ፈልግ

በደቡባዊ ማላዊ ዕርዳታው የደረሳቸው የአደጋው ተጠቂዎች በደቡባዊ ማላዊ ዕርዳታው የደረሳቸው የአደጋው ተጠቂዎች   (2010)

ኢየሱሳውያን በማላዊ በአውሎ ንፋስ የተጎዱትን ለመደገፍ በሚደረገው ጥረቶች እየተሳተፉ ነው

እ. ኤ. አ. መጋቢት 12 በደቡባዊ ማላዊ ፥ ፍሬዲ በተባለው አውሎነፋስ በደረሰው አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ማሻቀቡን ቀጥሏል። እስከ ባለፈው ሰኞ ድረስ የሟቾች ቁጥር 447 ሲደርስ ፥ ወደ 300 የሚጠጉ ሰዎች አሁንም ድረስ አልተገኙም ፤ 350,000 የሚጠጉ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ላይ ተፈናቅለዋል። በመሆኑም የጄሱሳዊያን የስነ-ምህዳር እና ልማት ማእከል ፥ የድጋፍ እና አደጋን የመከላከል ሥራ እንዲሰራ ጥሪውን እያደረገ ይገኛል። ፍሬዲ የተባለው አዉሎ ንፋስ ደቡባዊ የአፍሪካ ሃገራትን በመምታቱ ምክንያት በተከሰተው የመሬት መደርመስ እና የጎርፍ አደጋን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል፣ ቤትና የእርሻ መሬቶች ወድሟል ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ተፈናቅለዋል ተብሏል ፥በዚህም የተነሳ የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተነግሯል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ - አዲስ አበባ

ከሁሉም በላይ በአውሎ ንፋሱ በጣም በተጠቃችው ሀገር ማላዊ ፥መንደሮች በሙሉ ወድመዋል ፥ በመሆኑም የአከባቢው ማህበረሰብ በየትምህርት ቤቶች እና በካምፖች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ። የቤተክርስቲያን የዕርዳታ ድርጅቶችን ጨምሮ የሰብአዊ እርዳታ ሰጪዎች በአደጋው ምክንያት ሁሉን ነገር ላጡ ሰዎች እገዛ እያደረጉ ይገኛሉ።

ማርታ ፋሪ በማላዊ ዋና ከተማ ፥ ሊሎንግዌ የሚገኘው የኢየሱሳውያን ማኅበር የስነ-ምህዳር እና ልማት ማእከል ፥ የፖሊሲ ተመራማሪ እና ተሟጋች ባለሙያ ነች። እሷ በምትመራው ቡድን እና ከካሪታስ ማላዊ ጋር በመተባበር የህዝቡን አስቸኳይ ፍላጎት ለመገምገም እና አስቸኳይ እርዳታ ለመስጠት ፥ ያደረጉትን የአብሮነት ጉብኝት ለቫቲካን ረዲዮ አስረድተዋል። በአደጋ ለተጎዱ ወገኖች የስነ ልቦና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጻ በባለሥልጣናት በኩል የተሻለ የአደጋ ቅድመ ዝግጅትና መከላከል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ማርታ እንዳብራራችው፥ በኢየሱሳውያን ማኅበር የሚተዳደረው JCED የተባለው ድርጅት ፥ በገጠር እና የተገለሉ ማህበረሰቦች ውስጥ በጣም የተጎዱ እና ተጋላጭ የሆኑት ላይ በማነጣጠር የማቋቋም ፣ አቅም ግንባታ ሥራ፣ የማላመድ እና ፍትሃዊ አየር ንብረት አጠቃቀም ላይ የተሰማራ ድርጅት ነው። ‘ይሄን ሥራ እንድንሰራ ያነሳሳን ትልቁ ነገር’ ትላለች ማርታ ፥ ‘ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በባለፈው አስተምህሮዋቸው ውስጥ የድሆችን ጩኸት እና የምድራችንን ጩኸት እንድንሰማ የጋበዙን ትምህርት ነው። በመሆኑም መስማት ብቻ ሳይሆን እርምጃ መውሰድም ይገባል ትላለች ማርታ።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ቅርበት

ማርታ ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ባለፈው ረቡዕ ዕለት ያደረጉትን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ፥ በተፈጥሮ አደጋው እና በአውሎ ነፋሱ ለተጎዱት ሁሉ ያላቸውን ቅርበት የገለጹትን በማመልከት ፥ ንግግራቸው ለማላዊ ሕዝብ በተለይ ደግሞ በአብያተ ክርስቲያናት በኩል የተላለፈ ነው ብላለች።

