ፈልግ

2021.09.22 Amore

ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ

ክፍል ሦስት

ፍቅር ከሌሎች ጋር ይደሰታል

በሰዎች ክፉ መደሰት በሰው ልብ ውስጥ የመሸገ አሉታዊ ስሜት ነው። በሌሎች ሰዎች ላይ በደረሰ በደል የሚደሰቱ ሰዎች ያላቸው መርዘኛ አስተሳሰብ ነው። ‹‹ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል›› የሚለው አገላለጽ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው። በሌላ አነጋገር፣ እኛ በሌሎች በጎ  የምንደሰተው ክብራቸውን ስናይና ለችሎታቸውና መልካም ሥራዎቻቸው ዋጋ ስንሰጥ ነው። ሁልጊዜ ሰውን ከሰው ለሚያወዳድሩና ከትዳር አጋሮቻቸው ጋር እንኳ ለሚፎካከሩ ይህን ማድረግ ስለማይሆንላቸው  በሌሎች  ውድቀት በስውር ደስ ይላቸዋል።

አፍቃሪ ሰዎች ለሌሎች በጎ ሲያደርጉ ወይም ሌሎች ሲደሰቱ ሲያዩ፣ እነርሱ ራሳቸው ደግሞ በደስታ ይኖራሉ፣ በዚህም መንገድ ለእግዚአብሔር ክብርን ይሰጣሉ፣ ምክንያቱም ‹‹ እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳልና›› (2 ቆሮ. 9፡7)። ጌታችን በተለይ በሌሎች ደስታ ሐሤት የሚያደርጉ ሰዎችን ይወዳል። በሌሎች በጎ መደሰትን ካላወቅንና በራሳችን ፍላጎት ላይ ብቻ ብናተኩር፣ ራሳችንን ለደስታ አልባ ሕይወት እንዳርጋለን፤ ምክንያቱም ኢየሱስ እንዳለው፣‹‹ ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው›› (የሐዋ. 20፡ 35)። ስለዚህ፣ ቤተሰብ ከአባላቱ አንዳቸው  መልካም ነገር በሚገጥመው ጊዜ ሁሉ ሌሎችም አብረው እንደሚደሰቱ የሚያውቁበት ቦታ መሆን አለበት።

ፍቅር ሁልጊዜ ይታገሣል

ጳውሎስ ስለ ፍቅር ያቀረበውን ዝርዝር ‹‹ሁሉን›› በሚሉ አራት ስንኞች  ያጠቃልላል። ፍቅር ሁሉን ይታገሣል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ በሁሉ ይጸናል። እዚህ ላይ የሚያሰጋውን ነገር ሁሉ መሸከም የሚችለውን የፍቅርን ፀረ ባህላዊ ኃይል እናያለን። አንደኛ፣ ጳውሎስ እንዳለው፣ ፍቅር ‹‹ሁሉን ይታገሣል››። ይህም ክፋትን መkkም ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ነው። አንደበትን ከመጠቀም ጋር የተያያዘ ነው። ግሡ ከሌላው ሰው በደል ጋር በተያያዘ ‹‹የራስን ሰላም መጠበቅ››ነው ሊባል ይችላል። ፍርድ ከመስጠት መቆጠብን፣ ብርቱና ጨካኝ የውግዘት ስሜት መቆጣጠርን ያመለክታል። ‹‹አትፍረዱ፣ አይፈረድባችሁም›› (ሉቃ. 6፡ 37)። በተለምዶ አንደበታችንን ከምንጠቀምበት ሁኔታ በተቃራኒ፣ የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ወንድሞችና እህቶች ሆይ፣  እርስ በርሳችሁ አትወነጃጀሉ›› (ያዕ. 4፡ 11) ይለናል። ሌላውን ሰው መወንጀል፣ ራሳችንን ንጹሕ የማድረጊያና ስለምናደርሰው ጉዳት ግድ ሳይኖረን ቅሬታንና ቅናትን  መተንፈሻ መንገድ ይሆናል። ሐሜት ኃጢአት መሆኑን ብዙውን ጊዜ እንዘነጋለን፤ የሌላውን ሰው መልካም ስም ክፉኛ የሚጎዳና ያንን ስም ማደስ የማያስችል ጉዳት የሚያደርስ ከሆነ፣ በእግዚአብሔር ላይ የተፈጸመ ከባድ በደል ይሆናል። ስለዚህ፣ የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ እንደሚያትተው፣ ምላስ ‹‹ የክፋት ዓለም ናት፣ ሰውነትን ሁሉ ታረክሳለች›› (ያዕ. 3፡ 6)፤ ‹‹የሚገድል መርዝ የሞላባትና ዕረፍት የሌላት ክፉ ነገር ናት›› (ያዕ. 3፡ 8)። ምላስ ‹‹በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠሩትን ሰዎች ለመርገም›› (ያዕ. 3፡ 9) ስታገለግል፣ ፍቅር ደግሞ የሌሎችን፣ የጠላቶችን ጭምር፣ መልካም ስም ይጠብቃል። ስለዚህ፣ የእግዚአብሔርን ሕግ ለመጠበቅ ስንሻ፣ ይህን የፍቅርን ልዩ ትእዛዝ ከቶ መርሳት የለብንም።  

