የአፍሪካ እና የአውሮፓ ብጹአን ጳጳሳት ‘አፍሪካ ፍትህ እንጂ ምፅዋት አትፈልግም’ አሉ
አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መጪው ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሚያደርጉት ስብሰባ በፊት የሁለቱ አህጉራት ጉባኤዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ “አውሮፓውያን ቅድሚያ በሚሰጧቸው ጉዳዮች ላይ ጥልቅ የሆነ ለውጥ መደረግ” እንዳለበት አሳስበዋል።
ከአምስት ዓመት በፊት ጀምሮ እስከ ዛሬ…
ከግማሽ አስር ዓመታት በፊት የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ሲምፖዚዬም እና የአውሮፓ ህብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን እንዳረጋገጡት አውሮፓ እና አፍሪካ በጋራ ታሪኮቻቸው እና በጂኦግራፊያዊ ቅርበታቸው የተመሰከረውን የረጅም ጊዜ ግንኙነታቸውን በማጠናከር፣ የጋሪዮሽ ትብብርን የማበረታታት አቅም እንዳላቸው ‘በጽኑ እርግጠኞች’ መሆናቸውን አበክረው ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።
ሆኖም ሁለቱ የብጹአን ጳጳሳት ጉባኤዎች ግንቦት 7 ባወጡት መግለጫ አሁናዊ ሁኔታዎችን ሲገልጹ፥ “በጣም ደካማ ከሆኑ ክልሎች እና ማህበረሰቦች ጋር ያለውን ትብብር ከማበረታታት ይልቅ ወደ ጠባብ የጂኦፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ስብስብ ማተኮሩ ይበልጥ እንደሚያሳስባቸው በአጽንዖት ገልጸዋል።
ምን መደረግ አለበት?
አሁን ላይ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚነሱት ሃሳቦች ወደ “ነባሩ ጭብጦች” መቀየር እንዳለባቸው የጠቆመው መግለጫው፥ “የአውሮፓ ኮርፖሬሽን እና ስትራቴጂካዊ ዓላማዎች በአፍሪካውያን እውነተኛ ፍላጎቶች እና ምኞቶች ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን ችላ በማለት ወደአልተገባ ተግባር መሻገራቸውን” በማሳሰብ፥ ይሄም ማለት የህይወት መሰረታዊ ፍላጎቶች የሆኑት መሬት፣ ውሃ፣ ዘር እና ማዕድኖች “ለውጭ ሃገራት ትርፍ” ሸቀጥ ሆነዋል በማለት አብራርቷል።
ይህም በመሆኑ የአፍሪካ አህጉር የአውሮፓን የካርቦን ልቀትን የመቀነስ ተነሳሽነቶችን ለመደገፍ ስትል፥ በ “አረንጓዴ ኢነርጂ” ፕሮጄክቶች አካል በመሆን ወይም የግብርና ኢንዱስትሪው መርዛማ ግብዓቶችን እና ቆሻሻዎችን ወደ ሌሎች ክልሎች ለማሸጋገር በተደረጉ የመሬት ስምምነቶች በኩል ስነ-ምህዳሮቿን እና ማህበረሰቦቿን አደጋ ላይ እንድትጥል እየተደረገ ነው በማለት መግለጫው አሳስቧል።
የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ሲምፖዚዬም እና የአውሮፓ ህብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን መግለጫ በማከልም አሁን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ‘ወዳጅነትን እና ፍትህን አያረጋግጥም’ በማለት በአጽንዖት ገልጿል።
የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ጥረት ይቀጥላል
መግለጫው የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስን ሃዋሪያዊ መልዕክት ‘ላውዳቶ ሲ’ን በማስታወስ፥ የብጹአን ጳጳሳት ጉባኤዎቹ “በመላው አፍሪካ በጉልህ የሚሰማው እና ግልጽ” የሆነውን “የምድራችንን እና የድሆችን ጩኸት” በመጥቀስ፥ የአፍሪካ ሀገራት በእነሱ እና በአውሮፓ መካከል ባለው ግንኙነት አለመመጣጠን የተነሳ እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ ጠቁሟል።
የሁለቱ አህጉራት ጉባኤዎች የአየር ንብረት ለውጥ፣ የብዝሀ ህይወት መጥፋት እና የአፈር መራቆት ያስከተሉትን ውጤቶች ጠቅሶ፥ በአፍሪካ አህጉር ረሃብ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ እንደሆነ በማጉላት፥ ይህም የሆነበት ምክንያት “የምግብ እጥረት ስላለን ሳይሆን ከህዝብ በፊት ለትርፍ ቅድሚያ የሚሰጡ ስርዓቶች እንዲስፋፉ ስለፈቀድን ነው” በማለት ገልጸዋል።
ለለውጥ የተደረገ ጥሪ
ሁለቱ ጉባኤዎች ግንቦት 13 በብራስልስ የሚሰበሰቡት የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች “የአፍሪካ ህዝቦችን ሰብአዊ ክብር በአፍሪካ ህብረት እና በአውሮፓ ህብረት አጋርነት ማዕከል እንዲያደርጉ በማሳሰብ፥ “በምግብ ራስን ለመቻል ቁልፍ” የሆነውን በአርሶ አደሩ የሚተዳደር የዘር ሥርዓትን የመጠበቅ እና የማበረታታት አስፈላጊነትን በማጉላት አንስተዋል።
የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ሲምፖዚዬም እና የአውሮፓ ህብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን መግለጫ ከሃሳባዊ ወደ ተጨባጭ የሆኑ ተግባራት እንዴት ወደፊት መራመድ እንደሚቻል የሚያሳዩ የተወሰኑ ምሳሌዎችን የያዘ የድርጊት ጥሪ በማቅረብ፥ “በከፍተኛ ሁኔታ አደገኛ የሆኑ ፀረ ተባይ ኬሚካሎችን ወደ አፍሪካ መላክ እና መጠቀም በአስቸኳይ እንዲታገድ” ድጋፍ እንደሚያደርጉ ከገለጹ በኋላ፥ በአውሮፓ የተከለከሉ ኬሚካሎች አሁንም ድረስ እየተመረቱ ለአፍሪካ አርሶ አደሮች እየተሸጡ እንደሆነ ጠቁመው፥ ይህ ኢፍትሃዊነት በአስቸኳይ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።
መግለጫው በመጨረሻም የአፍሪካን አህጉር እና ስነ-ምህዳሯን እንዴት በተሻለ ሁኔታ መንከባከብ እና ማክበር እንደሚቻል በርካታ አስተያየቶችን ካቀረበ በኋላ፥ “አፍሪካ በአሁኑ ወቅት ምጽዋት ሳይሆን፥ ከዚህም ይልቅ ፍትህ እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ አጋርነት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ሰብአዊ ክብርን ማዕከል ያደረገ ውይይት” እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል። ይህንን ለማድረግ የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት ሚኒስትሮች የአፍሪካ ሲቪል ማህበረሰብን፣ ተወላጆችን እና የእምነት ማህበረሰቦችን የበለጠ በትኩረት እንዲያዳምጡ ብሎም እንደ ተሳታፊ ብቻ ሳይሆን እንደ ረዳት ፖሊሲ አውጪዎችም ጭምር እንዲመለከቷቸው የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ብጹአን ጳጳሳት ጉባኤ ሲምፖዚዬም እና የአውሮፓ ህብረት የጳጳሳት ጉባኤዎች ኮሚሽን ጥሪያቸውን አቅርበዋል።