ፈልግ

አንዳንድ ደቡብ ሱዳናውያን ምዕመናን የቤንቲዩ ሃገረ ስብከት ጳጳስ ከሆኑት ብጹእ አቡነ ክርስቲያን ካርላሳሬ ጋር አንዳንድ ደቡብ ሱዳናውያን ምዕመናን የቤንቲዩ ሃገረ ስብከት ጳጳስ ከሆኑት ብጹእ አቡነ ክርስቲያን ካርላሳሬ ጋር 

የደቡብ ሱዳን ጳጳስ ለሁሉም ህዝቦች ተስፋ እንድንሰጥ ተጠርተናል አሉ

በደቡብ ሱዳን የቤንቲዩ ሃገረ ስብከት ጳጳስ የሀገሪቱ እየታየ የሚገኘው የሰላም እጦት በአመጽ፣ በፖለቲካ አለመረጋጋት እና ሊተነበይ በማይችል የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት መሆኑን በመግለጽ፥ እነዚህ ችግሮች የደቡብ ሱዳን ህዝብ አሁን ያለበትን እውነታ ይገልፃሉ ማለታቸው ተነግሯል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

የዓለማችን ትንሿ ሀገር የሆነችው ደቡብ ሱዳን እንደገና ወደ ግጭት ለመግባት አፋፍ ላይ እንደሆነች የተገለጸ ሲሆን፥ ለፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ታማኝ በሆነው በደቡብ ሱዳን ህዝብ መከላከያ ሃይል (SSPDF) እና ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪክ ማቻርን በሚደግፉ የነጩ ጦር ሚሊሻ መካከል በተፈጠረው ግጭት የሀገሪቱ ሰላም ስጋት ውስጥ ገብቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ ታህሳስ ወር ላይ ሊደረግ ታቅዶ የነበረው ምርጫ ወደ 2019 ዓ.ም. መገባደጃ ላይ እንዲደረግ ተላልፏል። ይህ የፖለቲካ አለመረጋጋት በ 2011 ዓ.ም. በሁለቱ ወገኖች መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ሊያፈርስ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።

ቤተክርስቲያን ለሕዝብ
በዚህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመጣው አለመረጋጋት መካከል የቤንቲው ሃገረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብጹእ አቡነ ክርስቲያን ካርላሳሬ እንደተናገሩት ቤተክርስቲያኗ ሰላምን ለመገንባት እና ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ተስፋ ለመስጠት ያላትን ቁርጠኝነት በመግለጽ፥ ብጹእነታቸው ከቫቲካን ዜና ጋዜጠኛ ማሲሚላኖ ሜኒቼቲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በርካታ ችግሮች ቢያጋጥሙም በቤንቲዩ ሀገረ ስብከት ላይ የደረሰው አንዱ እንደሆነ በመግለጽ፥ “ክልላችን 450,000 የሚያህሉ ካቶሊኮች እና 350,000 ፕሮቴስታንቶች የሚኖሩበት ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ባሕላዊ ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ናቸው” በማለት ከገለጹ በኋላ አክለውም “የእምነት ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ለሁሉም ሰው ተስፋ እንድናደርግ ተጠርተናል” በማለት አብራርተዋል።

የቤንቲዩ ሀገረ ስብከት 38,000 ካሬ ኪሎ ሜትር እንደሚሸፍን ያስረዱት ጳጳሱ፥ በሰባት አጥቢያዎች የተከፋፈለ እንደሆነ እና እያንዳንዳቸው በአከባቢው የሚገኙትን የክርስቲያን ማህበረሰቦችን ህልውና ለማስቀጠል ወሳኝ ሚና በሚጫወቱ ሃዋሪያዊ ሥራ ሰራተኞች እና ካቴኪስቶች እንደሚደገፉ በመግለጽ፥ ብጹእ አቡነ ካርላሳሬ “የክርስቲያኑ ማኅበረሰብ የጀርባ አጥንት” በማለት በገለጹት የምዕመናን መሪዎች ቁርጠኝነት ላይ በእጅጉ የሚተማመኑ ዘጠኝ የሀገረ ስብከት ካህናት እንዳሉ ገልጸዋል።

ቤንቲዩ በደቡብ ሱዳን ከሚገኙት በጣም ድሃ ክልሎች አንዱ ስትሆን፥ እ.አ.አ. በ 2013 እና 2020 ዓ.ም. መካከል ለዓመታት የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት አካባቢውን እንዳፈራረሰ እና በዚህም ምክንያት በርካታ ሰዎች እስከ ዛሬ ድረስ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ እንደሚኖሩ መረጃዎች ያሳያሉ።

