ፈልግ

2023.03.01 Logo dell'assemblea continentale sinodale dell'Africa Addis Ababa Etiopia

ሲኖዶሳዊነት በቤተክርስቲያን ሕይወት እና ተልዕኮ ውስጥ

በሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ ማግስ ላይ ያጠላው አዲስ ገደብ

ክፍል ሁለት

8.    በሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ ላይ የቤተክርስቲያንን ሕብረት በተመለከተ ኤጲስ ቆጶሳት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በጋራ እና በትብብር የመወጣት አስተሳሰብን እና 'ሲኖዶሳዊ' ተግባርን ለማስተዋወቅ ቃል የገባላቸው የእድሳት ፍሬዎች አንጡራ ሀብት እና ውድ ነበሩ። ጉባሄው በወቅቱ ባወጣው ፎንተ ካርታ ላይ ግን ገና ብዙ ይቀረው ነበር። በእርግጥ ዛሬ ለሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያን ተስማሚ ቅርጽ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት - ምንም እንኳን በሰፊው የሚካፈለው እና በአዎንታዊ መልኩ በተግባር ላይ የዋለ ቢሆንም - ግልጽ የሆኑ ሥነ-መለኮታዊ መርኾችን እና ቆራጥ የሐዋርያዊ አገልግሎት አቅጣጫዎች የሚያስፈልገው ይመስላል።

9      ለዚህም ነው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ እንድንሻገር የጋበዙን አዲሱ ገደብ የሆነው። የሁለተኛውን ቫቲካን ጉባሄ ተከትሎ፣ የቀደሙትን ፈለግ በመከተል፣ ሲኖዶሳዊውነት ከኢየሱስ ወንጌል የሚወጣውን፣ በታሪክ ውስጥ ሥጋ ለመልበስ ከተጠራው፣ ለትውፊት ባለው ታማኝነት በቤተክርስቲያንን ቅርፅ እንደሚገልጽ አጥብቆ ተናግሯል።

በላቲን ቋንቋ “Lumen Gentium” (የሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ፣ ስለቤተክርስቲያን ቀኖናዊ አቋም የተመለከተ ሰነድ) አስተምህሮ ጋር በተጣጣመ መልኩ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተለይ ሲኖዶሳዊነት “የተዋረድ አገልግሎትን እንድንረዳ በጣም ተስማሚ የሆነ ማዕቀፍ ይሰጠናል” እናም የምእመናን እምነት ስሜት አስተምህሮ ላይ በመመስረት፣ ሁሉም የቤተክርስቲያኗ አባላት የስብከተ ወንጌል ወኪሎች ናቸው፣ ስለዚህ የሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያንን እውን ማድረግ መላውን የእግዚአብሔርን ሕዝብ የሚያሳትፍ አዲስ ሚስዮናዊ ኃይል ለማግኘት በጣም አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ ነው የሚሉት።

በተጨማሪም ሲኖዶሳዊነት የክርስቲያኖች ልዩ ቁርጠኝነት እምብርት ነው፣ ምክንያቱም ወደ ሙሉ ኅብረት በሚወስደው መንገድ ላይ አብረን እንድንጓዝ የሚጠራንን ግብዣን ስለሚወክል እና በትክክል ስንረዳ - ትክክለኛ ልዩነቶች ያሉባትን ቤተክርስቲያንን የመረዳት እና የመለማመድ ዘዴን ይሰጣል ። ልዩ ልዩ ለሆኑ የፀጋ ስጦታዎች በእውነት ውስጥ ቦታ ማግኘት እንዳለብን ያስገነዝበናል።

የሰነዱ ዓላማ እና መዋቅር

10    ይህ ሰነድ በመጀመርያዎቹ ሁለት ምዕራፎች ውስጥ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉብሄ  አስተምህሮ ጋር በሚስማማ መልኩ ወደ ሲኖዶሳዊነት ሥነ-መለኮታዊ ትርጉም ከካቶሊክ የቤተክርስቲያን ጥናት አስተምህሮ መስመር ጋር በጥልቀት የመግባትን አስፈላጊነት ላይ ምላሽ ይሰጣል። ወደ መጀመሪያው የቅዱሳት መጻሕፍትና ትውፊት ምንጮች ተመልሰን የቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ምስል ከሥሩ የመነጨው ራዕይ በታሪክ ውስጥ በተገለጠው መንገድ እንዴት እንደሆነ ለማብራራት እና ጽንሰ-ሐሳቡን የሚገልጹትን መሠረታዊ ፍችዎች እና ልዩ ሥነ-መለኮታዊ መመዘኛዎችን ለመጠቆም እና እንዴት በተግባር ላይ ሊውል እንደሚችል ያመላክታሉ።

