ፍቅር በቤተሰ ውስጥ፥ “እምነትን ለሌሎች ስለ ማስተላለፍ”
ሕጻናትን ማሳደግ እምነትን በወጉ የማስተላለፍ ሂደትን ይጠይቃል። አሁን ያሉ የአኗኗር ስልቶች፣ የሥራ ጊዜያትና ብዙ ሰዎች በሕይወት ለመኖር ሲሉ የሚሯሯጡበት የዛሬው ዓለም ውስብስብነት ይህን ክንዋኔ አዳጋች ያደርጉታል። ሆኖም፣ ቤት የእምነትን ትርጉምና ውበት የምናደንቅበት፣ የምንጸልይበትና ጎረቤታችንን የምናገለግልበት ሥፍራ ሆኖ መቀጠል ይኖርበታል። ይህም የሚጀምረው በጥምቀት ሲሆን፣ ቅዱስ አጉስጢኖስ እንዳለው፣ እናቶች ልጆቻቸውን ለጥምቀት በማብቃት “በተቀደሰ ዳግማዊ ልደት ይተባበራሉ”። በአዲስ ሕይወት የማደግ ጉዞ የሚጀምረውም በዚህ ዐይነት ነው። እምነት በጥምቀት የምንቀበለው የእግዚአብሔር ስጦታ እንጂ የራሳችን የሥራ ውጤት አይደለም። ሆኖም እምነት እንዲያድግና እንዲዳብር እግዚአብሔር ወላጆችን በመሣሪያነት ይጠቀማል። ስለዚህ፣ “እናቶች ትናንሽ ልጆቻቸውን ለኢየሱስ ወይም ለእመቤታችን የአክብሮት ሰላምታ እንዲሰጡ ሲያስተምሩ ማየት ያስደስታል። በዚያም ውስጥ ትልቅ ፍቅር ይታይበታል። ያኔ የሕጻን ልብ የጸሎት ስፍራ ይሆናል”። እምነትን ማስተላለፍ ወላጆች ራሳቸው እግዚአብሔርን በሐቅ እንዲያምኑ፣ እርሱን እንዲሹና ለእርሱ ያላቸውን ፍላጎት እንዲገልጹ ይጠይቃል። ምክንያቱም “ሥራህን አንዱ ትውልድ ለሌላው ትውልድ የሚያስተጋባው፣ ብርቱ ሥራህንም የሚያውጀው” (መዝ. 145፡4) “ስለ አንተ ታማኝነት አባቶች ለልጆቻቸው የሚነግሩት” (ኢሳ. 38፡ 19) በዚህ መንገድ ብቻ ነው። ይህም ማለት እኛ ራሳችን በማንደርስበት በጥልቁ ልባቸው ውስጥ እንዲሠራ እግዚአብሔርን መለመን ያስፈልገናል። የሰናፍጭ ዘር ያነሰች ብትሆንም ትልቅ ዛፍ ትሆናለች (ማቴ. 13፡31)። ይህም በእኛ ሥራና በውጤቱ መካከል ያለውን አለመመጣጠን እንድናውቅ ያደርገናል። ስጦታው የራሳችን እንዳልሆነ፣ ነገር ግን፣ እንድንጠብቀው አደራ የተሰጠን መሆኑን እናውቃለን። ሆኖም፣ ፈጠራ የታከለበት ዝግጁነታችን ራሱ በእግዚአብሔር እቅድ እንድንተባበር የሚያስችለን ስጦታ ነው። በዚህ ምክንያት፣ “ጥንዶችና ወላጆች በትምህርተ ክርስቲያን ረገድ ንቁ ወኪሎች መሆናቸው በሚገባ ሊታወቅ ይገባል… የቤተሰብ ትምህርተ ክርስቲያን ወጣት ወላጆች የራሳቸው ቤተሰብ የወንጌል ሰባኪዎች የመሆን ተልእኮአቸውን እንዲገነዘቡ የሚረዳ ውጤታማ የማስተማሪያ ዘዴ ስለ ሆነ ትልቅ ጠቀሜታ አለው”።
የእምነት ትምህርት፣ ከእያንዳንዱ ሕጻን ሁኔታ ጋር የተጣጣመ መሆን አለበት፣ ምክንያቱም ያረጁ አስተሳሰቦችና የአሠራር ዘዴዎች ሁልጊዜ አይጠቅሙም። ሕጻናት ምልክቶችን፣ ድርጊቶችንና ታሪኮችን ይፈልጋሉ። ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ሥልጣንና ሕግጋትን በተለመከተ የሚያነሡአቸው ጉዳዮች ስላሏቸው፣ የራሳቸውን እምነት እንዲለማመዱና በውበታቸው ብቻ የሚማርኩ ምሥክርነቶችን እንዲሰጡ ማበረታታት መልካም ነው። የልጆቻቸውን እምነት ለማሳደግ የሚመኙ ወላጆች ለልጆቻቸው የእድገት ሁኔታ ትኩረት ይሰጣሉ፤ ምክንያቱም መንፈሳዊ ተሞክሮ በግድ የሚጫን ሳይሆን፣ በነጻ የሚሰጥ መሆኑን ያውቃሉ። ስለዚህ፣ ጸሎት ለወላጆቻቸው እውነትም አስፈላጊ ነገር እንደሆነ ልጆች በትክክል እንዲገነዘቡ ማድረግ ያስፈልጋል። በመሆኑም፣ የቤተሰብ ጸሎትና መንፈሳዊ ሥራዎች በክፍል ውስጥ ከሚሰጥ ትምህርተ ክርስቶስ ወይም ከስብከት የበለጠ ወንጌልን የመስበክ ኃይል አላቸው። እዚህ ላይ እንደ ቅድስት ሞኒካ ከክርስቶስ ለራቁ ልጆቻቸው ያለማkረጥ ለሚጸልዩ እናቶች ምሥጋናዬን ለመግለጽ እወዳለሁ።