1,130,000 የሚጠጉ በአከባቢው የሚኖሩ ሰዎች የሁለቱ ዋና ዋና ብሄረሰቦች ማለትም የኑዌር እና የዲንቃ ብሄረሰብ አባላት ሲሆኑ፥ ብጹእ አቡነ ካርላሳሬ ይሄንን አስመልክተው እንደተናገሩት “በእነዚህ ሁለት ቡድኖች መካከል ያለው ግንኙነት በእውነቱ ቀላል አይደለም” ካሉ በኋላ፥ በመሆኑም ሀገረ ስብከቱ ቅድሚያ የሚሰጠው በሁለቱ ህዝቦች መሃል ድልድይ መገንባት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በግጭት እና በአየር ንብረት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች
ብጹእ አቡነ ካርላሳሬ የቤንቲዩ ከተማ በደቡብ ሱዳን ውስጥ ትልቁ የተፈናቃዮች ካምፕ የሆነው የሩኮና ካምፕ መገኛ እንደሆነም ጭምር በመግለጽ፥ ይህ ካምፕ እ.አ.አ. በ 2014 ዓ.ም. የተመሰረተ ሲሆን፥ ካምፑ 140,000 ሰዎችን የያዘ እንደሆነ እና ከ 800,000 በላይ ደቡብ ሱዳናውያን መካከል ጥቂቱ ብቻ በግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለመፈናቀል እንደተገደዱ ገልጸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በዋናነት የኑባ ብሄረሰብ አባል የሆኑ ወደ 130,000 የሚጠጉ ሱዳናውያን ስደተኞች በቤንቲዩ ሃገረ ስብከት ሥር በሚገኙ በአይዳ እና ጃም ጃም ዙሪያ በሚገኙ ካምፖች ውስጥ ይኖራሉ ብለዋል።

“የሰላም ስምምነት ቢደረግም አሁንም ድረስ በርካታ ሰዎች ወደ ቤታቸው መመለስ አልቻሉም” ያሉት ብጹእነታቸው፥ ከዚህም በላይ ጉዳዩን እያባባሰ የሚገኘው ተለዋዋጭ እና ያልተጠበቀ የአየር ንብረት እንደሆነ እና በዚህም ምክንያት ከባድ ድርቅ እና ከፍተኛ ዝናብ የጣለባቸው ጊዜያት እንዳሉ ገልፀው፥ “ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ታይቷል፥ ይህም በየዓመቱ አንድ ሚሊዮን ሰዎችን ያፈናቅላል” ካሉ በኋላ፥ ይህም በመሆኑ የግብርናውን ዘርፍ እያዳከመ እንደሚገኝ እና የምግብ አቅርቦትም የበለጠ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።

ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች በውሃ እንደተጥለቀለቁ እና በርካታ እንስሳት በተበከለው ውሃ ምክንያት በበሽታ ማለቃቸውን ያነሱት ጳጳሱ፥ “ተጎጂዎች በአስከፊው ድህነት ምክንያት አዲስ ቤቶችን መፈለግ ስለነበረባቸው እና ወደ ሌላ ቦታ ሲዘዋወሩም በአካባቢው ነዋሪዎች ብዙ ጊዜ በጥላቻ አይን እንደሚታዩ ገልጸዋል።

በዩኒቲ ግዛት የነዳጅ ጉድጓዶች በወንዙ አቅራቢያ ስለሚገኙ እና ጎጂ ኬሚካሎች ወደ ውሃው ውስጥ ሊገቡ ስለሚችሉ እና በሚከሰተው ጎርፍ የውሃ ምንጮችንም ጭምር ሊበክሉ እንደሚችሉ በማስጠንቀቅ፥ ከዚህም በዘለለ በዚህ ችግር ምክንያት የማይቀረው የአፈር መሸርሸር እና የደን መጨፍጨፍ የግጭት ስጋትን በእጅጉ የሚጨምሩ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።

