ፈልግ

2018.12.30 festa della sacra Famiglia, festività santa famiglia, Gesù, Giuseppe e Maria

ቅዱስ ዮሴፍ

እናታችን ቅድስት ቤተክርስቲያን ከእመቤታችን ቅድስት ማርያም ቀጥላ ቅዱስ ዮሴፍን ከመላእክትና ከቅዱሳን አብልጣ ታከብራለች፡፡ ጸሎቷንም ከእመቤታችን ማርያም ቀጥላ ወደ ቅዱስ ዮሴፍ በአማላጅነት እንዲያግዛት ትጠራለች፡፡ ይህን ቅዱስ ከመላእክትና ከቅዱሳን ከፍ የሚያደርገው ቅድስናው ወይም ተአምራቱ አይደለም የእመቤታችን ጠባቂና የኢየሱስ ደግሞ መንፈሳዊ አባት በመሆኑ ነው።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

አንድ ዝነኛ ሰባኪሐ የመቄዶንያ ንጉሥ ፈሊጶስን በዘሩ ትልቅነት፣ በሞያው፣ በሀብቱ፣ በድል አድራጊነቱ ካሞገሰው በኋላ «ይህ ታዲያ ዓለምን ሁሉ የገዛ ንጉሥ የታላቁ እስክንድር አባት መሆኑ ነው´ በማለት ንግግሩን ጨረሰ፡፡ ቅዱስ ዮሴፍም እንደዚሁ በትሕትናው፣ በንጽሕናው፣ በየዋህነቱና በተጋድሎው … ትልቅ ቢሆንም ዋናው የቅድስናው ትልቅነት ግን ቀደም ብለን እንዳልነው የእመቤታችን ማርያም ጠባቂና የኢየሱስ መንፈሳዊ አባት መሆኑ ነው፡፡

መላእክትና ቅዱሳን ለማርያምና ለኢየሱስ ይታዘዛሉ፤ ያከብሯቸውል፡፡፡ ቅድስ ዮሴፍ ግን የቤተሰቡ የበላይ እንደ መሆኑ መጠን ኢየሱስና ማርያምን ያዛቸው ነበር፤ ሁሉም ከበታቹ ሆነው ለቅዱስ ዮሴፍ ይላላኩና ያከብሩት ነበር፡፡ በዚህ ከፍ ያለ ኃላፊነቱ ቤተክርስቲያን በታላቅ ሁኔታ በዓመት ሁለት ጊዜ ታከብረዋለች፡፡ በምድር በነበረበትም ጊዜ ኢየሱስና ማርያምን እንደ ጠበቃቸው እንዲሁ ደግሞ አሁን በሰማይ ሆኖ ቅድስት ቤተክርስቲያን ጠባቂዋ እንዲሆን መረጠችው፡፡ ቤተክርስቲያን ይህን ኃላፊነት ለቅዱስ ዮሴፍ ብቻ እንጂ ለሌላ ቅዱስ ወይም ለአንድ መልአክ አልሰጠችውም፡፡

የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ከማንኛውም ሰው ልቆ በሥልጣን ከፈርዖን በታች ሆኖ የግብፅ አስተዳዳሪ የሆነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው (ዘፍ. 41)፡፡ እንዲሁም ቅዱስ ዮሴፍ ከተራ ሰውነት  (ከጠራቢነት) ከፍ ብሎ የመላእክትና የቅዱሳን የበላይ ሊሆን የቻለው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ ፈርዖን ለዮሴፍ ሥልጣን በመስጠት የግብፅ አስተዳዳሪ አድርጐ እንደ አከበረው እንዲሁ እግዚአብሔር ደግሞ ለዳግማዊ ዮሴፍ የማርያም እጮኛና የኢየሱስ አባት እንዲሆን ከመምረጡ በፊት ልዩ ጸጋና የቅድስና ማዕረግ ሰጠው፡፡ ለአብነታችን እንዲሆን አስቀድመን ቅድስናውን እንመልከት፡፡