በፍቅር የተሳሰሩ ጥንዶች ስለ እርስ በርሳቸው በጎ ይነጋገራሉ፤ የአጋራቸውን ድክመትና ስሕተት ሳይሆን በጎ ጎኑን ለማሳየት ይጥራሉ። በማናቸውም ወቅት፣ ስለ እርስ በርሳቸው ክፉ በመናገር ፈንታ ዝም ይላሉ። ይህም በሌሎች ሰዎች ፊት ብቻ የሚደረግ አይደለም፤ ከውስጣዊ አስተሳሰብ የሚመነጭ ድርጊት ነው። በብልጠት የሌሎችን ችግሮችና ድክመቶች አናይም ከማለት ይልቅ እነዚያን ድክመቶችና ስሕተቶች ሰፋ ባለ አገባብ ማየትና እነዚህ ድክመቶች የትልቁ ሥዕል አካል መሆናቸውን መገንዘብ ነው። ሁላችንም የብርሃንና የጨለማ ውስብስብ ድብልቅ መሆናችንን መገንዘብ አለብን። ሌላው ሰው እኔን ከሚያናድዱ ጥቃቅን ነገሮች ድምር ውጤት ይበልጥብኛል። ዋጋ እንሰጠው ዘንድ ፍቅር የግድ ፍጹም መሆን የለበትም። ሌሎች ሰዎች የተቻላቸውን ያህል፣ ከነድክመታቸውና ዓለማዊነታቸው ይወዱኛል። ፍቅር ፍጹም አለመሆኑ ግን ሐሰት ነው ወይም እውነት አይደለም ማለት አይደለም። ውስንና ዓለማዊ ቢሆንም እውነት ነው። እኔ ብዙ ነገር የምጠብቅ ከሆነ፣ ሌላው ሰው ይህ እንዳይሆን ይነግረኛል፤ ምክንያቱም እርሱ እንደ እግዚአብሔር ሊሆንልኝ ወይም ፍላጎቴን ሁሉ ሊያሟላልኝ አይችልም። ፍቅር ከጉድለት ጋር አብሮ ይኖራል። ‹‹ ሁሉን ይታገሣል››፣ ሰላሙንም ከሚወዱት ሰው ጉድለት ያስቀድማል።

ፍቅር ሁሉንም ነገር ያምናል

ፍቅር ሁሉን ያምናል። እዚህ ላይ ‹‹እምነት›› ሲባል ቃሉ መታየት ያለበት ከነገረ መለኮታዊ ትርጉሙ አኳያ ሳይሆን፣ ይልቁንም ‹‹መተማመን›› በሚለው መልኩ ነው። ይህም ሌላው ሰው አይዋሽም ወይም አያታልልም ብሎ ከማሰብ በላይ ነው። ይህን የመሰለ መሠረታዊ እምነትን ማሳደር ከዐመድ ሥር እንዳለ ፍም፣ በጨለማ ውስጥ የሚያበራውን የእግዚአብሔርን ብርሃን ይቀበላል።  