“የአየር ንብረት ለውጥ እና የአካባቢ መራቆት የደቡብ ሱዳንን ህዝብ ችግርን የመቋቋም አቅሙን እያዳከመ ለተለያዩ ችግሮች የበለጠ ተጋላጭ እያደረጋቸው ነው” ያሉት ብጹእ አቡነ ካርላሳሬ፥ ነገር ግን ደቡብ ሱዳን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተፈናቃይ ደቡብ ሱዳናውያንን ችግር ብቻ ሳይሆን እየተጋፈጠች ያለችው፥ ከድንበሯ ባሻገር ባለችው ሱዳን በተቀሰቀሰ ከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎቿ ከመኖሪያ ቀያቸው እየተፈናቀሉ እና ደህንነትን ለማግኘት በሚል ተስፋ ወደ ደቡብ ሱዳን እየተሰደዱ እንደሆነ ገልጸው፥ በዚህም ምክንያት ደቡብ ሱዳን በአሁኑ ጊዜ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የተፈናቀሉ ሱዳናውያንን እያስተናገደች እንደሆነ፥ ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ ሀገሪቱ ካለባት ችግር አንፃር እያንዳንዱ ተፈናቃይ የሚገባውን እርዳታ ማድረግ እንዳልቻለች ጠቁመዋል።

የአንድነት ጥሪ
የደቡብ ሱዳን ህዝብ የወደፊት እጣ ፈንታ አስተማማኝ እንዳልሆነ ያነሱት ብጹእ አቡነ ካርላሳሬ፥ ምንም እንኳን ፖለቲካ ጸጥታን እና መረጋጋትን ሊያመጣ እንደሚችል ቢታመንም፥ መጪውን የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ሁኔታ መተንበይ እንደሚያስቸግር እና ምርጫው በቅርቡ ለሁለተኛ ጊዜ መራዘሙን ጠቁመዋል። ብጹእነታቸው ሀገሪቱ ለምርጫ ያላት ዝግጁነት ላይ ያላቸውን ስጋት ገልጸው፥ መዘግየቶች በፖለቲካዊ ፍላጎት ላይ ጥያቄዎችን እንደሚያስነሱ አስታውሰዋል። 

ሲቪል ማህበረሰቡ እና መሪዎች ለምርጫው መዘጋጀታቸው ወሳኝ ነገር እንደሆነ ያስታወሱት ጳጳሱ፥ መራጮች እጩዎቻቸውን የሚመርጡት በጎሳ ላይ በመመስረት እና ለአንዳንድ ቡድኖች ብቻ በሚያስጠብቁት ጥቅም ብቻ ሳይሆን፥ ነገር ግን በእውነት ለመላው ሀገር እና የጋራ ጥቅም የሚሰሩ ፖለቲከኞችን እንዲመርጡ ግንዛቤን መፍጠር እና ህዝብን ማደራጀት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ 85 በመቶውን የሚይዘው የነዳጅ ዘይት ገቢ በአንድ ወቅት ለሃገሪቷ መረጋጋት መሰረት ሆኖ ይታይ ነበር፥ በአሁኑ ወቅት ግን ግጭትና መከፋፈል እንዲባባስ እያደረገ እንደሆነ ጠቅሰው፥ “ደቡብ ሱዳን በነዳጅ ሀብቷ ትለማለች ተብሎ ይጠበቅ ነበር፥ ከዚህ በተቃራኒ እነዚህ ገቢዎች ለአመፅ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛል” ብለዋል።

ጳጳሱ በቅርቡ በናስር ግዛት በመንግስት ሃይሎች እና በተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት በማስታወስ፥ ጉዳዩ አስቸኳይ ውይይት እንደሚያስፈልገው ጠቁመው፥ “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ያለው ግጭት በጣም አሳስቦናል፥ ውይይቱ በጣም አስቸጋሪ ስለሆነ ወደ አንድ የጋራ መግባባትና ከሁከት የራቁ መፍትሄዎችን ለማግኘት ያልቻልን ይመስላል” በማለት ደቡብ ሱዳንን ወደ ሰላም ጎዳና ለማምጣት የአንድነት ራዕይ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቤተክርስቲያን የተስፋ ተልዕኮ
ሃገሪቷ በእነዚህ ችግሮቹ መካከል ባለችበት በአሁኑ ወቅት ቤተክርስቲያኗ ከደቡብ ሱዳን ህዝብ ጎን መቆሟን ያረጋገጡት ብጹእ አቡነ ካልላሳሬ፥ በመጨረሻም “ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ የእርቅ ድልድዮችን መገንባት ነው” ካሉ በኋላ፥ አገሪቱ በፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ መፈናቀል እና የአካባቢ አደጋዎች እየተጋፈጠች ባለችበት ወቅት ቤተክርስቲያኒቱ በአንድነት፣ በፍትህ እና በዘላቂ ሰላም ጥሪዎች አማካኝነት ተስፋን እየዘራች መሆኗን ጠቁመዋል።
 

14 Mar 2025, 13:48