ፈልግ

የአካል ጉዳተኝነት የአካል ጉዳተኝነት  (©saelim - stock.adobe.com)

ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፥ “በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ማንም ሊገለል እና ሊዘነጋ አይገባም!” አሉ

የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፣ የአካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ በተካሄደው ሁለተኛ ብሔራዊ ጉባኤ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ ዓርብ ግንቦት 25/2015 ዓ. ም. በሮም በተካሄደው እና በጣሊያን መንግሥት የአካል ጉዳተኞች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ አሌሳንድራ ሎካቴሊ በተገኙበት የውይይት መድረክ ላይ ባሰሙት ንግግር፥ በማኅበረዊ ሕይወት ውስጥ ማንም ወደ ጎን ሊባል እንደማይገባ አሳስበዋል። የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ለአካል ጉዳተኞች እያበረከተ የሚገኘውን ሐዋርያዊ አገልግሎት መሠረት በማድረግ ባሰሙት ንግግር፥ "ቤተ ክርስቲያን እና የሕዝብ ተቋማት፥ ለብዙሃነት ትኩረትን በመስጠት የተረጋጋ ማኅበራዊ ሕይወት ለመምራት የሚያስችል እቅድ ለማውጣት በኅብረት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“‘እኛ’ ከሚለው አስተሳሰብ መጀመር ያስፈልጋል” ያሉት ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፣ ቤተ ክርስቲያን እና ሕዝባዊ ተቋማት በዚህ ሃሳብ ላይ በመስማማት፥ የአካል ጉዳተኞች በሁሉም የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ እንዲካተቱ እና ሙሉ በሙሉ ወደ ማኅበረሰቡ እንዲገቡ የሚያስችል የሕይወት ዕቅድ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ በዚህም ቤተ ክርስቲያን እና መንግሥት መተባበር እንደሚገባ፥ የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ ለውይይት በተዘጋጀው መድረክ ላይ ገልጸዋል። በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት፣ በጣሊያን የአካል ጉዳተኞች ሐዋርያዊ አገልግሎት ኃላፊ እህት ቬሮኒካ ዶናቴሎ፣ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ባቀረቡት ሃሳብ፥ "ሁሉም የአካል ጉዳተኞች የተወለዱት እና ከተወለዱ በኋላም ለጉዳት የበቁት በበሽታ ወይም በአደጋ ምክንያት" በመሆኑ በቂ ሕክምና እና ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል” ብለዋል። 

በውይይት መድረኩ ላይ ከጣሊያን ልዩ ልዩ ሀገረ ስብከቶች የምዕመናን ማኅበራት እና እንቅስቃሴዎች የተውጣጡ 300 ልኡካን ተገኝተዋል። ከእነዚህም በተጨማሪ 6 የውጭ አገራት ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፥ የውይይት መድረኩን የመሩት የቫቲካን የመገናኛ ብዙኃን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አሌሳንድሮ ጂሶቲ ሲሆኑ፥ አቶ አሌሳንድሮ ውይይቱን በመሩበት ወቅት፤ ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ እና በጣሊያን መንግሥት የአካል ጉዳተኞች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ አሌሳንድራ ሎካቴሊ ውይይቱ ላይ ባቀረቡት አስተያየት፥ "በአካል ጉዳተኞች እና በተቀረው የማኅበረሰብ ክፍል መካከል ያለውን ልዩነት በማሸነፍ፣ የአካል ጉዳተኞችን በማኅበረሰቡ ውስጥ የማካተት ባሕል የአዲሱ የመሰባሰብ እና የመገናኘት ምልክት እንደሆነ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ሁላችንም በአንድ ጀልባ ላይ የተሳፈርን በመሆናችን፣ በዚህ ጉዞ መካከል ማንም ሰው ራሱን ብቻ ሊያድን አይችልም” ማለታቸውን አስታውሰዋል። 

በኅብረት መሆን የሁሉም ሰው ሃላፊነት ነው!

“ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በኅብረት መሆን ማለት ለአካል ጉዳተኞችም ጭምር ትኩረትን መስጠት እና መንከባከብ ማለት ነው” ያሉት ሚኒስትር ወ/ሮ አሌሳንድራ ሎካቴሊ፥ "ቤተ ክርስቲያን እና ተቋማት፥ ለብዙሃነት ትኩረትን በመስጠት የተረጋጋ ማኅበራዊ ሕይወት ለመምራት የሚያስችል እቅድ ለማውጣት ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበው፥ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም ሰው ኃላፊነትን ተቀብሎ በጋራ መረባረብ ይገባል” ብለዋል።  “ማኅበራዊ ሕይወትን ለመምራት የሚያስችል እቅድ ጊዜያዊ ብቻ መሆን የለበትም” ያሉት የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፥ እቅዱ እርግጠኛነትን እና ከለላን የሚሰጥ እንዲሁም ልዩነትን ከግምት ውስጥ በማስገባት፥ ሁሉም ሰው የሚፈልገውን እንዲያገኝ ለማድረግ በጋራ ማሰብ እንደሚገባ እና የአካል ጉዳተኛውን ወደ ማኅበረሰቡ ውስጥ የሚያስገባ መሆን አለበት” ብለዋል። “ማኅበራዊ ደህንነትን እና የግል ፍላጎቶችን የሚያሟሉ እቅዶችን ማውጣት እና የአካል ጉዳተኞችን የተለያዩ ችግሮች ሊቀርፉ የሚችሉ አገልግሎቶችን መደገፍ ያስፈልጋል” የሚለው ሃሳብ በሁሉም ሰው ላይ ትልቅ ሃላፊነት መኖሩን ያሳያል ያሉት ሚኒስትር ወ/ሮ አሌሳንድራ ሎካቴሊ፣ “ኅብረተሰቡን ሊያዋህድ የሚችል የአብሮነት አስተሳሰብን ማስረጽ እና እንቅፋቶችን የማስወገድ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል” ብለዋል።

ሁሉን አቀፍ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ቤተ ክርስቲያን እና ተቋማት መተባበር አለባቸው

“የአካል ጉዳተኞች ሁል ጊዜ አቅመ ደካሞች ስላልሆኑ በቁምስናዎች እና በሀገረ ስብከቶች ውስጥ አቅማቸውን የሚጨምሩ ልምዶችን ማስተዋወቅ ይቻላል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፣ ወደ ፊት ብዙ የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸው፣ ኅብረት እና አንድነት ቤተ ክርስቲያን በተግባር እንድትገልጸው የተጠራችበት መንገድ እንጂ አማራጭ አይደለም” ብለዋል። ብጹዕነታቸው በማከልም ኅብረት እና አንድነት ማለት ቤተሰባዊነት እና ወንድማማችነት ማለት እንደሆነ በመግለጽ፣ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ማንም ሊዘነጋ እና ሊገለል እንደማይገባ አስረድተዋል። በመሆኑም ከሁሉ አስቀድሞ ለሥራ በርትተን መነሳት እና መረዳዳት ይገባል" ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፣ በዓለም ውስጥ ሰዎች የአካል ጉዳተኞችን እንዲቀርቡ ካደረጉት መልካም ተሞክሮዎች መካከል አንዱ ከቤተሰብ ጋር የተደረገ የቅዱስ ሲኖዶስ አካል የሆነው የቤተሰብ ጉባኤ እንደ ነበር አስታውሰዋል።

ሚኒስትር አሌሳንድራ ሎካቴሊ በመጨረሻም፣ በቤተ ክርስቲያን እና በተቋማት ላይ የአመለካከት ለውጥ ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመው፣ በሁሉም አጋጣሚ ለእያንዳንዱ ሰው ትኩረትን መስጠት እና እንክብካቤን ማድረግ እንደሚያስፈልግ፣ ይህን ወደ ኃላፊነት መቀየር እንደሚገባ ተናግረዋል። የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒም በበኩላቸው፣ ለአካል ጉዳተኞች ባለው ቁርጠኝነት ላይ ሌላው ጠቃሚ ነገር፥ ሰብዓዊ ልምድ፣ ጥበብ፣ ብልህነት እና ባሕል ቤተ ክርስቲያን የያዘቻቸው እና የምታስተላልፋቸው እሴቶች ናቸው” ብለው፣ ተጨባጭ እና ዘላቂ የተግባር ዕቅዶችን ለማውጣት መንገዶችን ማመቻቸት፣ ትኩረትን በመስጠት በጋራ መወያየት እና ማደግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

03 June 2023, 16:31