ፈልግ

የክቡር አቡነ ተስፋስላሴ (ተስፋዬ) ታደሰ ቅብዓተ ጵጵስና በልደታ ለማሪያም ካቴድራል ተካሄደ የክቡር አቡነ ተስፋስላሴ (ተስፋዬ) ታደሰ ቅብዓተ ጵጵስና በልደታ ለማሪያም ካቴድራል ተካሄደ 

የክቡር አቡነ ተስፋስላሴ (ተስፋዬ) ታደሰ ቅብዓተ ጵጵስና በልደታ ለማሪያም ካቴድራል ተካሄደ

በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ረዳት ጳጳስ ተደርገው የተሾሙት ክቡር አቡነ ተስፋስላሴ ታደሰ ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ልደታ ለማሪያም ካቴድራል ውስጥ በብጹዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነኢየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን በተመራ መስዋዕተ ቅዳሴ ሢመተ ጵጵስናቸው ተፈፅሟል።

አዘጋጅ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. የኮንቦናዊያን የኢየሱስ ልብ ሚሲዮናዊያን ማሕበር ጠቅላይ የበላይ አለቃ የነበሩትን ክቡር አባ ተስፋዬ ታደሰ ገብረስላሴን የአዲስ አበባ (ኢትዮጵያ) አገረ ስብከት ምክትል ጳጳስ አድርገው መሾማቸው ይታወሳል።

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ አዲስ ከተሾሙት ዕጩ ጳጳሳት መካከል አንዱ የሆኑት ክቡር አባ ተስፋዬ ታደሰ ገብረስላሴ ስለተለያዩ ሃይማኖቶች በቂ የአካዳሚክ ዕውቀትን ያካበቱት እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፥ በዚህም ባካበቱት ልምድ እና የትምህርት ዝግጅት ቤተክርስቲያኒቷ በሃይማኖቶች መካከል ያለውን ግንኙነት እና የክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ተነሳሽነቶችን ለማሳደግ ለምታደርገው ጥረት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ረዳት ጳጳስ ተደርገው የተሰየሙት ክቡር አባ ተስፋዬ ከዚህም በተጨማሪ የቅድስት መንበር የግብጽ የመንበረ ክሊዮፓትሪስ ተወካይ ተደርገውም ተሹመዋል።

በመሪነት ሚና የረጅም ዓመት ልምድ ያካበቱት ተመራጩ ክቡር አባ ተስፋዬ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የማኅበረ ኮምቦኒ የበላይ አለቃ ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፥ በዚያም የጉባኤውን ዓለም አቀፋዊ የተልእኮ ጥረቶች ይቆጣጠሩ ነበር።

 ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በቅርቡ ከሾሟቸው አምስት ጳጳሳት መካከል ለሀዋሳ ሃገረስብከት የተመረጡት እጩ ጳጳስ በኢትዮጵያ ደረጃ ለሃገረ ስብከቱ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሾሙ ኢትዮጵያዊ ጳጳስ ሲሆኑ፥ ለነቀምት ሃገረ ስብከት የተመረጡት ደግሞ ከብጹእ አቡነ ፍቅረ ማሪያም ገመቹ ቀጥሎ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ ጳጳስ ያደርጋቸዋል። ይህ ወሳኝ ምዕራፍ ቤተክርስቲያን ለሃገር በቀል አመራር ያላትን ቁርጠኝነት እንደሚያጎላ እና ይህም በተለይ በፖሊሲ አወጣጥ እና አስተዳደር ላይ ያለውን ተጽእኖ እንደሚያጠናክር ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ጠንካራ ተደራሽነት እና መመሪያ የሚፈልግበት ወቅት በመሆኑ፥ በቤተክርስቲያኒቱ እየተስፋፋ የመጣው የሃገር በቀል የመሪነት ሚና ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ የተደረገ ነው ተብሏል።

