ፈልግ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የመቁጠሪያው ጸሎት ሲጸልዩ - የማህደር ፎቶ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ የመቁጠሪያው ጸሎት ሲጸልዩ - የማህደር ፎቶ   (ANSA)

በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት በዓለም የተልዕኮ የመቁጠሪያ ጸሎት ቀን ላይ በጋራ ለመጸለይ እንደተሰባሰቡ ተነገረ

በመላው ዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ሳምንት ሲከበር በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት የዩናይትድ ስቴትስ ጳጳሳዊ ተልእኮ ማኅበራትን በመቀላቀል የዓለም የተልዕኮ የመቁጠሪያ ጸሎት እንዳቀረቡ ተነገረ።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በዩናይትድ ስቴትስ ሚድዌስት ዙሪያ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ጥር 8 ቀን 2017 ዓ.ም. በተከበረው የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ሳምንት በዓል ላይ በድህረ ገጽ አማካይነት ተሰባስበው የዓለም ተልዕኮ የመቁጠሪያ ጸሎትን ለመጸለይ ችለዋል።

ብሔራዊ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ሳምንት በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ዓመታዊ በዓል ሲሆን፥ በጥር የመጨረሻው እሁድ እንደሚጀምር እና ሳምንቱን ሙሉ እንደሚከበር ተገልጿል።

ከአራቱ ጳጳሳዊ የተልዕኮ ማኅበራት መካከል አንዱ በሆነው በሚስዮናውያን የልጅነት ማኅበር (MCA) የተዘጋጀው የጸሎት ተነሳሽነት ከ77 የካቶሊክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በ14 አህጉረ ስብከት የሚገኙ ተማሪዎችን አንድ ላይ አሰባስቧል።

በዝግጅቱ ላይ የተሳተፉት 14ቱ የአሜሪካ አህጉረ ስብከቶች የሚልዋውኪ ሀገረ ስብከት፣ የኮሎምበስ ሀገረ ስብከት፣ የዴስ ሞይን ሀገረ ስብከት፣ የፋርጎ ሀገረ ስብከት፣ የግራንድ ራፒድስ ሀገረ ስብከት፣ የጀፈርሰን ከተማ ሀገረ ስብከት፣ የጆሊየት ሀገረ ስብከት፣ የማዲሰን ሀገረ ስብከት፣ የማርኬቴ ሀገረ ስብከት፣ የፔዮሪያ ሀገረ ስብከት፣ የሳሊና ሀገረ ስብከት፣ የሲዎክስ ከተማ ሀገረ ስብከት፣ እና ስፕሪንግፊልድ ሀገረ ስብከት እንደሆኑ ተገልጿል።

በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙ የጳጳሳዊ ተልእኮ ማኅበራት የእምነት ማስፋፊያ ማኅበርን፣ የሚስዮናውያን የልጅነት ማኅበርን፣ የቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያ ማኅበርን፣ እና የተልዕኮ ኅብረትን ያካትታል። በዚህም መሰረት የሚስዮናውያን የልጅነት ማኅበር ፕሮግራም በመላው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና የሃይማኖት ትምህርት ፕሮግራሞችን ያገለግላል ተብሏል።

የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ሳምንት
ማክሰኞ ዕለት በድህረ ገጽ ቀጥታ ግንኙነት የተከበረው የዓለም የተልዕኮ የመቁጠሪያ ጸሎት መርሃ ግብር በዓለም ዙሪያ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናት መሰረታዊ ትምህርት የማግኘት እድል የሌላቸውን እኩዮቻቸው እውነታ እንዲያስቡ እና እንዲያሰላስሉ እድል ሰጥቷቸዋል ተብሏል።

የዓለም ተልዕኮ ቀን በእያንዳንዱ አስርት ዓመታት ውስጥ ሚስዮናውያን ወንጌልን ማካፈላቸውን የሚቀጥሉበት የተለያዩ የዓለም ክልሎችን የሚወክል ሲሆን፥ ለአፍሪካ ደኖች እና የሣር ሜዳዎች አረንጓዴ፣ ለፓስፊክ ደሴቶች እና ውቅያኖስ ሰማያዊ፣ የቅዱስ አባታችን መኖሪያ ለሆነችው አውሮፓ ነጭ፣ ሚስዮናውያንን ወደ አሜሪካ ላመጣው የእምነት እሳት ቀይ፣ እንዲሁም በምስራቅ ለምትወጣው እና እስያን ለምትወክለው የጧት ብርሃን ቢጫ ተምሳሌታዊ ቀለሞች እንደሆኑ ተብራርቷል።

እ.አ.አ. በ1951 ሊቀ ጳጳስ ሺን የእምነት ማስፋፋት ማኅበር ብሔራዊ ዳይሬክተር በነበሩበት ወቅት የዓለም የተልዕኮ የመቁጠሪያ ቀንን እንደመሰረቱ ዘገባዎች ያሳያሉ።

በጸሎት የሚተጉ እና በረከቶቻቸውን የሚቆጥሩ ህፃናት
የዩናይትድ ስቴትስ የጳጳሳዊ ተልእኮ ማህበራት ብሔራዊ ዳይሬክተር የሆኑት ሞንሲኞር ሮጀር ጄ. ላንድሪ “የካቶሊክ ትምህርት ቤቶች ሳምንትን ስናከብር ተማሪዎች በራሳቸው በረከቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በዓለም ዙሪያ ያሉ እኩዮቻቸው በትምህርት ቤት የመማር ዕድል አጥተው በሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች ላይ እንዲያሰላስሉ እድል ልንሰጣቸው እንፈልጋለን” ብለዋል።

ሞንሲኞር ሮጀር አክለውም “በዚህ የተስፋ ኢዮቤልዩ ወቅት፣ በሊቀ ጳጳስ ፉልተን አነሳሽነት፣ ልጆችን በአንድ ላይ ማሰባሰብ እና መጸለይ እንዲሁም በእስያ፣ በአፍሪካ፣ በኦሽንያ፣ በአውሮፓ እና በላቲን አሜሪካ የሚገኙ እኩዮቻቸው ስለሚያጋጥሟቸው የተለያዩ ተግዳሮቶች እንዲያውቁ እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማሪያምን አማላጅነት እንዲጸልዩ ግብዣ እናቀርባለን” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሚስዮናውያን የልጅነት ማኅበር ዳይሬክተር የሆኑት አሌክሳንድራ ሆልደን ማኅበሩ የተገነባው ‘ልጆች ልጆችን በመርዳት’ መርህ ላይ በመመስረት በጸሎትና በመደጋገፍ እርስ በርስ በሕይወታቸው ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ በማስተማር ላይ መሆኑን አስታውሰዋል።
 

31 Jan 2025, 15:28