የመጋቢት 07/2017 ዓ.ም የሁለተኛው የዐብይ ጾም ሣምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
የእለቱ ንባባት
1. ኦ. ዘፍጥረት 15፡5-12.17-18
2. መዝሙር 26
3. ፊል. 3፡17-4፡1
4. ሉቃስ 9፡28-36
የእለቱ ቅዱስ ወንጌ
የኢየሱስ መልክ መለወጥ
ኢየሱስ ይህን ከተናገረ ከስምንት ቀን ያህል በኋላ ጴጥሮስን፣ ዮሐንስንና ያዕቆብን ይዞ ሊጸልይ ወደ አንድ ተራራ ወጣ። በመጸለይ ላይ እንዳለም የፊቱ መልክ ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ መብረቅ የሚያንጸባርቅ ነጭ ሆነ። እነሆ፤ ሁለት ሰዎች፣ እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ በክብርም ተገልጠው፣ በኢየሩሳሌም ይፈጸም ዘንድ ስላለው ከዚህ ዓለም ስለ መለየቱ ይናገሩ ነበር። ጴጥሮስና አብረውት የነበሩት ግን እንቅልፍ ተጭኖአቸው ነበር፤ ሲነቁ ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር የቆሙትን ሁለት ሰዎች አዩ። ሰዎቹም ከኢየሱስ ተለይተው ሲሄዱ፣ ጴጥሮስ፣ “ጌታ ሆይ፤ እዚህ ብንሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ ሦስት ዳስ እንሥራ፤ አንዱ ለአንተ፣ አንዱ ለሙሴ፣ አንዱም ለኤልያስ ይሆናል” አለው፤ የሚናገረውንም አያውቅም ነበር።ይህንም እየተናገረ ሳለ ደመና መጥቶ ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ፈሩ። ከደመናውም ውስጥ፣ “የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት” የሚል ድምፅ መጣ። ድምፁም በተሰማ ጊዜ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ፤ ደቀ መዛሙርቱም ነገሩን በልባቸው ያዙ እንጂ ስላዩት ነገር በዚያን ወቅት ለማንም አልተናገሩም። (ሉቃ. 9፡28-36)
የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ
በዚህ በሁለተኛው የዐብይ ጾም ሳምንት እሑድ ስርዓተ አምልኮ ላይ የተነበበልን ቅዱስ ወንጌል የኢየሱስን ተአምራዊ ለውጥ ይተርካል (ሉቃ. 9፡28-36)። ረጅም በሆነ ተራራ ላይ ሲጸልይ መልኩ ተለውጧል ልብሱም ደምቆና እንደመብረቅ የሚያንጸባርቅ ሆኖ ይታያል በክብሩም ብርሃን ሙሴና ኤልያስ ተገለጡ በኢየሩሳሌም ስለሚጠብቀው ፋሲካ ይኸውም ስለ ሕማማቱ፣ ሞትና ትንሣኤ ሲነጋገሩ ይታያል።ለዚህ አስደናቂ ክስተት ምስክሮች ከኢየሱስ ጋር ወደ ተራራ የወጡት ሐዋርያቱ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ናቸው። ከዚያ ልዩ ትዕይንት በፊት ዓይኖቻቸው በሚገባ ተከፍተው እንደ ነበረ አድርገን እናስባቸው። እናም በእርግጠኝነት እንደዚያ መሆን አለበት። ነገር ግን ወንጌላዊው ሉቃስ እንደሚለው “ጴጥሮስና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ተጫጭኗቸው ነበር” እናም በቅጽበት “ሲነቁ ግን ኢየሱስን እና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሰዎች ክብር ሁሉ አዩ” በማለት ይናገራል (ሉቃስ 9፡32)። የሦስቱ ደቀ መዛሙርት እንቅልፍ መጫጫን አለመስማማት ይመስላል። ነቅተው እንዲጠብቁ በጠየቃቸው የኢየሱስ ጸሎት ወቅት እነዚሁ ሐዋርያት በጌቴሴማኒ አንቀላፍተዋል (ማር. 14፡37-41)። በእንደዚህ ያሉ አስፈላጊ ጊዜያት ውስጥ ይህ እንቅልፍ መምጣቱ በጣም አስገራሚ ነው።
