ፈልግ

አዲሱ የዓለም አቀፍ ወጣቶች ፌስቲቫል ዜማ የአውሮፓ ቱር ሽፋን ገጽ አዲሱ የዓለም አቀፍ ወጣቶች ፌስቲቫል ዜማ የአውሮፓ ቱር ሽፋን ገጽ  

ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል፥ “እንደ ማርያም በፍጥነት ተነስተን እንሂድ!”

ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ከሐምሌ 25-30/2015 ዓ. ም. በድምቀት እንደሚከበር ተገልጿል። ለፌስቲቫሉ ድምቀት ለመስጠት የተቋቋመው “ጄን ቨርዴ” የተሰኘ የዓለም አቀፍ አርቲስቶች ቡድን፥ “በተልዕኮ ላይ የምትገኝ ወጣት” በሚል ርዕሥ የዜማ ድርሰቱን ያዘጋጀ ሲሆን፣ ዋና ጭብጡ፥ “የወዳጅነት ዓለም ለመገንባት ሁሉም በጋራ መሥራት ይኖርበታል” የሚል እንደሆነ ታውቋል። ባለፉት ዓመታት ከዓለም ዙሪያ ከመጡ ወጣቶች ጋር በመገናኘት ያካበቱትን ልምድ የገለጹት ሁለት የቡድኑ አባላት፥ "ባለፉት ዓመታት እንደተደረገው ሁሉ ዛሬም ወጣቶች ለሕይወት የሚጠቅሙ መልካም ምክረ ሃሳቦችን ማግኘት ይፈልጋሉ" ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የሚሆን የዜማ ድርሰት እንዲቀርብ ተደጋጋሚ ጥያቄ እንደሚቀርብ የተናገረው እና አሥራ ዘጠኝ አባላት የሚገኙበት የ “ጄን ቨርዴ” ዓለም አቀፍ አርቲስቶች ቡድን፥ ከጣሊያን ፍሎረንስ ከተማ ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቆ በሚገኝ ሎፒያኖ ውስጥ በሚገኝ የፎኮላሬ እንቅስቃሴ  መንፈሳዊነት በመማረክ የዜማውን ድርሰት ለመጻፍ ማለሙን እና ጊዜውም አሁን መሆኑን አስረድቷል። በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ሊከበር የታቀደው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን መሪ ጭብጥም፣ በሉቃ. 1፡39 ላይ እንደተጠቀሰው፥ “ማርያም ኤልሳቤጥን ልትጎበኛት ፈጥና ተነሥታ ሄደች” የሚል ሲሆን፣ የአርቲስቶቹ ቡድንም ለበዓሉ የሚያዘጋጀው ዜማ ይህን መሠረት ያደረገ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዓለም ዙሪያ ከሚመጡ ወጣቶች ጋር ለመገናኘት የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉዞን የሚገልጽ እንደሆነ ታውቋል።

“ጄን ቨርዴ” የተሰኘ የዓለም አቀፍ አርቲስቶች ቡድን፥
“ጄን ቨርዴ” የተሰኘ የዓለም አቀፍ አርቲስቶች ቡድን፥

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለወጣቶች ያቀረቡት ግብዣ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሃንጋሪ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ለወጣቶች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ብርታትን እንደሚሰጣቸው ተናግረው፣ ወጣቶች ከሌሎች ወጣቶች ጋር መተባበር አስፈላጊ እንደሆነ እና ሕይወትን በኅብረት በመጓዝ የጋራ ልምድን ማካበት እንደሚገባ በማሳሰብ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ሊከበር የተቃረበውን ጨምሮ በየጊዜው የሚከበሩ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫሎችም ይህን ሃቅ እንደሚገልጹ አስረድተዋል። 

“ጄን ቨርዴ” የተሰኘ የዓለም አቀፍ አርቲስቶች ቡድን፥
“ጄን ቨርዴ” የተሰኘ የዓለም አቀፍ አርቲስቶች ቡድን፥

“በተልዕኮ ላይ የምትገኝ ወጣት” በሚል ርዕሥ የተቀነባበረውን ነጠላ ዜማ አቀንቃኝ ወጣት አድሪያና ማርቲንስ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ፥ በሊዝበት በሚከበረው የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለሚገኙ ወጣት ሴቶች እና ወንዶች የማበረታቻ መልዕክቷን ማስተላለፍ እንደምትፈል ገልጻለች። ከዚህ በፊት ይፋ ባደረገችው የቪዲዮ ክሊፗ ከልዩ ልዩ ወጣቶች ጋር በኅብረት መሥራቷን አስታውሳ፣ ከሌሎች ጋር አብሮ መሥራት ሁልጊዜ የሚያሳድግ መሆኑን አስረድታለች።

