ፈልግ

የቅዱስ ቤተሰብ የቅዱስ ቤተሰብ 

የቅዱስ ዮሴፍ አባትነት የእግዚአብሔር ርኅራኄ ያለበትን ፍቅር ይገልጻል

በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በመጋቢት 19/2015 ዓ.ም የቅዱስ ዮሴፍ አመታዊ በዓል በመከበር ላይ ይገኛል። ቅዱስ ዮሴፍ የቅዱስ ቤተሰብ ማለትም አንዱ አባል መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ከእግዚአብሔር የተሰጠውን አደራ ተቀብሎ ኢየሱስን በትጋት እና በትህትና አሳድጎታል፣ የኢየሱስ እናት ማርያምንም የሚገባትን ክብር ሰጥቷታል። ከእዚህ በመቀጠል ስለቅዱስ ዮሴፍ ያዘጋጀነውን አስተንትኖ እንደሚከተለው አናቀርበዋለን፣ እንድትከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በዛሬው ዕለት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮዬ የቅዱስ ዮሴፍን ርኅሩህ አባትነት ልዳስሰው እፈልጋለሁ። ኅዳር 29/2013 ዓ. ም. በጻፍኩት ሐዋርያዊ መልእክቴ በቅዱስ ዮሴፍ ባህርይ ላይ ለማሰላሰል እድሉን አገኝቼ ነበር። ቅዱሳን ወንጌላት ቅዱስ ዮሴፍ አባትነቱን እንዴት እንደተጠቀመበት ምንም ዓይነት ዝርዝር መግለጫ ባይሰጡንም “ጻድቅ” ሰው መሆኑን ለኢየሱስ ክርስቶስ በሰጠው ትምህርት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ኢየሱስ በእግዚአብሔር እና በሰው ፊት ሁሉ የተወደደ ሆኖ በጥበብ እና በቁመት እያደገ ይሄድ ነበር (ሉቃ. 2:52)። እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ እንዳደረገው ሁሉ ዮሴፍም ለኢየሱስ እንዲሁ አድርጓል። በእግሮቹ እንዲራመድ አስተማረው፣ ጎንበስ ብሎ ጉንጮቹን እየሳመ በእንክብካቤ እንደሚያድግ ጨቅላ ሕፃን አባት ሆኖ ነበር ያሳደገው (ሆሴዕ 11:3-4)። እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያሳየው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅስ ውብ ነው። በቅዱስ ዮሴፍ እና በኢየሱስ መካከል የነበረው ግንኙነትም ተመሳሳይ ነው ብለን እናስባለን።