ክቡር አባ ተስፋዬ ታደሰ ዘማኅበረ ኮምቦኒ መስከረም 12 ቀን 1962 ዓ.ም. (22/09/1969 እ.ኤ.አ.) በሐረር ከተማ የተወለዱ ሲሆን ከተወለዱ ከጥቂት ወራት በኋላ ወደ ቤተሰባቸው የመኖሪያ ከተማ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በአዲስ አበባ ከ 1ኛ እስከ 8ኛ በምስራቅና በነጻነት ብርሃን ትምህርት ቤቶች የተማሩ ሲሆን፣ ከ9ኛ ክፍል እሰከ 12ኛ በቦሌ አጠቃላይ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረዋል። በአዲስ አበባ የመድኃኔ ዓለም ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ወጣት ማኅበር አባል እያሉ፣ አስራ ሁለተኛ ክፍል ከጨረሱ በኋላ፣ በ1979 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው የኮምቦኒ ዘርዓ ክህነት በመግባት፣ በካፑቺን ፍራንሲስካውያን የፍልስፍናና የነገረ መለኰት ተቋም የፍልስፍና ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። ከዚያም በሃዋሳ ከተማ በማኅበረ ኮምቦኒ ተመክሮ አድርገው በሚያዝያ 23 ቀን 1983 ዓ.ም ከሌሎች ወንድሞች ጋር የመጀመሪያ መሃላቸውን አድርገዋል። በመቀጠልም ወደ ሮም ከተማ ለነገረ መለኮት ትምህርት ተልከው በግሪጎሪያን ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ ጥቅምት 22 ቀን 1987 ዓ.ም. በሮም ከተማ የመጨረሻ መሃላቸውን ካደረጉ በኋላ ታህሳስ 28 ቀን 1987 ዓ.ም. በሮም ከተማ ከረዳት ጳጳስ ክሌመንቴ ሪቫ እጅ ማዕረገ ድቁናን ተቀብለዋል።

ከዚያም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ከብፁዕ አባታችን ካርዲናል ጳውሎስ ጻድዋ እጅ ማዕረገ ክህነትን በቁምስናቸው በመድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ነሐሴ 20 ቀን 1987 ዓ.ም. ተቀብለዋል። ከሢመተ ክህነታቸው በኋላ ወደ ካይሮ ከዚያም ወደ ሮም ተልከው የጀመሩትን ትምህርትን ቀጥለዋል።

ክቡር አባ ተስፋዬ ወደ ሱዳን ተመድበው በካርቱም ከ 1990 -1993 ዓ.ም. ድረስ በሐዋርያዊ ስራ ያገለገሉ ሲሆን፥ ወደ ሮም ተመልሰው የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ለሁለት ዓመት ያህል በሃዋሳ ሀገረ ስብከት ባሉ ሁለት ቁምስናዎች በሃሮ ዋቶ ጕጂና በቱሎ ሲዳማ የሐዋርያዊ ሥራና የትምህርት ቤት አገልግሎት ሰጥተዋል። ከነዚህ አገልግሎቶች በኋላ ወደ ሮም ተልከው በሳሌዝያውያን ዩኒቨርሲቲ ስለ ዘርዓ ክህነት የሕንፀት አገልግሎት አጭር ኮርስ ወስደው ወደ ሃገር ቤት በመመለስ ጉለሌ በሚገኘው የማኅበረ ኮምቦኒ ዘርዓ ክህነት አገልግሎት ሰጥተዋል። ከዚህም በተጓዳኝ በጉለሌ ፍራንሲስካውያን የፍልስፍና የነገረ መለኰት ተቋም ሲያስተምሩ የነበረ ሲሆን፥ ከ 1994 - 1997 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ የማኅበረ ኮምቦኒ አለቃ አማካሪ ሆነው በማገልገል ከቆዩ በኋላ በ 1998 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የማኅበረ ኮምቦኒ አለቃ ሆነው እንዲያገለግሉ የተመረጡ ሲሆን፣ ከሦስት ዓመት አገልግሎት በኋላ እንደገና ተመርጠው ሁለተኛ ዙር እያገለገሉ ሳሉ በተጓዳኝ የኢትዮጵያ የካቶሊክ ገዳማዊ ማኅበራት አለቆች ጉባዔ ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል። አገልግሎታቸውን መስጠት በመቀጠል ሮም ላይ በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ጥቅምት 2008 ዓ.ም. የኮምቦኒ ማኅበር ጠቅላይ አለቃ ሆነው ተመርጠው ሰኔ 2014 በድጋሚ ጠቅላይ አለቃ ሆነው ተመርጠዋል። በሮም የማኅበራትና የገዳማት ጠቅላይ አለቆች ኅብረት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ለሶስት ዓመታት ያገለገሉት ክቡር አባ ተስፋዬ በሕብረቱ ስም በተለያዩ አገልግሎቶች የተሳተፉ ሲሆን ባለፉት ሶስት ዓመታት ስለ ሲኖዳዊ የቤተክርስቲያን ተልዕኮ የሲኖዶስ ልዑክ ሆነው ተሳትፈዋል።

