ፈልግ

2021.01.22  Gesù e i pescatori ( Vangelo domenica 24 gennaio)

የግንቦት 13/2015 ዓ.ም ዘትንሣኤ 6ኛ እለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል አስተትኖ

የእለቱ ምንባባት

1.      ሮሜ 4፡ 14-25

2.    ራእ 20፡ 1-15

3.    ሐዋ ሥራ 10፡ 39-43 

4.    ዮሐ 21፡ 1-14

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

ደቀ መዛሙርቱ ዓሣ በታምር መያዛቸው

ከዚያም በኋላ ኢየሱስ በጥብርያዶስ ባሕር እንደ ገና ለደቀ መዛሙርቱ ታየ፤ በዚህም ሁኔታ ተገለጠ፤ ስምዖን ጴጥሮስ፣ ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ፣ የቃና ዘገሊላው ናትናኤል፣ የዘብዴዎስ ልጆችና ከደቀ መዛሙርቱ ሌሎች ሁለት አንድ ላይ ነበሩ፤ ስምዖን ጴጥሮስም፣ “ዓሣ ላጠምድ መሄዴ ነው” አላቸው፤ እነርሱም፣ “እኛም ከአንተ ጋር እንሄዳለን” አሉት። ወጥተውም ወደ ጀልባዋ ገቡ፤ በዚያ ሌሊት ግን ምንም አላጠመዱም። ሲነጋም፣ ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም ነበር። እርሱም፣ “ልጆች፣ ዓሣ አላችሁ?” አላቸው። እነርሱም፣ “የለንም” አሉት።

እርሱም፣ “መረባችሁን ከጀልባው በስተ ቀኝ ጣሉ፤ ዓሣ ታገኛላችሁ” አላቸው። እነርሱም በጣሉ ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ መረቡን መጐተት አቃታቸው። ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙርም፣ ጴጥሮስን፣ “ጌታ እኮ ነው!” አለው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ ‘ጌታ እኮ ነው!’ የሚለውን ቃል በሰማ ጊዜ፣ አውልቆት የነበረውን መደረቢያ ልብስ ታጠቀና ዘሎ ወደ ባሕሩ ገባ። ሌሎች ደቀ መዛሙርት ግን ከባሕሩ ዳርቻ የራቁት ሁለት መቶ ክንድ ያህል ብቻ ስለ ነበር፣ ዓሣ የሞላበትን መረብ እየሳቡ በጀልባዋ መጡ። ወደ ምድርም በደረሱ ጊዜ፣ ዓሣ በላዩ የነበረበት የከሰል ፍምና እንጀራ አዩ። ኢየሱስም፣ “አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ እስቲ አምጡ” አላቸው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ወደ ጀልባዋ ወጥቶ መረቡን ወደ ምድር ጐተተው፤ መረቡንም መቶ አምሳ ሦስት ትልልቅ ዓሣ ሞልተውት ነበር፤ ይህን ያህል ቢይዝም መረቡ አልተቀደደም። ኢየሱስም “ኑ፤ ቍርስ ብሉ” አላቸው። ጌታ እንደሆነ ዐውቀው ስለ ነበር፣ ከደቀ መዛሙርቱ፣ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ለመጠየቅ የደፈረ አልነበረም። ኢየሱስም መጥቶ እንጀራውን አንሥቶ ሰጣቸው፤ዓሣውንም ሰጣቸው። እንግዲህ ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ሲታይ ይህ ሦስተኛ ጊዜ ነው።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

በክርሰቶስ የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ!

ዛሬ እንደ ቤተክርስቲያናችን ሥርዓት አቆጣጠር የትንሳኤ ስድተኛ ሰንበትን እናከብራለን። እግዚአብሔር ሁሌም ሕይወታችን የተቀደሰ፣ የተስተካከለ እንዲሆን ይፈልጋል። ስለዚህ ዘወትር በሚሰጠን ጸጋና በረከት ብቻ ሳይሆን በየዕለቱ በተለይም በየሰንበቱ በሚሰጠን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባት አማካኝነት የእርሱን መንገድ ያሳየናል፤ ለየዕለቱ የሚሆን የሕይወት መመሪያ ይሰጠናል። እኛም ይህንን የሕይወት መምሪያ ማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ካዳመጥንም በኋላ በሕይወታችን ለመተግበር ብርቱ ጥረት እንድናደርግ ያስፈልጋል።

በዚህም መሠረት እንግዲህ ዛሬ በመጀመሪያ ንባብ ቅዱስ ሀዋርያው ጳውሎስ በሮሜ ሰዎች አድርጎ ወደ እያንዳዳችን ይመጣል፣ እንዲህም ይለናል “እምነት የክርስትና ሕይወታችንን የምንመራበት ሥር መሠረት በመሆኑ በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ልንሰጠው እንደሚገባ” ያሳስበናል።