ይህ መተማመን ግንኙነትን ነጻ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህም ማለት ሌላውን ሰው መቆጣጠር፣ ሰዎች ከቁጥጥራችን ሥር ቢወጡም እንኳ እያንዳንዱን እርምጃቸውን መከታተል የለብንም ማለት ነው። ፍቅር ያምናል፣ ነጻ ያደርጋል፣ ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር፣ ለመያዝ፣ ለመግዛት ጥረት አያደርግም። ነጻነትንና  በዙሪያችን ላለው ዓለምና ለአዳዲስ ተሞክሮዎች ክፍት መሆንን የሚያዳብረው፤  ይህ ነጻነት ግንኙነቶችን ያጠናክራል፣ ያስፋፋል። ባለትዳሮችም ከቤተሰብ ክልል ውጭ ያገኙትንና የተማሩትን ነገር ሁሉ እርስ በርስ ይጋራሉ። እንደዚሁም፣ ይህ ነጻነት ሐቀኝነትንና ግልጽነትን ያመጣል፤ ምክንያቱም መታመናቸውንና መመስገናቸውን የሚያውቁ ሰዎች ግልጽ ይሆናሉ፣ የሚደብቁት ነገር አይኖራቸውም። የትዳር አጋራቸውን ሁልጊዜ በጥርጣሬ ዐይን የሚያዩ፣ ኮናኝና ነጻ ፍቅር የሌለው ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ምሥጢር ወደ መደበቅና ጉድለታቸውንና ድክመታቸውን ወደ መሸፋፈን ያዘነብላሉ፤ ማንነታቸውን ትተው ሌላ ሰው ለመምሰል ይሞክራሉ። በሌላ በኩል፣ ምንም ይሁን ምን፣ በፍቅር የሚተማመን ቤተሰብ አባላቱን ራሳቸውን እንዲሆኑና ሽንገላን፣ ሀሰትንና ውሸትን  እንዲጠሉ ያደርጋቸዋል።

ፍቅር በሁሉ ነገር ተስፋ ያደርጋል

ፍቅር ስለ መጪው ጊዜ ተስፋ አይቆርጥም። ቀደም ሲል ከተነገረው  ቀጥሎ ያለው ይህ ሐረግ ሌሎች ሰዎች ሊለወጡ፣ ሊያድጉና ያልተጠበቀ ውበትና ያልተነገረ እምቅ ኃይል ሊያንጸባርቁ እንደሚችሉ ተስፋ ስለሚያደርግ ሰው ይናገራል። ይህ ማለት ግን፣ በዚህ ሕይወት ውስጥ ሁሉ ነገር ይለወጣል ማለት አይደለም። ነገሮች ሁልጊዜ እኛ በተመኘነው መልኩ ባይፈጸሙም፣ እግዚአብሔር ጠማማ መስመሮችን እንደሚያቃናና በዚህ ዓለም ከምንታገሠው ክፉ ነገር መልካም ነገርን ማውጣት እንደሚችል መገንዘብን ያካትታል።

እዚህ ላይ ተስፋ በራሱ ምሉእ የሚሆነው ከሞት በኋላ ያለውን እውነተኛ ሕይወት ስለሚቀበል ነው። እያንዳንዱ ሰው፣ ከነጉድለቶቹ፣ ለመንግሥተ ሰማይ ሙሉ ሕይወት ተጠርቶአል። በዚያም፣ ድክመት፣ ጨለማና ስንኩልነት ሁሉ ይወገዳል፣ በክርስቶስ ትንሣኤ ሙሉ በሙሉ አዲስ ይሆናል። በዚያ የሰው እውነተኛ ማንነት ከነ ሙሉ ደግነቱና ውበቱ ይንጸባረቃል። በዚህ ዓለም ሕይወት ውስጥ የሚያበሳጩ ሁኔታዎች ቢኖሩም፣ ይህ ግንዛቤ መኖሩ በራሱ እያንዳንዱን ሰው ከመለኮታዊ እይታና ከተስፋ ብርሃን  አንጻር እንድንመለከትና፣ ገና ባይገለጥም እንኳ፣ በመንግሥተ ሰማይ የሚያገኘውን ሙላት በተስፋ እንድንጠባበቅ ያደርገናል።