በአጠቃላይ ክቡር አባ ተስፋዬ በሮም ከሚገኘው ጳጳሳዊ ግሪጎሪያን ዩኒቨርሲቲ በነገረ መለኮት ዘርፍ የሊሴንት ዲግሪ፣ በሮም ከሚገኘው ጳጳሳዊ የአረብ እና እስላማዊ ጥናት ተቋም የእስልምና ጥናት ዲፕሎማ ያገኙ ሲሆን፥ በካይሮ በሚገኘው ዳር ኮምቦኒ ለአረብኛ ጥናት ኢስላማዊ ትምህርታቸውን የቀጠሉ ሲሆን በሮማ ሳሌሲያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የምስረታ ኮርስ ወስደዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ሃገረ ስብከቶቿ ውስጥ ሁለቱንም የግዕዝ እና የላቲን ሥርዓቶችን የምታካሂድ ልዩ የሆነ ሥነ ስርዓትን የምታንፀባርቅ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ አራት የግዕዝ ሥርዓትን የሚከትሉ ሃገረስብከቶችን እና ዘጠኝ የላቲን ሥርዓትን የሚከተሉ ሃዋሪያዊ ሰበካዎችን እንደሚያጠቃልል፥ ይሄም የአገሪቱን መንፈሳዊ ስብጥር ያሳያል ተብሏል።

አዲሶቹ ሹመቶች ይህንን ድርብ ቅርስ የሚያንፀባርቁ ሲሆን፥ ሁለቱ ጳጳሳት የግዕዝ ሥርዓትን የሚከተሉ ሃገረስብከቶች ውስጥ ሲያገለግሉ፥ ሦስቱ ደግሞ የላቲን ሥርዓትን በሚከተሉ ሰበካዎችን ያገለግላሉ።

በእነዚህ አዳዲስ ሹመቶች ቤተክርስቲያኗ በኢትዮጵያ ሰላምን፣ አንድነትን እና መንፈሳዊ እድገትን የማጎልበት ተልእኮዋን እንደምታስፋፋ ተስፋ ተጥሎባታል።

በክቡር አባ ተስፋሥላሴ የጵጵስና መርሃ ግብር ላይ ብፁዕ አቡነ መንግስተአብ የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል የኡጋንዳ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የጉሉ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሊዮናርዶ የኮንጎ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የኪሳንጋሊ ሀገረስብከት ረዳት ጳጳስ፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ብፁዓን ጳጳሳት፣ የቅድስት መንበር ተወካይ፣ ከተለያዩ ሀገራት የተወከሉ የኮምቦኒ ልዑካን አለቆች፣ የሌሎች ሀይማኖት ተወካዮች፣ የመንግስት ተወካዮች፣ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች፣ በርካታ ካህናት፣ ገዳማውያን፣ ምዕመናን እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

 

 

03 Feb 2025, 15:11