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቃላቶች አስፈላጊ ናቸው ፥ ጳጳሱ ከእኛ ጋር ሲሆኑ ፣ ከእኛ ጋር ሲጓዙ እና ለእኛ ተስፋ ሊሰጡን ሲሞክሩ ማየት በጣም የሚያጽናና ነገር ነው ብላ አክላለች። ማርታ አሁን ባደረገችው የአብሮነት ጉብኝት ወደ ደቡባዊው አከባቢ እና በጣም በተጎዱ የሀገሪቱ ክፍሎች፣ ቡድኑን በተበላሹ የማላዊ መንገዶች እንዴት እንደወሰደች እና በሺዎች ከሚቆጠሩ በመጠልያ ካምፖች ውስጥ የተሰበሰቡ ሰዎችን ለማግኘት እንዴት አስቸጋሪ ጉዞ እንዳደረጉም አብራርታለች። በመሬት ላይ ያለው ሁኔታ በጣም በጣም አስከፊ ነው ፤ በማላዊ ውስጥ ትርምስ አለ ፥ እጅግ በጣም ብዙ የተፈናቀሉ ሰዎች ያሉበት የመጠልያ ማዕከላት እና ጊዜያዊ ካምፖች አሉን። ብዙ የመጠልያ ማእከላት ትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዳሉ እና ይህም በመሆኑ ምክንያት ትምህርት ቤቶች ዝግ መሆናቸውን ገልጻለች።

የኢየሱሳውያን ማኅበር እና የካሪታስ ማላዊ አባላትን ያቀፈው ቡድን በአውሎ ነፋሱ ከተጎዱ አካባቢዎች ከመጡ አንዳንድ የካቶሊክ ጳጳሳት ጋር በመገናኘት የአብሮነት እና የመቀራረብ ምልክትን አሳይተዋል። በጉብኝታቸው ወቅትም ምግብ እና ሌሎች እንደ ልብስ፣ ጫማ፣ ብርድ ልብስ እና ባልዲ የመሳሰሉ ቁሳቁሶችን ማቅረብ ችለዋል።

ተስፋ አስቆርጭ ሁኔታ

“እነዚህ ሰዎች ምንም ተስፋ የላቸውም ፥ ሁሉም ነገር ተጠርጎ ተወስዷል ፥ ሁሉንም ነገር አጥተዋል ምንም ሳይዙ ወደ መጠልያ ማዕከላት ደርሰዋል” ስትል ተናግራለች ማርታ። ከመሠረታዊ ፍላጎቶች እጦት በተጨማሪ ማርታን በጣም ያስደነገጠው ምንም ነገር የሌላቸው ሰዎች ተስፋ መቁረጥ ነበር። ‘በካምፑ ውስጥ በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ነው ያለው ፥ እዚያ በነበርኩበት ጊዜ ህጻናት ወላጆቻቸው የት እንዳሉ ሳያውቁ ፣ ወላጆቻቸው እንደሌሉ ሳይነገራቸው ተስፋ ሳይቆርጡ ሲያለቅሱ አይቻለሁ’ ትላለች።

እነዚህን ሰዎች ቁሳዊ ፍላጎቶቻቸውን ብቻ ሳይሆን “የስነ ልቦና ጉዳት ስለደረሰባቸው ፥ ከዚህም እንዲፈወሱ መርዳትን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፥ እንዴት በተሻለ መንገድ መጓዝ እንዳለብን ልንገነዘበው ይገባል ስትል ተናግራለች። "እነዚህ ሰዎች ከሥነ ልቦና አንፃር መፈወስ አለባቸው." ትላለች ማርታ። ምንም እንኳን ማላዊ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለሚደርሱ የተፈጥሮ አደጋዎች አዲስ ባትሆንም ፥ እንደ ብላንታይር ባለ ትልቅ ከተማ ፥ ይህን ያህል ውድመት እና ጉዳት ይደርስባታል ብሎ የጠበቀ አልነበረም።

ለአደጋ ዝግጁነት

ከዚህ በዘለለ ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈሉ ያሉ ድሆች በሚኖሩባት ሀገር ፥ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነትን ማሳደግ ስለሚያስፈልግበት ሁኔታ ማርታ አስተያየቷን ገልጻለች። "እየሆነ ያለውን ነገር በትክክል ማወቅ አለብን ፥ እንደ ሀገር ወደፊት እንደዚህ አይነት አሳዛኝ ሁኔታዎች እንዳይከሰቱ ለማድረግ ፥ ከአደጋ ዝግጁነት አንፃር የተሻለ መስራት እንደሚገባን አስባለሁ ፥ ይህን ስናረግ ምንም እንኳን የተፈጥሮ አደጋ ቢሆንም፥ ምናልባት ተጽኖው የዚህን ያህል ትልቅ ላይሆን ይችላል” ብላ ሃሳቧን ደምድማለች ማርታ።

 

         

22 March 2023, 17:19