እንግዲህ እምነት ስንል ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ የእግዚኣብሔር ልጅ መሆኑን፣ የሰውን ልጅ ከኃጢያት ለማንፃት በአባቱ መልካም ፈቃድ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በኩል አድርጎ ወደ ምድር መምጣቱን፣ ስለሰው ልጅ ኃጢያት ሲል መሰቃየቱን፣ መሞቱን፣ መቀበሩን፣ በሦስተኛ ቀንም ከሙታን ተለይቶ መነሳቱን፣ ማመንና ከዚህም እምነት የሚመነጨውን መንፈሳዊ ቡራኬ በዕለት ተዕለት ኑሮአችን ተግባራዊ ማድረግ ማለት ነው።

በዚህ በመጀመሪያው ንባብ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ሰለ እምነትና ሕግ ዘርዘር አድርጎ ያስረዳናል። እውነት ነው ሕግን መጠበቅ፣ ሕግን መፈጸም ተገቢ ነገር ሆኖ ሳለ ሰው ግን የሚጸድቀው ሕግን በመጠበቁ ብቻ ኣይደለም። ይልቁንም ከእግዚኣብሔር ከሚመጣ ምሕረትና ከእርሱ ቸርነት የተነሳ ብቻ ነው። ሰው ምን ያሕል ጠንካራና ጥንቁቅ ቢሆንም በዕድሜ ልኩ ሁሉ ሕግን ብቻ ጠብቆ ሊኖር አይችልም። የምንኖረው ገና በዚህ ምድር በመሆኑ ይህ ምድር ደግሞ በብዙ ክፋትና ኃጢያት የተተበተበ በመሆኑ በክርስትና ጉዞአችን ሁሌም ሕግን ብቻ ጠብቀን ለመጓዝ አንችልም። በጉዞአችን መውደቅና መነሳት መድከምና መበርታት አለ። ነገር ግን ትኩረታችን ሕግ ላይ ብቻ ከሆነ የምንሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት ይሁን መንፈሳዊ ጉዟችን ልክ የሙሴ መምሕራንና ፈሪሳውያኑ ያደርጉት እንደነበረው ለታይታና ከሰው ዘንድ ምስጋናና ከበሬታ ለመሰብሰብ ብቻ ይሆናል።

ሁልጊዜም ትኩረታችን ሕግ ላይ ብቻ ከሆነ ሕግን ባፈረስን ጊዜ ቁጣና ቅጣት ይኖራል። ይህም ከእግዚኣብሔር ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት ያደፈርሳል። እግዚኣብሔር ደግሞ ለልጆቹ ያለውን የምሕረትና የአባትነት ባሕሪ ዋጋ ያሳጣል። ስለዚህ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ሕግን ብቻ ለመጠበቅ ሳይሆን እምነታችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከቀን ወደቀን እያጠነከርንና እያበረታን እንድንሄድ ያሳስበናል። ምክንያቱም ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ገላትያ 3፡29 ላይ እንደጻፈው ወራሽ የመሆን መብት ወይም ዋስትና የሚገኘው በእምነት ብቻ መሆኑን ይገልፃል። ስለዚህ በእምነት በኩል ጸጋና በረከት እናገኛለንና እምነታችንን በየጊዜው ለማሳደግ ብርቱ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል። ሕግን  ብቻ ለመፈፀም የምንጥር ከሆነ ግን በስተመጨረሻ ከቅጣትና ከፍርድ አናመልጥም።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ የአብርሃምን እምነት እንደ ምሳሌ አድርጎ ይወስዳል። እንዲሁ የእኛም እምነት የአብርሃምን እንዲመስል ይፈልጋል። አብርሃም በሕይወቱ ብዙ መከራና ፈተና ደርሶበታል፣ ነገር ግን በእነዚህ ፈተናዎች ሁሉ ለእግዚኣብሔር ያለውን ታማኝነትና የእምነቱን ጠንካራነት አስመሰከረበት። ዛሬም ከእኛ የሚጠበቀው ይኸው ነው። በየትኛውም ዓይነት ፈተናና መከራ ውስጥ ብናልፍ ይህ መከራና ፈተና ምን ያህል ታማኞችና በእምነታችን ጠንካሮች መሆናችንን የምናስመሰክርበት አጋጣሚ እንጂ የውድቀታችን መገለጫ ሊሆን ኣይገባም።