ሁለተኛው ምዕራፍ የሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ ከቤተክርስቲያን አስተምህሮ ጋር በተጣጣመ መልኩ የሲኖዶሳዊነት ሥነ-መለኮታዊ መሠረቶችን ያስቀምጣል፣ ይህም ከምእመናን እና ከሚስዮናውያን የእግዚአብሔር ሰዎች እይታ እና ከቤተክርስቲያን ምሥጢራት ጋር በማያያዝ፣ ከቤተክርስቲያን ልዩ ባህሪያት ጋር በማዛመድ፣ አንድነት፣ ቅድስና፣ ካቶሊካዊነት እና ሐዋርያዊነት ምን እንደ ሆኑ ያስረዳል። በመጨረሻም ሁሉም የሕዝበ እግዚአብሔር አባላት በቤተክርስቲያኗ ተልዕኮ ውስጥ በሚያደርጉት ተሳትፎ እና በመጋቢዎቻቸው ስልጣን አጠቃቀም መካከል ያለውን ግንኙነት ይመለከታል።

በዚህ መሠረት፣ ሦስተኛው እና አራተኛው ምዕራፎች አንዳንድ የሐዋርያዊ ተግባራት አቅጣጫዎችን ለመጠቆም የታሰቡ ናቸው፡- ሦስተኛው ምዕራፍ ‘ሲኖዶሳዊነት እንዲፈጸም ማድረግ’ የሚለውን ተግባራዊ ጥያቄ በሁሉም ደረጃ፣ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን፣ በአንድ ክልል ውስጥ ባሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ስላለው ግንኙነት እና ከአለም አቀፋዊቷ ቤተ ክርስቲያን ጋር ስላለው ተዋረዳዊ ግንኙነት የሚገልጽ እና የምያብራራ ሲሆን አራተኛው ምዕራፍ ደግሞ የሚያመለክተው መንፈሳዊ እና ሐዋርያዊ ተግባራት መንፈሳዊ ለውጥ ማስገኘት የሚችሉበትን እና ለእውነተኛ የቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ልምድ አስፈላጊ የሆኑትን የጋራ እና ሐዋርያዊ አስተውሎን የሚገልጽ ነው ፣ ይህም በቤተክርስቲያን እና በማሕበራዊ አገልግሎት ላይ ስላለው አወንታዊ ተጽእኖ በማድነቅ የተገለጸ ነው።

ምዕራፍ አንድ

ሲኖዶሳዊነት በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በትፊት እና በታሪክ ውስጥ

11      የቤተክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ሕይወት በቅዱሳት መጻሕፍት እና በትውፊት ውስጥ የሚገኙት መደበኛ ምንጮች እንደሚያሳዩት ከሆነ በእግዚአብሔር የማዳን ዕቅድ ልብ ውስጥ የሰው ዘር በሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት እንዲኖረን እና በእርሱም አንድነት እንዲመጣ በኢየሱስ ክርስቶስ እና በአገልግሎት የተገኘው የቤተክርስቲያን ጥሪ የሚያመልክት ነው። የሲኖዶሳዊ ህይወትን፣ አወቃቀሮችን፣ ሂደቶቹን እና የሚያካትታቸው ክስተቶችን የሚያንቀሳቅሱ እና የሚቆጣጠሩትን የስነ-መለኮት መርኾችን ለመለየት የሚያስፈልገንን መመሪያ ይሰጣሉ። በዚህ መሠረት በአንደኛው ሚሌኒዬም ውስጥ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ የተገነቡትን የሲኖዶሳዊ ሥርዓቶችን እና ከዚያም በሁለተኛው ሚሊኒየም ውስጥ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና የቤተክርስቲያን ማህበረሰቦች ሲኖዶሳዊ አሠራር አንዳንድ ገጽታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት መፈለግ ይቻላል።

የቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ

12    ብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ሰውን ወንድና ሴት አድርጎ በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረው ኅብረተሰባዊ ፍጡር አድርጎ በኅብረት ምልክት ወደ ፊት በመጓዝ፣ አጽናፈ ዓለሙን በመንከባከብና ወደ ውስጡ እንዲመራው አድርጎ እንደፈጠረ የሚገልጸውን ግብ ያሳያል (ዘፍጥረት 1፡26-28)። ከመጀመሪያው ጀምሮ ኃጢያት የእግዚአብሔርን እቅድ ያሰናክላል፣ እውነትን፣ መልካምነትን እና የፍጥረትን ውበት የሚገልፅ የታዘዙ ግንኙነቶችን መረብ ይበጣጠሳል፣ እናም ወንዶች እና ሴቶች የተሰጣቸውን የጥሪ ልብ አሳወረ።  እግዚአብሔር ግን በምሕረት ባለ ጠጋ ሆኖ የተበተነውን ሁሉ ወደ አንድነት ጎዳና ለመመለስ ቃል ኪዳኑን አረጋግጦ ያድሳል፣ የሰውን ነፃነት ፈውሶ ከእግዚአብሔር ጋር የመዋሐድን፣ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር አንድነት እንዲኖረን ወደ ፍጥረት ማለትም የጋራ ቤታችን እየመራ ነው (ለምሳሌ ዘፍጥረት 9፣8-17፣ 15፣ 17፣ ዘጸአት 19-24፣ 2 ሳሙኤል 7፣11 መመልከት ይቻላል)።

13    እቅዱን ሲፈጽም እግዚአብሔር አብርሃምንና ዘሩን ጠራ (ዘፍጥረት 12፣1-3፤ 17፣1-5፤ 22፣16-18)። ይህ ጉባኤ በእብራይስጥ ቋንቋ “קָחַל/עֵדה” (ኃይል) በማለት መተርጎ የሚችላ ሲሆን የመጀመሪያው ቃል ብዙውን ጊዜ ወደ ግሪክ ቋንቋ “έκκλησία” ኤክሌዚያ (ቤተክርስቲያን) ተብሎ ይተረጎማል)፣ በሲና ተራራ ላይ በተደረገው ቃል ኪዳን የጸደቀው (ዘጸአት 24፣6-8፤ 34፣20) ከባርነት ነፃ የወጡትን ሰዎች አስፈላጊ እና እግዚአብሔርን የመናገር መብት ሰጥቶ ብቁ ያደርጋቸዋል።  በስደት ጉዞ አምላካቸው ዙሪያ ተሰብስበው አምልኮቱን ለማክበር እና የእርሱ ብቻ መሆናቸውን አውቀው በህጉ ይኖራሉ (ዘዳ. 5፣1-22፣ ኢያሱ 8፣ ነህምያ 8፣1-18)።

“qahal /'edah” የተሰኘው የእብራይስጥ ቃል የእግዚአብሔር ሕዝብ ሲኖዶሳዊ ጥሪ የሚገለጥበት የመጀመሪያው መልክ ነው። በምድረ በዳ፣ እግዚአብሔር የእስራኤላውያን ነገዶች የሕዝብ ቆጠራ እንዲደረግ  ያዛል፣ ለእያንዳንዱም ቦታ ይሰጣል (ዘኁ. 1-2)። በጉባኤው መሃል፣ ብቸኛ መሪ እና እረኛ የሆነው በሙሴ አገልግሎት የሚገኘው ጌታ ነው (ዘኁ. 12፤ 15-16፤ ኢያሱ 8፣30-35)፣ ሌሎችም በየደረጃቸው እና በመተባበር  እንዲሰሩ መንገድ ይከፍታል፣ መሳፍንት (ዘጸአት 18፣25-26)፣ ሽማግሌዎች (ዘኍልቍ 11፣16-17.24-30) እና ሌዋውያን (ዘኍልቍ 1፣50-51)። የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ ወንዶችን ብቻ ያቀፈ አልነበረም (ዘጸአት 24፣7-8) ነገር ግን ሴቶችንና ሕጻናትን አልፎ ተርፎም የውጭ አገር ማለትም የሌላ አገር ሰዎችን ያቀፈ ነበር (ኢያሱ 8፣33.35)። እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ባደሰ ቁጥር ከሕዝቡ ጋር ይነጋገር ነበር (ዘዳ. 27-28፤ ኢያሱ 24፤ 2 ነገሥት 23፤ ነህምያ 8)።