ነገር ግን፣ በጥንቃቄ ካነበብን፣ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስ እና ያዕቆብ ተአምራዊ ለውጥ ከመጀመሩ በፊት ማለትም ኢየሱስ በጸሎት ላይ እያለ እንቅልፍ እንደወሰዳቸው እንመለከታለን። በጌቴሴማኒም እንዲሁ ይሆናል። ይህ ለተወሰነ ጊዜ በዝምታ እና በትኩረት የቀጠለ ጸሎት ነው። መጀመሪያ ላይ እነሱም ድካም እስኪያሸንፋቸው ድረስ ይጸልዩ ነበር ብለን እናስብ ይሆናል።
ወንድሞች፣ እህቶች፣ ይህ በጊዜው ያልታሰበ እንቅልፍ ምን አልባትም አስፈላጊ እንደሆኑ በምናውቅባቸው ጊዜያት ከሚመጡት የራሳችን ብዙ ሰዎች ጋር ይመሳሰላል ወይ? ምናልባት ምሽት ላይ፣ መጸለይ በምንፈልግበት ጊዜ፣ ከተጠመድንበት ቀን በኋላ ከኢየሱስ ጋር የተወሰነ ጊዜ ለማሳለፍ ስንፈልግ የሚመጣ እንቅልፍ ይመስላችኋል? ወይም ከቤተሰብ ጋር ጥቂት ቃላትን ለመለዋወጥ ጊዜው ሲደርስ እና ጥንካሬ አይኖረንም። ውድ እድሎችን ላለማጣት የበለጠ ንቁ ፣ በትኩረት ፣ አሳታፊ መሆን እንፈልጋለን ፣ ግን አንችልም ፣ ወይም በሆነ መንገድ ግን በደካማ ሁኔታ እናስተዳድራለን።
በዚህ ረገድ የዐብይ ጾም ጠንካራ ጊዜ የሚሰጠን ዕድል ነው። እግዚአብሔር ከውስጣችን ከጭንቀት መንፈሱ ራሱን ሊገልጥ ከማይችለው እንቅልፍ ሊያነቃን የሚፈልግበት ወቅት ነው። ምክንያቱም - ይህን እናስብ - ልብን ነቅቶ እንዲጠብቅ ማደረግ በእኛ ላይ ብቻ የተመካ አይደለም፡ ጸጋ ነውና መለመን አለበት። ሦስቱ የወንጌል ደቀ መዛሙርት ይህንን ያሳያሉ፡- ጥሩ ነበሩ፣ ኢየሱስን ወደ ተራራው ተከትለውት ነበር ይሄዱት፣ ነገር ግን በራሳቸው ብርታት ነቅተው መጠበቅ አልቻሉም። ይህ በእኛ ላይም ይከሰታል። ነገር ግን፣ የኢየሱስ መልክ በተለወጠበት ወቅት በትክክል ከእንቅልፋቸው ነቅተው ተነሱ። እንደገና ያነቃቸው የኢየሱስ ብርሃን ነው ብለን እናስብ ይሆናል። እንደነሱ፣ እኛም ነገሮችን በተለየ መንገድ እንድንመለከት የሚያደርገን የእግዚአብሔር ብርሃን ያስፈልገናል፡ ይማርከናል፣ እንደገና ያነቃናል፣ ለመጸለይ ያለንን ፍላጎት እና ጥንካሬ ያግዛል፣ ራሳችንን ለመመልከት እና ለሌሎች ጊዜ ለመስጠት እንችል ዘንድ ይረዳናል። በእግዚአብሔር መንፈስ ብርታት የሰውነትን ድካም ማሸነፍ እንችላለን። ይህንንም ማሸነፍ ሲያቅተን መንፈስ ቅዱስን “ እርዳን፣ ና፣ ና፣ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ና ልንለው ይገባናል። እርዳኝ፡ ከኢየሱስ ጋር መገናኘት እፈልጋለሁ፣ በትኩረት መከታተል እፈልጋለሁ፣ ነቅቼ እንድጠብቅ እርዳኝ ልንል ይገባል። ከመጸለይ የሚከለክለንን ከዚህ እንቅልፍ እንዲያወጣን መንፈስ ቅዱስን እንለምነው።
በዚህ የዐብይ ጾም ጊዜ ከእያንዳንዱ ቀን ድካም በኋላ ራሳችንን በእግዚአብሔር ብርሃን ሳናስቀምጥ በክፍሉ ውስጥ ያለውን ብርሃን ባናጠፋው ይጠቅመናል። ከመተኛታችን በፊት ትንሽ ለመጸለይ ጊዜ መውሰድ ይኖርብናል። ጌታ እንዲያስገርመን እና ልባችንን እንዲያነቃቃ እድል እንስጠው። ይህንን ማድረግ የምንችለው ለምሳሌ ወንጌልን በመክፈት እና ራሳችንን በእግዚአብሔር ቃል እንድንደነቅ ማድረግ ስንችል ነው፣ ምክንያቱም ቅዱሳት መጻሕፍት አካሄዳችንን ያበራሉ እና ልብን ያሞቃሉ። ወይም የተሰቀለውን ኢየሱስን ተመልክተን ለእኛ የማይታክት እና ዘመናችንን የመለወጥ ኃይል ያለው፣ አዲስ ትርጉም፣ አዲስ፣ ያልተጠበቀ ብርሃን እንዲሰጠን እና ወደ ወሰን የለሽ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዲመራን ልንማጸነው ይገባል።
እግዚአብሔር የሰጠንን የጸጋ ጊዜ ለመቀበል ልባችንን እንድናነቃ ድንግል ማርያም ሁላችንን ትርዳን።
ምንጭ፦ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጋቢት 03/2014 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደርጉት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የተወሰደ ነው