የዮሴፍ ቅድስና፣ በወንጌል ውስጥ ስለ ቅዱስ ዮሴፍ ታሪክ የምናገኘው እጅግ በጣም ጥቂት ነው፡፡ የማቴዎስ ወንጌል ብቻ «ጻድቅ ነው” (ማቴ. 1፣49) ብሎ ይጠራዋል፡፡ እንደ ቅዱስ ሄሮኒሞስ ሐሳብ ይህ ቃል የቅዱስ ዮሴፍን ቅድስና ሁሉ ይገልጽልናለ፡፡ ታላቅ ቅዱስ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ በዚህ ተመርኩዛ ቤተክርሰቲያን «ፍጹም ጻድቅ ዮሴፍ ሆይ” እያለች ትለምነዋለች፡፡ ብናስተውለው የእግዚአብሔር ልጅና የአምላክ እናት ለማስተዳደርና ለመጠበቅ የተመረጠ እንዴት ብሎ ከፍ ያለ ቅድስና የሌለው ሊሆን ይችላል፤ ትሕትናው፣ ትዕግሥቱ፣ ንጽሕናው፣ ድኻነቱ፣ ተጋድሎውን ማን ሊያውቀው ይችላል፣ በእርሱ የነበረ የእግዚአብሔር ፍቅር፣ የመታዘዝ መንፈስ እና ጸሎት፣ ትሕትናው …. የሚደንቅ ነው። ቅዱስ ዮሴፍ የጥሞና እና የሥራ ወዳጅ ነበር። ፈቃዱ የእግዚአብሔር ፈቃድ፣ የሕይወቱ ሐሳብ ለአምላኩ ማገልገለ ብቻ ነበር፡፡ እርሱ በቅድስና ኑሮ በኢየሱስና በማርያም እጅ በሰላም አረፈ፡፡ እንግዲህ ቅድስናውን ከተመለከትን አብነቱን እንከተል፤ በትሕትና በጸሎት፣ በንጽሕና በአምላክ ፍቅር እርሱን እንምሰል፤ እንደ እርሱ የተጋድሎ፣ የድኸነት፣ የትዕግሥት፣ የጥሞናና የሥራ ወዳጆች እንሁን።

ችሎታው ትልቅ ከሆነው ጠባቂያችን አማላጅነትን እንጠቀምበት። ቤተክርስቲያን ጠባቂዋ እንዲሆን እንደመረጠችው እኛም ደግሞ የእኛ ልዩ ጠባቂና ረዳት እንዲሆነን እንምረጠው፡፡ ሥልጣኑ ትልቅ ነው ሁሉን የሚችል የኢየሱስ አባት ነው፡፡ በምድር ሳለ ለኢየሱስ ሁሉን ያደርግለት እንደነበር አሁን ደግሞ በሰማይ ኢየሱስ ለዚህ መንፈሳዊ አባቱ የሚለውን ሁሉ ያደርግለታለ፤ ልመናውን ይሰማለታል። በግብፅ አገር ረሃብ በገባ ጊዜ ንጉሥ ፈርዖን ግብፃውያን እህል ፈልገው ወደ እርሱ ሲመጡ «ወደ ዮሴፍ ሂዱ” ይላቸው ነበር፡፡ የሚፈልጉትን ከዮሴፍ እንዲጠይቁ ይፈልግ ነበር፡፡ እዲሁ ኢየሱስ እኛን «በዮስፍ አባቱ በኩል ለምኑኝ፤ በእርሱ ወደ እኔ ኑ” እያለ የቅዱስ ዮሴፍን አማላጅነት እንድንለምንና ወደ እርሱ እንድንጠጋ ይፈልጋል፡፡

እናታችን ቤተክርስቲያን ቅዱስ ዮሴፍን ጠባቂዋ አድርጋ የመረጠችው በችግርዋ እርዳታውን ስላገኘች ነው። ታላቋ ቅድሰት ቴሬዛ «እኔ ቅዱስ ዮስፍን ለምኜው ያላደረገልኝ ነገር የለም፤ ብዙዎችም ለምነው ዕርዳታውን ያላገኙ አልሰማሁም´” ትላለች፡፡ ይህንን የቅዱሳንንና የቤተክርስቲያንን ፈለግ በመከተል እንጠቀምበት፡፡ ጭንቀታችንን ተረድተን በሙሉ እምነት ወደ ቅዱስ ዮሴፍ እንጠጋ፡፡ በልባችን እናክብረው፣ ዕርዳታውን ሁል ጊዜ በተለይም በችግራችን ጊዜ እንለምነው። እንግዲህ በጽድቅ ኑረን በኢየሱስና በማርያም እጅ በመልካም እናርፍ ዘንድ እንዲያማልደን አንለምነው፡፡

 

20 March 2023, 10:37