ኢየሱስ ስለ እግዚአብሔር እና ስለ ፍቅሩ ሲናገር ሁልጊዜ “አባት” የሚለውን ቃል እንደሚጠቀም ወንጌላት ይመሰክራሉ። በወንጌላት ውስጥ የተጠቀሱ ብዙ ምሳሌዎች እንደ ዋና ገፀ ባህሪያቸው የአባትነት ምስል አላቸው። በጣም ዝነኛ ከሆኑት መካከል አንዱ ወንጌላዊው ሉቃስ የተናገረው የመሐሪ አባት ታሪክ ነው (ሉቃ. 15:11-32)። ይህ ምሳሌ የሚያሳየው የኃጢአት እና የይቅርታ ልምድን ብቻ ሳይሆን ጥፋት ላጠፋው ሰው የይቅርታ መንገድ ላይ የሚደርስበትንም ሁኔታ ጭምር ነው። ጥቅሱም እንዲህ ይላል:- “ስለዚህ ተነስቶ ወደ አባቱ ሄደ። አባቱም ገና በሩቅ ሳለ ልጁን አየው፤ ራርቶለትም ወደ እርሱ ሮጠ፤ እቅፍ አድርጎም ሳመው (ሉቃ. 15:20)። ልጁ ቅጣትን ይጠብቅ ነበር፣ ቢበዛ ፍርዱ የአንድ አገልጋይ ቦታ ሊያሰጠው ይችል ነበር፣ ነገር ግን እራሱን በአባቱ እቅፍ ውስጥ አገኘው። ርህራሄ ዓለም ካለው አስተሳሰብ እጅግ የበለጠ ነገር ነው። ያልተጠበቀ ፍትህ የሚሰጥበት መንገድ ነው። እግዚአብሔር በኃጢአታችን እንደማይደነግጥ መዘንጋት የሌለብን ለዚህ ነው። ይህንን በአዕምሮአችን በደንብ ልንይዘው ይገባል። እግዚአብሔር ከኃጢአታችን ስለሚበልጥ ኃጢአታችንን አይፈራም። እርሱ አፍቃሪ እና ርኅሩኅ አባት ነው። እርሱ በኃጢአታችን እና በስህተታችን አይደነገጥም፤ ነገር ግን የልባችን መዘጋት ያስፈራዋል፣ ያስደነግጠዋል።  አዎ! ይህ ያሰቃየዋል፤ በፍቅሩ ላይ ያለንን እምነት ማጣት ያስፈራዋል። በእግዚአብሔር የፍቅር ልምድ ውስጥ ታላቅ ርኅራኄ አለ። ይህን እውነታ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢየሱስ ያስተላለፈው ዮሴፍ ራሱ ነው ብሎ ማሰብ ጥሩ ነው። ይህን ታሪክ ከዚህ በፊት ነግሬአችሁ ከሆነ አላውቅም። ከረጅም ዓመታት በፊት፣ አንድ የቲያትር ቡድን በመሐሪ አባት ታሪክ ስለተማረከ በዚህ ላይ ተመሥርቶ አንድ ቲያትር ለመሥራት ወሰነ። ተዋናዮቹ የቲያትሩን በሚገባ ሠሩት። ታሪኩም፥ ጓደኛው ከአባቱ የራቀውን ልጅ ሲያዳምጥ የሚያሳይ ነበር። ልጁ ወደ አባቱ ቤት መመለስ ቢፈልግም ነገር ግን አባቱ እንዳይገርፈው ይፈራ ነበር። ጓደኛውም እንዲህ አለው፥ ወደ ቤት መመለስ እንደምትፈልግ መልዕክተኛ ላክበት አለው። አባትህ የሚቀበልህ መሆኑን የምታውቀው መሀረቡን መስኮቱ ላይ ሲሰቅል አንደሆነ አስረዳው። ይህም ተደረገ። ልጁ ወደ ቤቱ በሚወስድ መንገድ ላይ ደርሶ ቤቱን እስኪያይ ድረስ ዘፈኑ እና ዳንሱ ቀጠለ። ልጁም ቀና ብሎ ሲመለከት የቤቱ መስኮቶች በሦስት እና በአራት ነጫጭ መሀረቦች ታስረው ያያቸዋል። የእግዚአብሔርም ምሕረት እንደዚሁ ነው። ባለፈው ሕይወታችን፣ ባደረግነው መጥፎ ነገር ተስፋ አይቆርጥም። ችግሮቻችንን ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም እርሱን ስናወያይ ያቅፈናል፣ ይራራልናል።

ስለዚህ እኛ ይህን የእግዚአብሔር ርኅራኄ ተመልክተን በተራችን ምስክሮቹ ሆነን እንደሆነ ራሳችንን እንጠይቅ።  ርኅራኄ በዋነኛነት ስሜታዊ ጉዳይ አይደለም። ነገር ግን በእኛ ድህነት እና ጉስቁልና ውስጥ በትክክል እንደተወደድን፣ ተቀባይነትን እንዳገኘን እና በእግዚአብሔር መለወጣችንን የመገንዘብ ልምድ ነው።

እግዚአብሔር በጉብዝናችን ብቻ ሳይሆን የተቤዠን ድካማችንም ይመለከታል። ይህ ለምሳሌ፣ ቅዱስ ጳውሎስ የአንድ ሰው ደካማነት እቅድ እንዳለው እንዲናገር ያደርገዋል። እንዲያውም ለቆሮንጦስ ሰዎች እንዲህ ሲል ጽፏል፥ “ከእነዚህ ከተገለጡልኝ ታላላቅ ነገሮች የተነሳ እንዳልታበይ፣ ሥጋዬን እንደ እሾኽ የሚወጋ ስቃይ ተሰጠኝ፤ ይህም የሰይጣን መልዕክተኛ በመሆን እየጎሸመ በማሰቃየት እንዳልታበይ ያደርገኛል። ይህ የሚያሰቃየኝ ነገር ከእኔ እንዲወገድልኝ ጌታን ሦስት ጊዜ ለመንሁት። ነገር ግን እርሱ ‘የእኔ ኃይል የሚገለጠው በአንተ ደካማነት ስለሆነ ጸጋዬ ይበቃሃል አለኝ። ስለዚህ የክርስቶስ ኃይል በእኔ እንዲሆን ከምን ጊዜውም ይልቅ በደካማነቴ ልመካ እወዳለሁ (2ኛ ቆሮ. 12:7-9)። እግዚአብሔር ድክመቶቻችንን በሙሉ ከእኛ አያስወግድም። ነገር ግን በድካማችን ጊዜም ድጋፋችን ይሆንልናል። ድክመቶቻችንን በመቀበል እጃችን ይዞ ከጎናችን ይቆማል፤ ርህራሄ ማለት ይህ ነው።

