሩሳሌም በጋዛ ሰርጥ አስቸኳይ እርዳታ ለመስጠት 122 የቡድን አባላትን በአስር የህክምና ማዕከላት እንዳሰማራ የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ እነዚህ ቡድኖች ሥራቸውን የሚያከናውኑት በቦምብ ድብደባ ውስጥ ሆነው፣ በተለይም በሰሜኑ ክፍል ውስጥ በየቀኑ የሞት አደጋ እንደሚያጋጥማቸው ገልጸዋል።

በአከባቢው የሚታየውን የመድሃኒት፣ የምግብ እና የመጠጥ ውሃ እጥረትን በመጥቀስ “ሁኔታው አስከፊ” መሆኑን የገለጹት አቶ አስፋር፥ በቅርብ ጊዜ ተደርጎ በነበረው የተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት የሚችሉትን ያህል መድሃኒት እና የህክምና ቁሳቁሶችን ይዘው ወደ ስፍራው እንደሄዱ፥ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የሰብአዊ እርዳታ ቁሳቁሶቻቸው እያለቁ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህም ምክንያት ቡድኖቻቸው አንዳንድ ጊዜ ከዓለም ጤና ድርጅት ወይም ከሌሎች አጋሮች መድሃኒቶችን ተቀብለው እንደሚሰሩም ጭምር አብራርተዋል።

አቶ አስፋር በጋዛ ሰርጥ ልብን የሚሰብሩ የዕለት ተዕለት የህይወት ትዕይንቶች እንደሚገጥማቸው አስታውሰው፥ ከእነዚህም መካከል ህፃናት በባዶ እግራቸው ሆነው የምግብ ፍርፋሪ ለማግኘት በቆሻሻ መጣያ ሥፍራዎች እንደሚርመሰመሱ፣ ተላላፊ በሽታዎችን የሚያሰራጩ ትንኞች በአከባቢው በስፋት መኖራቸውን እና ለተጎጂዎች ምግብ የሚያሰራጩ የጋዛ ሰብአዊ እርዳታ ፋውንዴሽ ወደ ሞት ቀጠናነት ሲለወጥ ማየታቸውን በሃዘኔታ ገልጸዋል።

የማያቋርጥ የቦምብ ጥቃት
የቦምብ ጥቃቶች በተደጋጋሚ በሚፈፀምበት ጋዛ በሚገኘው የቅዱስ ቤተሰብ ካቶሊካዊ ሰበካ አከባቢ የሚገኙ ክርስቲያኖች በዝግታ እና በሂደት መተንፈሻ አካልን በሚያጠቃ ህመም እየተሰቃዩ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፥ ካሪታስ እየሩሳሌም በጋዛ ብቸኛው የካቶሊክ ደብር አስተዳዳሪ ከሆኑት ከአባ ገብርኤል ሮማኔሊ ጋር እርሳቸውን ማግኘት በሚቻልበት ጊዜ ሁሉ በቅርበት እንደሚገናኝ የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ በቅርቡ ካህኑ የመገናኛ ሲግናሎችን ለማግኘት የቤተክርስቲያኑ ጣሪያ ላይ መውጣት ግዴታ እንደሆነባቸው ገልጸዋል።

የካሪታስ እየሩሳሌም ዳይሬክተር እንዳሉት የተቋሙ የቡድን አባላት በአስቸጋሪ አከባቢዎች እየተንቀሳቀሱ ስለሚሰሩ ሁሌም ስጋት ውስጥ እንደሆኑ ጠቁመው፥ “ቡድኖቻችንን ለአደጋ ማጋለጥ ስለማንፈልግ ሁኔታውን እንደገና ለመገምገም እንገደዳለን” ያሉ ሲሆን፥ ህግ አልባ ዞን በሆነችው ጋዛ ውስጥ መንቀሳቀስ በጣም አደገኛ እንደሆነ አክለው ተናግረዋል።

'ዌስት ባንክ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው'
ካሪታስ እየሩሳሌም በዌስት ባንክ ስላለው አስከፊ ሁኔታ ማስጠንቀቂያ የሰጠ ሲሆን፥ በቅርቡ የሰሜኑን አከባቢ ጎብኝተው የተመለሱት አቶ አስፋር አዳዲስ ግንቦችና ሰፈሮች ሲገነቡ መመልከታቸውን ተናግረዋል። ከኢየሩሳሌም በስተሰሜን 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘውን የሲንጂል መንደር በአሁኑ ወቅት ብዙ ሜትሮች ከፍታ ባላቸው የሽቦ አጥር መከበቧን ጠቁመው “በምድር ላይ ጉልህ የሆኑ ለውጦች” ማየታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ በዌስት ባንክ ውስጥ ከ900 ያላነሱ የፍተሻ ኬላዎች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ አስፋር፥ በዌስት ባንክ የመንቀሳቀስ ነፃነት በጣም እንደተገደበ እና በዚህም ምክንያት ከተማዋ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች አመላክተዋል።

በእነዚህ ገደቦች ምክንያት የግብርና፣ የትምህርት እና አጠቃላይ ኢኮኖሚው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መግባቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ወደ ቅድስት ሀገር የሚደረገው ጉዞ በመቋረጡ እንደ ቤተልሔም ያሉ በርካታ ከተሞች መዳከማቸውን ገልጸዋል።

ወደ 200,000 የሚጠጉ ሰራተኞች በዌስት ባንክ ውስጥ ሥራ አጥ እንደሆኑ ካሪታስ እየሩሳሌም ይፋ ያደረገ ሲሆን፥ ተቋሙ ለግብርና የሚሆኑ ምርጥ ዘሮችን በማቅረብ እንዲሁም የልብስ ስፌት እና ምግብ ዝግጅት የመሳሰሉ ለተለያዩ የሥራ ፈጠራ ፕሮጀክቶች ጥቃቅን ድጎማዎችን በማቅረብ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት እየጣረ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከ40,000 በላይ ተፈናቃዮች
ካሪታስ እየሩሳሌም በጄኒን፣ ኑር ሻምስ እና ቱልካረም ካምፕ ውስጥ ከሚኖሩት 40,000 ስደተኞች ጋር እየሰራ እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ እነዚህ ከአከባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ምንም ነገር እንደሌላቸው ገልጸው ምግብ፣ የንፅህና መጠበቂያ ዕቃዎች፣ እና አንዳንድ አስፈላጊ ቀሳቁሶች እንደሚያስፈልጓቸው እንዲሁም እነሱን ለመርዳት የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ እንደሆነ ብሎም በዌስት ባንክ ሰሜናዊ ክፍል የህክምና ቀናት እና የስነ-ልቦና ድጋፍ ፕሮግራሞችን እንደሚጀምሩ አብራርተዋል።

የካሪታስ እየሩሳሌም ዳይሬክተሩ እሳቸው እና ቡድናቸው ተስፋ እንደማይቆርጡ ጠቅሰው፥ ጦርነቱን ለማስቆም ዓለም አቀፍ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፥ የተሻለ ቀናት እንደሚመጡ ተስፋ እንዳላቸው ከሁሉም በላይ በእምነታቸው እንደሚተማመኑ ገልጸው፥ “ማህበረሰቡ የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን በውስጡ ተስፋን እንደገና ለመዝራት እየሞከሩ እንደሆነ በአጽንዖት ከገለጹ በኋላ፥ በመጨረሻም በዓለም ዙሪያ ባሉ አጋሮቻቸው ድጋፍ የበለጠ እንደሚበረታቱ ተናግረዋል።
 

19 Jun 2025, 13:24