ፈልግ

የየካቲት 26/2015 ዓ.ም የመጀመሪያው የዐብይ ጾም ሳምንት ንባባት እና የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

ከእግዚአብሔር ጋር ያላችሁን አንድነት አጠናክሩ፣ በፈተና ወቅት ቃሉን ተቀበሉ

የእለቱ ምንባባት

1.      ኦሪት ዘፍጥረት 2፡7-9፣ 3፡1-7

2.     መዝሙር 50

3.     ሮም 5፡12-19

4.    ማቴዎች 4፡1-11

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል

የኢየሱስ መፈተን

ከዚህ በኋላ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን በዲያብሎስ ይፈተን ዘንድ ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ተራበ። ፈታኙም ወደ ኢየሱስ ቀርቦ፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ እነዚህን ድንጋዮች እንጀራ እንዲሆኑ እዘዝ” አለው ኢየሱስም፣ “ ‘ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም’ ተብሎ ተጽፏል” ሲል መለሰለት።

ቀጥሎም ዲያብሎስ ኢየሱስን ወደ ቅድስት ከተማ በመውሰድ ከቤተ መቅደሱም ዐናት ላይ አውጥቶ፣ “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ራስህን ወደ መሬት ወርውር፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፤ “ ‘እግርህ በድንጋይ እንዳይሰናከል፣ በእጃቸው ያነሡህ ዘንድ፣ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዝልሃል።’ ” ኢየሱስም፣ “እንደዚሁም በመጻሕፍት፣ ‘እግዚአብሔር አምላክህን አትፈታተነው’ ተብሎ ተጽፏል” በማለት መለሰለት።

እንደ ገናም ዲያብሎስ ኢየሱስን እጅግ ከፍ ወዳለ ተራራ አወጣው፤ የዓለምንም መንግሥታት ከነክብራቸው አሳየውና፣ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” አለው። ኢየሱስም፣ “አንተ ሰይጣን ከፊቴ ራቅ! ‘ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ እርሱንም ብቻ አምልክ’ ተብሎ ተጽፏልና” አለው። ከዚያም ዲያብሎስ ትቶት ሄደ፤ መላእክትም መጥተው አገለገሉት።

የእለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

 

የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እሕቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

የዚህ የዐብይ ጾም ሳምንት የመጀመሪያ እለተ ሰንበት ላይ የተነበበው ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ በዲያቢሎስ በምድረ በዳ እንደ ተፈተነ የሚገልጸውን ታሪክ አቀረብልን (ማቴ. 4፡1-11)። “ዲያብሎስ” ማለት “ከፋፋይ” ማለት ነው። ስሙ የሚያደርገውን ይነግረናል፡ ይከፋፍላል። ኢየሱስን ለመፈተን ሲያደርገው በነበረው ጥረት እቅዱን ይፋ አድርጎታል። እንግዲያው ከማን ሊከፋፍለው እንደሚፈልግ እና እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ዲያብሎስ ኢየሱስን የሚከፋፍለው ከማን ነው? ከመፈተኑ ጥቂት ቀደም ብሎ፣ በዮርዳኖስ ወንዝ ጥምቀትን ከዮሐንስ ሲቀበል፣ ኢየሱስ በአብ “የምወደው ልጄ” ተብሎ ተጠርቷል (ማቴ 3፡17)፣ እና መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በእርሱ ላይ ወረደ (ማቴ 3፡16) ስለዚህ ቅዱስ ወንጌል በፍቅር የተቀላቀሉትን ሦስቱን መለኮታዊ አካላት አቅርቦልናል። ይህ ብቻ አይደለም፡ ኢየሱስ ራሱ ወደ ዓለም የመጣው በእርሱና በአብ መካከል ባለው አንድነት እንድንካፈል ሊያደርገን እንደሆነ ይናገራል (ዮሐ. 17፡11)። ዲያቢሎስ ይልቁንም ተቃራኒውን ያደርጋል፡ ወደ ስፍራው የገባው ኢየሱስን ከአብ ለመከፋፈል እና እኛን አንድ ለማድረግ ካለው ተልእኮ ለማዘናጋት ነው።