አለማመን የእግዚኣብሔርን ክብር ይቀንሳል፣ አለማመን ወደ ተስፋ መቁረጥ ይመራል፣ አለማመን ሰውን ወደ ግዴለሽነት ይመራል፣ አለማመን የሕሊናን ድምጽ እንዳንሰማ ይከለክላል፣ አለማመን ሰው የተፈጠረበትን ዓላማ እንዲስትና በስሜታዊነት ብቻ እንዲመራ ያደርጋል፣ አለማመን ሰውን ወደ ኃጢኣትና ወደ ጨለማ ውስጥ እንዲወርድ ያደርጋል። ስለዚህ እኛ በየጊዜው እምነታችንን በመፈተሽ ከእንደዚህ ዓይነቱ የጥፋት መንገድ ራሳችንንም ሆነ በክርስቶስ ያገኘናቸውን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንድንታደግ ያስፈልጋል።

ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስ አብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ እንደተቆጠረለት በዚሁም ምክንያት የዘለዓለም ሕይወት ወራሽ እንደሆነ ሁሉ እኛም እምነታችን ጠንካራ ሆኖ እንደ ጽድቅ እንዲቆጠርልን በዚሁም ምክንያት የዘለዓለም ሕይወት ወራሾች እንድንሆን ያበረታታናል። በዮሐንስ ራዕይ ላይም ወንጌላዊው ዮሐንስ በራዕዩ ለእግዚኣብሔር በመታመንና እግዚኣብሔርን በመፍራት የኖሩ ሰዎች ሁሉ መጨረሻቸው ያማረና በመንግስተ ሰማይ ከሰማዕታትና ከቅዱሳን ጋር ዳግመኛ ሞት በሌለበት እንደሆነ ይናገራል። እንዲሁም ሰዎች ሁሉ የሚድኑት በእምነታቸው ቢሆንም የእውነተኛ እምነት መገለጫው ደግሞ በመልካም ሥራ ነውና እኛም በምድር ላይ እያለን የሰራነው መልካም ሥራ ሁሉ በኋላ በመልካም ሥራ መዝገብ ውስጥ እንደሚጠብቀን ይናገራል። መልካም ያልሰራን ከሆነ ደግሞ ሥማችን በሕይወት መዝገብ ላይ ሰፍሮ አይገኝምና ከወዲሁ የመልካም ሥራ ሁሉ ተካፋዮች በመሆን የምድራዊም ሆነ የሰማያዊ ቤታችንን አንድናዘጋጅ ይጋብዘናል። የዛሬው የዮሐንስ ወንጌልም የሚያስረዳን ነገር ቢኖር እምነታችንን በእግዚኣብሔር ላይ ጥለን የምናደርገው ነገር ሁሉ ሁል ጊዜም ውጤታማና የተሳካ እንደሚሆን ያስተምረናል። በዛሬው በዮሐንስ ወንጌል እንዳዳመጥነው ሐዋርያቶች ሌሊቱን ሙሉ ዓሣ ለማጥመድ ሲደክሙ አድረው ምንም ዓይነት ዓሣ ለማጥመድ ኣልቻሉም ነገር ግን ጌታችን እየሱስ ክርስቶስ በዚህ በስተቀኝ በኩል መረባቸውን እንዲጥሉ ነገራቸው እነርሱም በሙሉ እምነት መረባቸውን በስተቀኝ በኩል ጣሉት ሌሊቱን ሙሉ ሲደክሙ ምንም ዓይነት ዓሣ ያላገኙት ኣሁን ግን በታዘዙት መሠረት መረቡን በመጣላቸውና በእርሱም ቃል ታምነው እንዳላቸው በማድረጋቸው እጅግ በጣም ብዙ ዓሣ ኣጠመዱ  ከዓሣውም ብዛት የተነሳ መረቡን ለመጎተት ኣቃታቸው። እንግዲህ ይህ የሚያስተምረን እኛም ዘወትር በምናደርገው ነገር ሁሉ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስን እርዳታ የእርሱ ጸጋ ከእኛ ጋር ካለ የማይሳካ ነገር ኣይኖርም ስለዚህ ኣጥብቀን የእርሱን እርዳታ መለመን ወይም መጸለይ ያስፈልገናል። በምናደርገው ነገር ሆነ በምንናገረው ነገር ሁሉ የጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእኛ ጋር ካለ ሥራችን ሆነ ቃላችን የተሳካና አጥጋቢ እንዲሁም ገንቢ ይሆናል።

እምነታችንን እንዲጨምርልን ከእምነታችንም በምናገኘው ጸጋና ብርታት ጌታችን እየሱስ ክርስቶስን በሙሉ ልብ መከተል እንድንችልና እውነተኛ ይእርሱ ደቀመዝሙር ለመሆን እንድንበቃ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ታግዘን ከልጇ ከጌታችን እየሱስ ክርስቶስ ይህንን መንፈሳዊ በረከት ታሰጠን።

 

 

20 May 2023, 20:29