ዘንድሮ ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የተዘጋጀው ዜማ፣ “ማርያም ፈጥና ተነሥታ ሄደች” የሚለውን የበዓሉን ጭብጥ መሠረት ያደረገ መሆኑን የገለጸችው አድሪያና፣ ከሁሉም በላይ ማርያም ሴት መሆኗ፣ ችግሮችን እና መሰናክሎችን ለማሸነፍ የሚያስችል ጥንካሬ እና ተልዕኮ የተላበሰች፣ ኢየሱስ ክርስቶስንም በውስጧ የያዘች ወጣት እንደነበር አስታውሳለች። ለወጣቶች ፌስቲቫል ተብሎ የተዘጋጀው ዜማ ብዙ ደስታን እና ጥንካሬን የሚያጎናጽፍ እንዲሆን መፈለጓን አድሪያና ገልጻ፥ ድርሰቱም ከማርያም ጋር ውይይት የተደረገበት እና በጉዟችን እርሷ እንድትረዳን የልመና ጸሎት የቀረበበት እንደሆነ ገልጻለች።

“ጄን ቨርዴ” የተሰኘ የአርቲስቶች ቡድን የሙዚቃ ኮንሰርቱን ሲያቀርብ
“ጄን ቨርዴ” የተሰኘ የአርቲስቶች ቡድን የሙዚቃ ኮንሰርቱን ሲያቀርብ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙውን ጊዜ ለወጣቶች ብርታትን መስጠት እንደሚፈልጉ፣ በተለይም ከዚያ አስፈሪ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጊዜ በኋላ በልዩ አጋጣሚ ከቅዱስነታቸው ጋር ለመገናኘት እንደምትፈልግ ገልጻለች። ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ለወጣቶች በሙሉ ታላቅ ደስታን የሚፈጥር፣ በዓሉን ከሌሎች ወጣቶች ጋር በኅብረት ለማክበር ዕድል በማግኘቷ የተሰማትን ደስታ ገልጻ፣ የበዓሉን ዜማ በጋራ ለመዘመር ከፍተኛ ጉጉት እንዳደረባት እና ወጣቶችም በዜማው እንዲሳተፋ ለማድረግ በተቻለ መጠን ሙከራ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ አስረድታለች።

ዜማው በሁለት ቋንቋዎች ተዘጋጅቷል

ዜማው በሁለት ቋንቋዎች እነርሱም በእንግሊዝኛ እና በፖርቱጋል ቋንቋዎች መዘጋጀቱን የተናገረችው ወጣት አድሪያና፥ እንግሊዘኛ ቋንቋ ሁሉም ሰው ሊረዳው የሚችለው በመሆኑ እና የፖርቱጋል ቋንቋ ዓለም አቀፍ ፌስቲቫሉ የሚከበርበት አገር ቋንቋ እንደሆነ አስረድታ፥ ጣሊያን ውስጥ ዜማውን ለመዘመር ዕድል ባገኙበት ወቅት በርካታ ወጣቶች በታላቅ ደስታ ምላሽ መስጠታቸውን ገልጻለች።  

እያንዳንዱ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል አከባበር እንደየአገሩ እንደሚለያይ የገለጸችው አድሪያና፥ በላቲን አሜሪካ አገር ፓናማ ውስጥ የደቡብ አሜሪካ አገራት ወጣቶችን ማግኘት ጥሩ ልምድ እንደ ነበር ተናግራ፣ ነገር ግን በማንኛውም ሁኔታ ዋናው ነጥብ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር የሚደረግ ስብሰባ መሆኑን አስረድታለች። ተመሳሳይ ስሜት ያደረባቸው በርካታ ወጣቶች በአንድ ሃሳብ ዙሪያ ሲሰበሰቡ መመልከት ደስታን እንደሚሰጥ ገልጻ፣ በፓናማ የተከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ልዩ ትዝታን ጥሎ ያለፈ ድንቅ በዓል እንደ ነበር አስታውሳለች።

“ማርያም ፈጥና ተነሥታ ሄደች” የሚለውን የበዓሉን ዋና ጭብጥ ያስታወሱት ዓለም አቀፍ የአርቲስቶች ቡድኑ በዜማው አማካይነት ማስተላለፍ የፈለገውን መልዕክት ሲገልጽ፥ ወጣቶች ተባብረው በድፍረት ወደ ፊት መጓዝ እንዳለባቸው እና ማርያም ተነስታ በፍጥነት እንድትሄድ ያነሳሳት በውስጧ የነበረው ታላቅ ኃይል እንደሆነ ገልጾ፥ “አስፈላጊ የሆነውን ነገር ለዓለም ለማቅረብ ጊዜን ማባከን የለብንም” የሚል ብዙ የፍቅር፣ የሰላም እና የተስፋ መልዕክት ያለው መሆኑን ቡድኑ ገልጿል።