ፍቅር በሁሉ ነገር ጸንቶ ይቆማል

ፍቅር ማንኛውንም ፈተና በአዎንታዊ አስተሳሰብ ይታገሣል። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ጸንቶ ይቆማል። ይህ ‹‹ጽናት›› አንዳንድ የሚያበሳጩ ነገሮችን የመታገሥ ችሎታን ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያ በላይ የሆነውን፣ ማለትም ማናቸውንም ተግዳሮት ለመkkም ሁልጊዜ ዝግጁ መሆንን ያካትታል። በጨለማ ሰዓት እንኴ ሳይቀር ከቶ ተስፋ የማይቆርጥ ፍቅር ነው። ቆራጥነትና ተጋድሎን ፣ ማናቸውንም አሉታዊ ማዕበል የመkkም ኃይልንና  ለደግነት ምንጊዜም ዝግጁ መሆንን ያሳያል። እዚህ ላይ ትዝ የሚለኝን፣ ማናቸውንም ዐይነት ፈተናና መከራ በወንድማማችነት ፍቅር የተቀበለውን የማርቲን ሉተርን አባባል መጥቀስ እፈልጋለሁ፣ ‹‹እጅግ የሚጠላህ ሰው አንዳች መልካም ነገር በውስጡ አለው፤ እጅግ የሚጠላህ አገርም አንዳች መልካም ነገር በውስጡ አለው፤ እጅግ የሚጠላህ ዘርም ቢሆን አንዳች መልካም ነገር በውስጡ አለው። ስለዚህ፣ እያንዳንዱን ሰው ፊት ለፊት አተኩረህ ስትመለከተውና ሃይማኖት ‹‹የእግዚአብሔር አምሳል›› ብሎ የሚጠራውን ሰው ውስጡን ጠልቀህ ስታየው፣ ያንን ሰው እንዲሁ መውደድ ትጀምራለህ። እርሱ ምንም ቢያደርግ፣ በዚያ ሰው ውስጥ የእግዚአብሔርን መልክ ታይበታለህ። ከቶ ሊደመስሰው የማይችል የደግነት ባህርይ አለው… ጠላትህን የምትወድበት ሌላው መንገድ ይህ ነው፤ ጠላትህን ማሸነፍ የምትችልበት አጋጣሚ ሲደርስ፣ ማድረግ የሌለብህ ያኔ ነው። … ወደ ፍቅር፣ ወደ ትልቅ ውበቱና ኃይሉ ደረጃ  ከፍ ስትል፣ ያኔ ክፉ ሥርዓቶችን ብቻ ለማሸነፍ ትሻለህ።… በዚያ ሥርዓት የተጠመዱ ሰዎችን ውደዳቸው፣ ሥርዓቱን ግን ለማሸነፍ እሹ።… ጥላቻን በጥላቻ መመለስ በዓለም ላይ የጥላቻንና የክፋትን ዕድሜ ያራዝማል። እኔ ብመታህና አንተም መልሰህ ብትመታኝ፣ እኔም እንደ ገና ብመታህ አንተም መልሰህ ብትመታኝ ወዘተ. ድርጊቱ የት የሌሌ  እንደሚሆን ታያለህ። ጨርሶ አይቆምም። አንድ ቦታ ላይ አንድ ሰው ትንሽ ወደ ልቡ መመለስ አለበት፣ ያ ሰው ብርቱ ነው። ብርቱ ሰው የጥላቻን ሰንሰለት፣ የክፋትን ሰንሰለት መቁረጥ የሚችል ሰው ነው።… አንድ ሰው ይህን ሰንሰለት ለመቁረጥና በዓለም መዋቅር ውስጥ ብርቱና ኃይለኛ የፍቅር ነገር የሚያሰርጽ በቂ ሃይማኖትና በቂ ግብረ ገብነት እንዲኖረው ያስፈልጋል››።

በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ የቤተሰብን ፍቅር  ለማጥፋት የሚጥረውን ማንኛውንም ክፋት ለመመከትም የሚረዳንን የፍቅር ኃይል ማዳበር ያስፈልገናል። ፍቅር በንዴት፣ ሌሎችን በመናቅ ወይም የሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ሌሎችን በመጉዳት አይሸነፍም። በተለይ በቤተሰቦች ዘንድ ያለው ዐይነተኛ ክርስቲያናዊ አስተሳሰብ ከቶ ተስፋ የማይቆርጥ ፍቅር ነው። አንዳንድ ጊዜ ለራሳቸው ደህንነት ሲሉ ከትዳር አጋራቸው የተለያዩ፣ ነገር ግን፣ ከዘላቂ የጋብቻ ፍቅራቸው የተነሣ፣ በሕመማቸው፣ በችግራቸው ወይም ፈተና በገጠማቸው ወቅት፣ ሌሎች ሰዎችን በማስተባበር ጭምር፣ ሊረዱዋቸው የሚጣጣሩ  ወንዶችን ወይም ሴቶችን ሳይ ይገርመኛል። እዚህም ላይ ተስፋ የማይቆርጥ ፍቅር እናያለን።

ምንጭ፡ ፍቅር በቤተሰብ ውስጥ በሚል ርእስ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ለጳጳሳት፣ ለካህናትና ለዲያቆናት፣ ለመነኮሳት፣ ለክርስቲያን ባለ ትዳሮች እና ለምእመናን በሙሉ ያስተላለፉት የድኅረ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ምክር ከአንቀጽ 108-119 ላይ የተወሰደ መሆኑን እንገልጻለን።

አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

 

 

29 March 2023, 11:04