14    የነቢያት መልእክት የእግዚአብሔር ሕዝብ በታሪክ መከራ ውስጥ ለቃል ኪዳኑ ታማኝ በመሆን መጓዝ እንደሚያስፈልግ ያስተምራል። ለዚህም ነው ነቢያት ከባልንጀራዎቻቸው፣ ብዙ ጊዜ ድሆች፣ ጭቁኖች፣ መጻተኞች፣ የእግዚአብሔር ምሕረት ተጨባጭ ምስክር እንዲሆኑ ልባቸውን ወደ እግዚአብሔር እንዲመልሱ እና ወደ ፍትህ እንዲሰጡ ይጋብዟቸዋል (ኤርምያስ 37፣21፤ 38፣ 1)።

ያ እንዲሆን፣ እግዚአብሔር አዲስ ልብና መንፈስ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል (ሕዝ. 11፣10)፣ እና በህዝቡ ፊት አዲስ የመውጫ መንገድ ከፈተላቸው (ኤርምያስ 37-38)፡ ከዚያም ይነሳል አዲስ ቃል ኪዳን ይሰጣቸዋል፣ ከእንግዲህ በድንጋይ ጽላቶች ላይ ሳይሆን በልባቸው የተቀረጸ (ኤርምያስ 31፣31-34) ቃል ኪዳን ይሰጣቸዋል። የጌታ አገልጋይ አሕዛብን ስለሚሰበስብ (ኢሳ. 53)፣ እና በሁሉም የሕዝቡ አባላት ላይ በጌታ መንፈስ መፍሰስ ይታተማል (ኢዩኤል 3፡1-4)።

15    እግዚአብሔር በመሲሕና እና ጌታ በሆነው በናዝሬቱ ኢየሱስ የገባውን አዲስ ቃል ኪዳን ፈፅሟል። እግዚአብሔር አምላክ በጸጋውና በምሕረቱ መላውን የሰው ልጅ በአንድነት ሊያቅፍ የሚፈልግ የፍቅር ማኅበር መሆኑን የሚገልጥ ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፣ የአብን ልብ ለመውደድ ከዘለአለም ጀምሮ ተወስኗል (ዮሐ. 1፣1.18)፣ ሰውን በዘመኑ ፍጻሜ (ዮሐ. 1፣14፤ ገላትያ 4፣4) የእግዚአብሄርን እቅድ ፍጻሜ ለማድረግ የመዳን ግብ (ዮሐንስ 8፣29፤ 6፣39፤ 5፣22.27)። ብቻውን አይሠራም፣ በሁሉም የአብን ፈቃድ ያደርጋል፡ አብ በእርሱ ይኖራል ወደ ዓለም በላከው በልጁም ሥራውን ይፈጽማል (ዮሐ. 14፣10)።

የአብ እቅድ ፍጻሜውን ያገኘው በፋሲካ ምሥጢር ነው፣ ኢየሱስ ሕይወቱን በሰጠ ጊዜ እና በትንሣኤ ዳግመኛ መልሶ ለማግኘት እንደ ቻለ (ዮሐ. 10፣17) እና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደ ወንድና ሴት ልጆች፣ እህቶች እና ወንድሞች “ያለ ምንም ሥሥት” መንፈስ ቅዱስ በሚፈስበት ጊዜ ለመካፈል ነው (ዮሐንስ 3፣34)። የፋሲካ ምሥጢር በጥምቀትና በቅዱስ ቁርባን ራሱን የሚመስለው በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ በአንድነት የሚሰበስብ አዲስ መውጣት ነው። የማዳን ሥራ ኢየሱስ ከሕማማቱ በፊት አብን የተማፀነበት አንድነት ነው፡- “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ አባት ሆይ አንተ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ እንዳለሁ እነርሱም ደግሞ በእኛ ውስጥ ይሆኑ ዘንድ። አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ” (ዮሐ. 17፣21) በማለት እንደ ገለጸው ነው።

ምንጭ፡ የካቶሊክ ዓለም አቀፍ የነገረ መለኮት ኮሚሽን፣ ሲኖዶሳዊነት በቤተክርስቲያን ሕይወት እና ተልዕኮ ውስጥ በሚል አርእስ ይፋ ካደርገው ሰነድ ከአንቀጽ 8-15 ላይ የተወሰደ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ይህንን ዝግጅት በድምጽ ለማዳመጥ ተጫወት የሚለውን ምልክት ይጫኑ
20 March 2023, 15:29