ፈልግ

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤  (Vatican Media)

ፍቅር በቤተስብ ውስጥ፤ ፍቅር ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም

መውደድ ጨዋና ለሌሎች አሳቢ መሆንም ነው። ፍቅር ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም ወይም ብልግና የለበትም፤ ጨካኝ አይደለም። ድርጊቶቹ፣ ቃላቱ እና እንቅስቃሴዎቹ ደስ የሚያሰኙ ናቸው፤ ሻካራ ወይም ግትር አይደሉም። ፍቅር ሌሎችን ማሰቃየትን አጥብቆ ይጠላል። ይሉኝታ አንድን ሰው “አእምሮውንና ስሜቶቹን ማዳበርን፣ እንዲሁም እንዴት መስማት፣ መናገርና አንዳንዴም ዝም ማለት እንዳለበት መማርን የሚጠይቅ የስሜትና አድልዎ የሌለበት ትምህርት ቤት ነው።” ክርስቲያን ሰው በፈቃደኝነት የሚቀበለው ወይም የሚተወው ነገር አይደለም። ፍቅር መሠረታዊ ነገር እንደ መሆኑ መጠን “ማንኛውም ሰው በዙሪያው ካሉት ጋር ተስማምቶ የመኖር ግዴታ አለበት።”  በየቀኑ “አንድ ሰው በሕይወታችን ውስጥ ቀድሞውኑ ሚና ቢኖረውም እንኳ፣ ወደ ሌላው ሰው ሕይወት ውስጥ መግባት፣ መተማመንንና መከባበርን የሚያድስ ስሜትን መቆጠብን ይጠይቃል። በእርግጥ የፍቅር ጥልቀቱ ሲጨምር የሌላውን ሰው ነጻነት የማክበርና ሌላው ሰው የልቡን በር እስኪከፍት ድረስ የመጠበቅ ችሎታ በይበልጥ ማዳበርን ይጠይቃል።”

ከሌሎች ጋር በሐቅ ለመገናኘት ዝግጁ ለመሆን “በጎ አስተሳሰብ” አስፈላጊ ነው። ይህም የራስን ችላ ብሎ የሌሎች ሰዎችን ድክመት ከመጠቆም አሉታዊ አስተሳሰብ ጋር አይጣጣምም። በጎ አስተሳሰብ ከራሳችን ውስንነቶች ባሻገር እንድንመለከትና ትዕግሥተኞችና ልዩነቶች ቢኖሩን እንኳ ከሌሎች ጋር እንድንተባበር ይረዳናል። በጎ አስተሳሰብ መስተጋብርን ይመሠርታል፤ ግንኙነቶችን ያዳብራል፤ አዳዲስ የውህደት መረቦችን ይዘረጋል፤ ጥብቅ ማኅበራዊ ትስስርን ይፈጥራል። በዚህ ዓይነት ይበልጥ እየጠነከረ ይሄዳል። ምክንያቱም የባለቤትነት ስሜት ሳይኖር ለሌሎች ያለንን ቁርጠኝነት መቀጠል አንችልም። የራሳችንን ምቾት ብቻ በመሻት ላይ የምናተኩር ከሆነ የጋራ ሕይወት የማይቻል ይሆናል። ጸረ ኅብረተሰብ አቅም ያላቸው ሰዎች ሌሎች ሰዎች ያሉት የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ለማርካት ነው ብለው ያስባሉ። በመሆኑም ለፍቅራዊ ጨዋነትና ለመገለጫዎቹ ክፍት ቦታ አይኖርም። የሚወዱ ሰዎች የሚያስደስት፣ የሚያጸና፣ የሚያጽናናና የሚያበረታታ ቃል መናገር ይችላሉ። “አይዞህ ልጄ! (ማቴ. 9፡2)። “እምነትሽ ታላቅ ነው” (ማቴ. 15፡ 28)። “ተነሺ ቁሚ” (ማር. 5፡ 41)። “በሰላም ሂጂ” (ሉቃ. 7፡ 50)። “አይዞአችሁ አትፍሩ!” (ማቴ. 14፡ 27) የሚሉ እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ራሱ የተናገራቸው ናቸው። እነዚህ ሰውን የሚያዋርዱ፣ የሚያሳዝኑ፣ የሚያስቆጡ ወይም የሚንቁ ቃላት አይደሉም። በቤተሰቦቻችን ውስጥ፣ እርስ በርስ ስንነጋገር፣ ጨዋ ኢየሱስን መምሰል መማር አለብን።

ፍቅር ለጋስ ነው

ደጋግመን እንደተናገርነው፥ ሌላ ሰውን ለመውደድ በቅድሚያ ራሳችንን መውደድ ይኖርብናል። ይሁን እንጂ በጳውሎስ የፍቅር መዝሙር ላይ ፍቅር “የራስን ጥቅም ብቻ አይሻም” ፣ “የራሱንም አይፈልግም” ይላል። ይኸው ሐሳብ በሌላ ጽሑፍ ላይ “እያንዳንዳችሁ ሌሎችንም የሚጠቅመውንም እንጂ ራሳችሁን የሚጠቅመውን ብቻ አትመልከቱ” (ፊልጵ. 2፡ 4) ተብሎ ተገልጾአል። ሌሎችን በልግስና ማገልገል ራሳችንን ከመውደድ እንደሚበልጥ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ያደርግልናል። ራሳችንን መውደድ አስፈላጊ የሚሆነው ሌሎችን ለመውደድ ሥነ ልቦናዊ መነሻ ሲሆን ነው። “ሰውነቱን የሚነፍግ ሰው ለማን ይለግስ ዘንድ አለው? ሰውነቱን ከሚነፍግ ሰው የሚከፋ የለም” (ሲራክ 14፡5-6)።