አብሮ የመሆን ፍላጎት

“ከብዙ አገሮች ወጣቶች እና ማኅበረሰቦች ጋር አብሮ መሆን ጉልበትን ከሚሰጡ ነገሮች አንዱ ነው” ያለችው የአርቲስቶች ቡድን አባል አሌሳንድራ ፓስኳሊ፥ በ “ጄን ቨርዴ” የአርቲስቶች ቡድን እና በወጣቶች መካከል ያለውን ልዩ ግንኙነት በቃለ-መጠይቋ ስትገልጽ፥ “በሁሉም አገሮች ዘንድ ያስተዋለችው አንድ የጋራ ነገር በአንድነት የመሰብሰብ ፍላጎት ነው” በማለት ተናግራለች። አሌሳንድራ ከሌሎች የቡድኑ አባላት ጋር በነበራት ቆይታ ያስታዋለቸው ነገር ቢኖር፥ ኮንሰርቶችን እና የጥበብ አውዶችን በኅብረት በሠራችባቸው ጊዜያት ሁሉ የወንድማማችነት መንፈስ እንደነበር ማስተዋሏን ገልጻለች። ከምንም በላይ በፖላንድ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ወላጆቻቸውን ያላዩ ወጣቶችን ማግኘቷን የገለጸችው አሌሳንድራ፥ እነዚያ አንድ ላይ የነበሩባቸው ቀናት የተለየ አየር የተነፈሱበት ዕለት እንደ ነበር ገልጻለች።

ለአርቲስቶች የተዘጋጀውን አውደ ጥናት የተካፈሉ ወጣቶች
ለአርቲስቶች የተዘጋጀውን አውደ ጥናት የተካፈሉ ወጣቶች

ከአዋቂዎች ብንጀምር፥ ወጣቶች የአዋቂዎችን ትክክለኝነት፣ ማዳመጥን እና የሚናገሩትን እንደሚያደርጉ ማየት እንደሚፈልጉ፥ እንዲሁም ከሌሎች የሚያቀርቡ ሃሳቦችን የሚገነዘቡ መሆናቸውን ማየት እንደሚፈልጉ አሌሳንድራ ተናግራ፥ ከሁሉም በላይ በአዋቂዎች እና በወጣቶች መካከል ያለውን ርቀት መቀነስ እንደሚገባ ተናግራለች። ወጣቶች ወደ ጎልማሶች እንዲቀርቡ ከመጠበቅ ይልቅ ጎልማሶች ወደ ወጣቶች በመቅረብ፥ ወደሚገኙበት ሥፍራ በመሄድ ችግር ውስጥ በሚወድቁባቸው ጊዜያት እና ቦታዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ማድረግ እንደሚገባ አሳስባለች።

የአውደ ጥናቱ ተካፋዮች በአውሮፓ ዙር ወቅት ያቀረቡት ዝግጅት
የአውደ ጥናቱ ተካፋዮች በአውሮፓ ዙር ወቅት ያቀረቡት ዝግጅት

ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ጥንካሬ የሚገኝበት ልምድ እንደሆነ አሌሳንድራ ገልጻ፥ በዓሉን ለመካፈል ወደ ቦታው የሚሄዱ ወጣቶች ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት እንደሚሄዱ፣ ምናልባት ገና እግዚአብሔርን ለማወቅ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙትም ወደ በዓሉን እንደሚሄዱ አስረድታለች። አንዳንዶችም በፌስቲቫሉ ላይ ለመገኘት ካላቸው ጉጉት ብቻ ቢሄዱም ዋናው ነገር ጥንካሬ የሚያገኙበት ክስተት ስለሆነ ማኅበረሰቡ እነዚህን ወጣቶች መቀበል እንደሚገባ አሳስባለች። “ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ወጣቶች ከወጣቶች ጋር በአንድነት የሚሆኑበት አጋጣሚ በመሆኑ ብቸኝነት እንደማይሰማቸው እና በዓለም ላይ ተመሳሳይ ነገርን የምንፈልግ ብዙዎቻችን ከበዓሉ ሥፍራ የሚገኘውን የጸጋ ሃብት ተቀብለን ወደ አካባቢያችን በማምጣት ከሌሎች አማኞች ጋር መካፈል ይገባል” ብላ “አንድ ሰው ብቻውን የትም ስለማይደርስ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ታላቅ መልዕክትም ይህ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት አሌሳንድራ በቃለ ምልልሷን ተናግራለች።

05 June 2023, 17:58