መገለጫውንና እድገቱን ከማመቻቸት አኳያ እምነትን ለሕጻናት የማስተላለፍ ሥራ መላው ቤተሰብ በስብከተ ወንጌል ተልእኮው እንዲገፋበት እገዛ ያደርጋል። ይህ ሥራ የሚጀምረው ከቤተሰብ ክልል ውጭ ያሉትን ጨምሮ በአካባቢ ላሉት ሁሉ እምነትን በማስፋፋት ይሆናል። በወንጌል ተልእኮ በተሰማራ ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ልጆች ብዙውን ጊዜ ራሳቸው የወንጌል ልኡካን ይሆናሉ፤ ደስታ በሞላበትና ምቹ ቤተሰብ ውስጥ በማደጋቸው ምክንያት እምነታቸውን ወይም አስተሳሰባቸውን ሳይለቁ በዚህ መንገድ ከዓለም ጋር መገናኘትን ይማራሉ። ኢየሱስ ራሱ ከኃጢአተኞች ጋር እንደ በላና እንደ ጠጣ እናውቃለን (ማር. 2፡ 16፤ ማቴ. 11፡19)። ከሳምራዊት ጋር እንደ ተነጋገረ (ዮሐ. 4፡7-26)፣ በሌሊት ከኒቆዲሞስ ጋር እንደ ተገናኘ (ዮሐ. 3፡ 1-21)፣ አንዲት ሴትኛ አዳሪ እግሮቹን እንድትቀባ እንደ ፈቀደ (ሉቃ. 7፡ 36-50) እና በታመሙት ላይ እጆቹን ከመጫን ወደ ኋላ እንዳላለ (ማር. 1፡ 40-45፤ 7፡ 33) እናውቃለን። ሐዋርያቱም እንዲሁ አደረጉ፤ ሌሎችን አልናቁም፣ ከወገኖቻቸው ተለይተው የራሳቸውን ትንሽ ቡድን ወይም የምርጦች ቡድን አልመሠረቱም። ባለሥልጣናት ቢያሳድዱአቸውም፣ “በሕዝቡ ሁሉ ፊት” ሞገስ ነበራቸው (የሐዋ. 2፡47 ፤ 4፡ 21፣33፤ 5፡13)።
“ስለዚህ፣ ቤተሰብ ወንጌልን በገሃድ በመስበክ እንዲሁም ከድሆች ጋር መተባበርን፣ ለተለያዩ ሰዎች ልብን ክፍት ማድረግን፣ ተፈጥሮ መጠበቅን፣ እጅግ ድሃ የሆኑትን ጨምሮ ሌሎች ቤተሰቦችን በግብረ ገብና በቁሳቁስ መደገፍን፣ የጋራ ጥቅምን ለማሳደግ ዝግጁ መሆንንና ከቤተሰብ ጀምሮ ሥጋዊና መንፈሳዊ የምሕረት ሥራዎችን በመሥራት ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ ማኅበራዊ ተቋማትን እንዲለወጡ ማድረግን የመሳሰሉ ልዩ ልዩ የምስክርነት ዐይነቶች በመስጠት የሐዋርያዊ ተግባር ወኪል መሆኑን ያሳያል” (310)። ይህ ሁሉ በሚመራንና በሕይወት በሚያኖረን አብ ፍቅር ያለንን ጥልቅ ክርስቲያናዊ እምነት የሚገልጽ ነው። ይህ የአብ ፍቅር ራሱን ሙሉ በሙሉ አሳልፎ በሰጠው፣ አሁንም ጭምር በመካከላችን በሚኖረውና በማናቸውም ደረጃ የሚያጋጥመንን የሕይወት ማዕበል በጋራ እንድንkkም በሚያስችለን በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጸ ነው። በሁሉም ቤተሰቦች ውስጥ የምስራቹ ቃል በክፉም ሆነ በደግ ጊዜያት ማስተጋባትና የመንገድ መብራት ምንጭ መሆን ይኖርበታል። ሁላችንም በቤተሰብ ውስጥ ስላለን የሕይወት ተሞክሮ ተመስገን ማለት ይገባናል፡- “እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እናውቃለን፣ በፍቅሩም እናምናለን” (1 ዮሐ. 4፡ 16)። ቤተሰቦች በቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ እንክብካቤ በመታገዝ የቤት ውስጥ አብያተ ክርስቲያናትና በኅብረተሰብ ውስጥ የስብከተ ወንጌል እርሾ መሆን የሚችሉት በዚህ ተሞክሮ መሠረት ብቻ ነው።
ምንጭ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 287-290 ላይ የተወሰደ።
አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