አሁን እንዴት ለማድረግ እንደሚሞክር እንመልከት። ዲያብሎስ አርባ ቀን እንደ ጾመ እና እንደተራበ ደካማ የሆነውን የኢየሱስን የሰው ልጅ ሁኔታ ለመጠቀም ይፈልጋል (ማቴ. 4፡2)። ከዚያም ይህ ክፉ መንፈስ የአንድነት ተልእኮውን ሽባ ለማድረግ ሦስት ኃይለኛ "መርዞችን" በእሱ ውስጥ ለመትከል ይሞክራል። እነዚህ መርዞች ማበር ወይም ግንኙነት፣ አለመተማመን እና ስልጣን የተሰኙት ናቸው። በመጀመሪያ ደረጃ ከቁሳዊ እቃዎች፣ ከፍላጎቶች ጋር የተያያዘ መርዝ፥ በሚያባብል ክርክር ዲያብሎስ ኢየሱስን ለማሳመን ሞከረ፡- “ተርበሃል፣ ስለ ምን ትጾማለህ? ፍላጎትህን አዳምጠህ አሟላው፤ መብትና ኃይል አለህ፤ ድንጋዮቹን ወደ ዳቦ ቀይር። ከዚያም ሁለተኛው መርዝ፣ አለመተማመን፡ “አብ የሚጠቅምህን ነገር ብቻ እንደሚፈልግ እርግጠኛ ነህ? እሱን ፈትነው፣ አስጨንቀው! ራስህን ከቤተ መቅደሱ ከፍተኛ ቦታ ወርውረህ የምትፈልገውን ነገር እንዲያደርግልህ አድርግ። በመጨረሻም ሥልጣን የሚለውን መርዝ እናገኛለን፡- “አባታችሁ በፍጹም አያስፈልጋችሁም! ለምን የእርሱን ስጦታዎች ትጠብቃላችሁ? የዓለምን መመዘኛዎች ተከተል፣ ሁሉንም ነገር ለራስህ ውሰድ፣ እናም ኃይለኛ ትሆናለህ! " ይህ ጉዳይ አስፈሪ አይደለም? ነገር ግን ለኛም እንደዛ ነው፡ ከቁሳዊ ነገሮች ጋር መጣበቅ፣ አለመተማመን እና የስልጣን ጥማት ዲያቢሎስ ከአብ ለመለያየት የሚጠቀምባቸው ሶስት የተስፋፉ እና አደገኛ ፈተናዎች ናቸው። በመካከላችን ያሉ እህቶች እና ወንድሞች ለእኛ እንደ ማይጠቅሙን እና እኛም ብቻችን እንደ ሆንን እንዲሰማን በማድረግ ወደ ተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ሊከተን ይፈልጋል። ይህን በኢየሱስ ላይ ሊያደርግ ፈልጎ ነበር ዛሬም በእኛ ላይ የሚነዛው መርዝ ነው፣ ሊያደርግም ይፈልጋል።

ኢየሱስ ግን ፈተናዎችን አሸንፏል። እንዴት? ከዲያብሎስ ጋር መወያየትን በማስወገድ እና በእግዚአብሔር ቃል መልስ በመስጠት። ከቅዱሳት መጻሕፍት ሦስት ሐረጎችን ጠቅሷል፣ ከቁሳቁሶች ነፃ ስለመሆን (ዘዳ 8:3)፣ መታመን (ዘዳ 6:16)፣ እና ለእግዚአብሔር አገልግሎት መስጠት (ዘዳ. 6:13)፣ የሚቃረኑ ሦስት ሐረጎች ወደ ፈተና ውስጥ ሊከቱን ይችሉ ይሆናል። እርሱ ከዲያብሎስ ጋር አይወያይም፥ ከዲያብሎስ ጋር አትከራከርም! ከእርሱ ጋር በመደራደር አሸናፊ መሆን የምትችል ሳይሆን በመለኮታዊ ቃል በእምነት በመቃወም አሸናፊ ያደርጋሃል። በዚህ መንገድ፣ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር ጋር እና በመካከላችን ያለውን አንድነት ከከፋፋዮች ጥቃት እንድንከላከል ያስተምረናል። እናም አንድነት ያስፈልገናል!

እናም፣ እራሳችንን እንጠይቅ፡ የእግዚአብሔር ቃል በህይወቴ ምን ቦታ አለው? በመንፈሳዊ ትግሌ ወደ እሱ እመለሳለሁ? መጥፎ ወይም ተደጋጋሚ ፈተና ካለብኝ፣ ለክፉ ነገር ምላሽ የሚሰጠውን የአምላክ ቃል ጥቅስ በመፈለግ ለምን እርዳታ አላገኘሁም? ከዚያም ፈተና ሲመጣ፣ አነባለሁ፣ እጸልያለሁ፣ በክርስቶስ ጸጋ አምኜ እኖራላሁ ወይ ብለን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል። እንሞክር፣ በፈተናዎች ውስጥ ይረዳናል፣ ስለዚህም በውስጣችን በሚቀሰቅሱት ድምፆች መካከል፣ ቸር የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ይሰማል። የእግዚአብሔርን ቃል ተቀብላ በትህትናዋ የከፋፍለህ ግዛውን ትምክህት ያሸነፈች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዐቢይ ጾም መንፈሳዊ ተጋድሎ ማድረግ እንችል ዘንድ በአማላጅነቷ ትርዳን።  

ምንጭ፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በየካቲት 19/2015 ዓ.ም በቫቲካን በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ካደረጉት ስብከት የተወሰደ።

አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

 

 

05 March 2023, 11:10