የእግዚአብሔር ርኅራኄ የሚታወቀው እኛ ድክመቶቻችንን ማሸንፍ ስንችል ነው። “ደካማነታችንን እንድናይ እና እንድንኮንን ከሚያደርግ ከሰይጣን እይታ ወጥተን፣ መንፈስ ቅዱስ በፍቅር ወደ ብርሃን ሲያወጣን ነው። በውስጣችን ያለውን ደካማነት ለመንካት ርኅራኄ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ነው። አንድ ሐኪም የታማሚውን ቁስሎች እንዴት እንደሚነካ አስቡ፥ በደግነት እና የበለጠ እንዳይጎዳ በመጠንቀቅ ነው። እግዚአብሔርም በርኅራኄ ቁስላችንን የሚነካው በተመሳሳይ መንገድ ነው። በምስጢረ ንስሐ በኩል የሚገኝ የእግዚአብሔርን ምህረት የሚያስፈልገን፣ ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት መገናኘት፣ የእርሱን እውነት እና ርኅራኄ ማወቅ በጣም አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው። ሰይጣን ደግሞ በማስመሰል እውነትን ሊናገረን ይችላል። እርሱ ውሸታም እንደሆነ እናውቃለን። ነገር ግን በውሸቱ ነገሮችን ሊያመቻች ይችላል። ይህን የሚያደርገው እኛን ለመኮነን ብቻ ነው። ይልቁንም እግዚአብሔር እውነቱን ይነግረናል። እኛን ለማዳን እጁን ዘርግቷል። የእግዚአብሔር እውነት እንደማይኮንን፣ ይልቁንም በደስታ እንደሚቀበለን፣ እንደሚደግፈን እና ይቅር እንደሚለን እናውቃለን። እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይቅር ባይ ነው። ይህንን በአእምሮአችን እና በልባችን ውስጥ በግልጽ ልናስቀምጥው ይገባል። እግዚአብሔር ሁል ጊዜ ይቅር ይላል። ይቅርታን መጠየቅ የሰለቸን እኛ ነን እንጂ። ክፉዎችንም ሁል ጊዜ ይቅር ይላል።

የእግዚአብሔርን አባትነት ገልጾ ስለሚያሳየን የዮሴፍን አባትነት ማስታወስ መልካም ነው። በእግዚአብሔር ቸርነት መወደድን እንፈቅዳለን ወይ? ብለን ራሳችንን እንጠይቅ። ይህ የዋህነት ከሌለን ለውጥ ማካሄድ ያስፈልገናል! የዋህነት በውስጣችን ከሌለ በቀላሉ እንዳንነሳ በሚያደርገን፣ በመቤዠት እና በቅጣት መካከል ግራ በሚያጋባ ፍትህ ውስጥ የመታሰር አደጋ ላይ እንገኛለን። በዚህ ምክንያት ዛሬ በልዩ ሁኔታ በእስር ላይ የሚገኙትን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ማስታወስ እፈልጋለሁ። በደል የፈጸሙ ሰዎች ለበደላቸው ዋጋ እንዲከፍሉ መደረጋቸው ትክክል ነው። ነገር ግን የበደሉት ሰዎች ከበደላቸው ነጻ መውጣት መቻላቸውም ልክ ነው። የተፈረደባቸው ሰዎች ያለ ተስፋ መቀመጥ አይችሉም። ማንኛውም ዓይነት ፍርድ ሁል ጊዜ የተስፋ መስኮት ሊኖረው ይገባል። በእስር ላይ ለሚገኙትን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የእግዚአብሔርን ርህራሄ እናስብላቸው። የተሻለ ሕይወት የሚጀምሩበትን መንገድ እንዲያገኙ እንጸልይላቸው።”

የዕለቱን አስተምህሮ በዚህ ጸሎት እናጠቃልላለን፡-

እጅግ ርኅሩኅ ዮሴፍ ሆይ!

በውስጣችን ካለው ደካማነታችን ጋር መወደዳችንን እንድንቀበል አስተምረን።

በድህነታችን እና በእግዚአብሔር ፍቅር መካከል እንቅፋት እንዳንፈጥር አግዘን።

ይቅር እንድንባባል እና በድህነት ሕይወት ውስጥ የሚገኙ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ማፍቅር እንድንችል ወደ እግዚአብሔር ምሕረት የመቅረብ ፍላጎት በልባችን አሳድርልን።

ለሠሩት ጥፋት ቅጣትን በመቀበል ላይ ካሉት ጋር ሁን።

አዲስ ሕይወት መጀመር እንዲችሉ ፍትህን ብቻ ሳይሆን ርህራሄንም እንዲያገኙ እርዳቸው።

ይህን ለመጀመር ቀዳሚው መንገድ ቅንነት፣ ይቅርታ መጠየቅ እና የእግዚአብሔርን እንክብካቤ መረዳት መሆኑን አስተምራቸው።

አሜን።

 

20 March 2023, 10:14