ፈልግ

ኢየሱስ በምድረበዳ በዲያቢሎስ ተፈተነ ኢየሱስ በምድረበዳ በዲያቢሎስ ተፈተነ  

የኢየሱስ ፈተና

ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ከአባቱ እቅፍ ከሰማይ ሰማያት ወርዶ በድንግል ማርያም ማኀጸን አንደ ማንኛውም ሕፃን ለዘጠኝ ወራት አድሮ ሥጋችንን መልበስ አልበቃውም፥ የሕወታችንን መከራ ሁሉ ሊሸከም ከኃጢአት በስተቀር በሁሉም እንደ እኛ መሆን ፈለገ። ሰይጣን ልክ እኛን እንደሚፈትነን እንዲሁም እርሱ እንዲፈትነው ፈቀደለት።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን  

የማቴዎስ ወንጌል የእየሱስን ፈተና በማስመልከት የሚከተለውን ይገልጻለ። ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ በዲያብሎስ እንዲፈተን ወደ በረሃ ሄደ። በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት እዚያ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቆየና ራበው፤ በዚህን ጊዜ ፈታኙ ዲያብሎስ ወደ ኢየሱስ መጥቶ «አንተ የእግዚአበሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ እነዚህን ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” (ማቴ 4፡3) አለው። ኢየሱስም «ሰው የሚኖረው እግዚአብሔር በሚናገረው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይደለም ተብሎ ተጽፎአል” (ማቴ. 4፡4) አለው። ዲያብሎስም ፈተናውን በመቀጠል ኢየሱስን ወደ ቅድስት ከተማ ኢየሩሳሌም ወሰደው፤ በቤተ መቅደስ ጣራ ጫፍ ላይ አውጥቶ አቆመውና «አንተን እንዲጠብቁ እግዚአብሔር መላእክቱን ያዝልሃል፣ እግርህም በድንጋይ እንዳይሰናከል በእጃቸው ይደግፋሃል ተብሎ ተጽፎል፤ ስለዚህ አንተ የእግዚአበሔር ልጅ ከሆንክ እስቲ ከዚህ ወደታች ዘለህ ውረድ” (ማቴ 4፡6) አለው። ኢየሱስም «እግዚአብሔር አምላክህን አትፈታተንው ተብሎ ተጽፏል” (ማቴ. 4፡7) ሲል መለሰለት።

ለመጨረሻ ጊዜ ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ ከፍተኛ ተራራ ላይ አወጣው የዓለምን መንግሥታትና ክብራቸውን በአንድ አፍታ ቁልጭ አድርጐ አሳየውና «ይህ ሁሉ የእኔ ነው፣ የእኔ የተሰጠ ነው፣ ተንበርክከህ ብትሰግድልኝ በሙሉ እሰጥሃለሁ” አለው። ኢየሱስም እጅግ ተቆጣና «ወዲያ ሂድ አንተ ሰይጣን ለአምላክህ ለእግዚአበሔር ብቻ ስገድ፤ እሱንም አምልክ ተብሎ ተጽፎአል” (ማቴ. 4፣1-11) አለው። በዚህ ዓይነት ለሁልጊዜ ከአርሱ እንዲርቅና ፈጽሞ እንዲሸሽ አደረገው፣ ያን ጊዜ ዲያብሎስ ኢየሱስን ትቶት ፈረጠጠ መላእክትም መጥተው አገለገሉት።

ኢየሱስ ሊፈተን መፈለጉ ፈተና እኛ እንደምናስበው ኃጢአት እንዳልሆነ ያስረዳናል። ኃጢአት ያልሆነ ብቻ ሳይሆን ብንቀበለውና ባናጉረመርም ትሩፋት አድርጐ እንደሚቆጥርልን የስረዳናለ። እኛ ፈተና ሲመጣብን ብዙ እንሸበራለን፤ ሰላምና እርጋታ እናጣለን፣ መዓት የወረደብን ይመስለናል፣ በፍራቻ ምክንያት ፈተናን መቋቋም ያቅተናል። ቅዱስ ያዕቆብ «ፈተናን ታግሶ የሚጸና ሰው የተባረከ ነው” (ያዕቆብ 1፡12)። ምክንያቱም በቃል ኪዳኑ መሠረት ለወዳጆቹ የሚሰጠውን የሕይወት አክሊል እያሰብን በፈተና ወቅት ጠንክረን፣ እንዋጋ፤ ያነቃቃናል፣ ያበረታታናልም፤ ነገሩ ከገባን ፈተና ለጥቅማችን ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ የመጡበትን ሶስት ዓይነት ፈተናዎች በርትቶ ወዲያውነ በድል ተወጣ። ይህም እኛ ፈተናን እንዴት እንድንዋጋ ወይም ከእርሱ ልንርቅ እንደሚገባን ሲያስተምረን ነው። ፈተና ሲመጣብን ተግተን ከተቋቋም ፈንታ ወዲያው ከማባረር ይልቅ ደህና ነው እስቲ ምን አለበት እያልን እንዲበረታ ችላ ብለን እንተወዋለን። ከበረታብን በኋላ ልንዋጋው እንነሣለን። «እራሱን ከፈተና የማይጠብቅ ሁሉ በእርሱ ይጠፋል” (መ. ምሳሌ 25፡8) እያለ ያስጠነቅቀናል። አንድ ትልቅ ሮማዊ ፀሐፊ «በመጀመሪያ ተከላከል፤ ምክንያቱም ፈተና ከበረታና ካየለ ትግል ሊገታው አይችልም” ይላል። ኢየሱስን መምህራችንን አይተን በፈተና ጊዜ ትጉሆች እንሁን ፈተናን በርትተን አንቋቋመው፣ ያን ጊዜ ጠላትን ድል እንነሣለን፣ አሸናፊዎችም እንሆናለን።

31 March 2023, 14:57