ቅዱስ ቶማስ አኳይናስ፥ “ከመወደድ መውደድ ተገቢ ነው”፣ በእርግጥ “ከሁሉ አስበልጠው የሚወዱ እናቶች፣ ከመወደድ በላይ ለመውደድ ይሻሉ” ይላል። ስለ ሆነም፣ ፍቅር ከፍትሕ ጥያቄ የላቀና ከዚያም የዘለለ “መልሶ ለመቀበል ተስፋ የማያደርግ ነው” (ሉቃ. 6፡ 35)። ከሁሉ የሚበልጠው ፍቅር ደግሞ “የራስን ሕይወት ለሌላ አሳልፎ እስከ መስጠት የሚያደርስ ነው (ንጽ. ዮሐ. 15፡ 13)። ለመሆኑ፣ በነጻነትና በሙላት ራሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ የሚያደርግ ይህን የመሰለ ቸርነት የሚቻል ነገር ነው? አዎን፣ ምክንያቱም ወንጌል “በነጻ የተቀበላችሁትን በነጻ ስጡ” (ማቴ. 10፡8) ይላልና።  

ፍቅር አይበሳጭም ወይም ቅር አይሰኝም

የጳውሎስ የመጀመሪያው የፍቅር መዝሙር ስለ ሌሎች ሰዎች ድክመትና ጥፋት ፈጥኖ በማመናጨቅ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ትዕግሥት እንደሚያስፈልግ ይናገራል። ቀጥሎ የተናገረው ቃል ደግሞ በውጫዊ ምክንያት የሚመጣውን ውስጣዊ ንዴት የሚመለከት ነው። ሌሎች ሰዎችን በተመለከተ ችግር ወይም ሥጋት ፈጣሪ ስለሆኑ ከእነርሱ መራቅ ይገባል የምንለውንና በውስጣችን ያለውን ኃይለኛ ስሜትና ሥውር ቁጣ የሚመለከት ነው። ይህን የመሰለ ውስጣዊ ጥላቻ ማሳደር ለማንም አይበጅም። መቀያየምንና መገለልን ብቻ ነው የሚፈጥረው። ንዴት ጤናማ የሚሆነው ለትልቅ በደል ምላሽ መስጠት ሲያስፈልግ ብቻ ነው። ለሌሎች ሰዎች ወዳለን አመለካከት ሰርጾ ሲገባ ግን ጎጂ ነው።

ወንጌል በዓይናችን ውስጥ ያለውን ግንድ እንድንመለከት ይነግረናል (ንጽ. ማቴ. 7፡5)። ክርስቲያኖች ለቁጣ ትኩረት እንዳይሰጡ የሚናገረውንና “በክፉ አትሸነፍ (ሮሜ. 12፡ 21) የሚለውን የእግዚአብሔርን ብርቱ ተግሳጽ ችላ ማለት የለባቸውም። “በጎ ነገር ከማድረግ አንታክት” (ገላ. 6፡ 9)። ድንገት ቱግ የሚል የጥላቻ ስሜት ማሳደር አንድ ነገር ሲሆን፣ በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰድ ማድረግ ግን ሌላ ነው፤ “ተቆጡ፣ ነገር ግን ኃጢአት አትሥሩ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ” (ኤፌ. 4፡ 26)። እንዲያውም የእኔ ምክር በቤተሰብ ውስጥ ዕርቅ ሳታወርዱ አንድ ቀን እንኳ ከቶ አታሳልፉ የሚል ነው። “ዕርቅ እንዴት ማውረድ እችላለሁ? በጉልበቴ ተንበርክኬ ነውን? አይደለም! ትንሽ እንቅስቃሴ በማሳየት፣ አንድ የተለየ ትንሽ ነገር በማድረግ፣ በቤተሰብ ውስጥ ስምምነትን ማደስ ይቻላል። ከትንሽ ማሻሸት ውጭ ሌላ ቃላት ላያስፈልጉ ይችላሉ። ነገር ግን በቤተሰባችሁ ውስጥ ሰላም ሳይወርድ አንድም ቀን አታሳልፉ።” ስንናደድ የመጀመሪያው ምላሻችን ልባዊ ቡራኬ፣ ያንን ሰው እንዲባርከው፣ ነጻ እንዲያወጣውና እንዲፈውሰው እግዚአብሔርን መለመን መሆን አለበት። “በዚህ ፈንታ ባርኩ፣ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው” (1 ጴጥ. 3፡ 9)። ክፋትን መዋጋት ካለብን እንዋጋ፤ ነገር ግን ለቤት ውስጥ ብጥብጥ “እምቢ” እንበል።

ምንጭ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 99-103 ላይ የተወሰደ።

አዘጋጅ እና አቅራቢ ባራና በርግኔ

18 November 2023, 17:36