ፈልግ

አባ ኦሮባቶር፣ በአህጉራዊ ምዕራፍ ሲኖዶሳዊነት ሰነድ ላይ ያስተነተኑትን ለስብሰባው ሲካፍሉ አባ ኦሮባቶር፣ በአህጉራዊ ምዕራፍ ሲኖዶሳዊነት ሰነድ ላይ ያስተነተኑትን ለስብሰባው ሲካፍሉ 

“የምዕመናንዋን ድምጽ የምታዳምጥ ቤተ ክርስቲያን፣ ለእህቶች እና ለወንድሞች የጋራ መኖሪያቸው ናት”

በአዲስ አበባ ከየካቲት 22/2015 ዓ. ም. ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአህጉራዊ ምዕራፍ የሲኖዶሳዊነት ስብሰባ ሁለተኛ ቀኑን በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በመጀመር ከቀደመው ቀን ያገኛቸውን ልምዶች መሠረት በማድረግ ውይይት አካሂዷል። በአህጉራዊ ምዕራፍ የተግባር ሰነድ ላይ ያስተነተኑት፣ የአፍሪካ እና ማዳጋስካር የኢየሱሳውያን ማኅበር ፕሬዚደንት እና የነገረ መለኮት ሊቅ አባ ኦሮባቶር ለስብሰባው ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር፥ በሲኖዶሳዊ ሂደት ላይ እርስ በእርስ መደማመጥ ማለት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደተዘነጉ የሚሰማቸው እህቶች እና ወንድሞች፣ ከስሜቱ ወጥተው በኅብረት የሚኖሩባት ቤተ ክርስቲያንን የሚያመለክት መሆኑን አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አባ ኦሮባቶር በመቀጠል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተረሱትን በማስመልከት ሲናገሩ፣ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሥልጣን ተዋረድ ያስከተላቸውን ቁስሎችን በማብራራት፣ ትልቁ የካቶሊክ ማኅበረሰብ ክፍል የሆኑ ሴቶች እውቅና እንዳልተሰጣቸው፣ ቤተ ክህነታዊ የሥልጣን ተዋረድ አሁንም የአፍሪካ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን እንደሚቆጣጠር ለተሳታፊዎቹ አስታውሰዋል። አባ ኦሮባቶር ያቀረቡትን ዝግጅት ተከትለው የሰብሰባው ተሳታፊዎች በቡድን ተመድበው በመንፈሳዊ የውይይት ዘዴ ላይ መነጋገራቸው ታውቋል።

በአዲስ አበባ እየተካሄደ የሚገኘው የአህጉራዊ ምዕራፍ የሲኖዶሳዊነት ሂደት ጉባኤ፣ ዓርብ የካቲት 24/2015 ዓ. ም. ባካሄደው ሁለተኛ ቀኑ፣ በመንፈሳዊ የውይይት ዘዴ ላይ ተነጋግሯል። በስብሰባው መግቢያ ላይ የቀረበው መንፈሳዊ የውይይት ዘዴ፣ የስብሰባው ተሳታፊዎች እርስ በእርስ መደማመጥን እና መንፈስ ቅዱስን ማዳመጥን እና መረዳዳትን በማጎልበት ላይ ያተኮረ እንደነበር ታውቋል።

የስብሰባው ተሳታፊዎች ሲኖዶሳዊነትን በተመለከተ፣ ከሀገረ ስብከት ደረጃ ጀምሮ ባገኙት የግል ልምድ ላይ ካሰላሰሉ በኋላ፣ ቤተ ክርስቲያን እንደ ወንጌል መልዕክተኛ ሲኖዶዶሳዊት እንድትሆን የሚያደርጓትን ግንዛቤዎች በመለየት እና በሲኖዶሳዊነት ሂደቱ የመጨረሻ ምዕራፍ ውስጥ ሊዳሰሱ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤን የሚያስጨብጡ ውይይቶችን አካሂደዋል። በሲኖዶሳዊነት ሂደት የመጀመሪያ ምዕራፍ ማጠቃለያ ላይ፣ ቫቲካን ወደሚገኝ ቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በደረሱ፣ በመላው ዓለም ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የደረሱ ምላሾችን መሠረት ባደረገ የሲኖዶሳዊነት አህጉራዊ ምዕራፍ የተግባር ሰነድ ላይ አስተንትነዋል።

ዓርብ የካቲት 24/2015 ዓ. ም. በጠዋቱ የውይይት መድረክ ላይ አህጉራዊ ምዕራፍ የተግባር ሰነድን በንባብ ካቀረቡ በኋላ አንዳንድ መመሪያዎችን በመስጠት ውይይቱን ያስጀመሩት፣ የአፍሪካ እና ማዳጋስካር የኢየሱሳውያን ማኅበር ፕሬዚደንት እና የነገረ መለኮት ሊቅ አባ ኦሮባቶር ናቸው። የጋራ ውይይቱን ከማስጀመራቸው አስቀድመው፣ የስብሰባው ተሳታፊዎች የጋራ የምስጢረ ጥምቀት ክብራቸውን እንዲገነዘቡት ጠይቀው፣ “ምስጢረ ጥምቀት፥ መሠረታዊ ማንነታችን፣ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት እና ተልዕኮ ለመሳተፍ የሚያስችለን፣ በኅብረት፣ በጋራ እና በሁሉም ቤተ እምነቶች ውስጥ ካሉት ሰዎች ጋር ለመወያየት ብቁ የሚያደርገን ምስጢር ነው” ብለዋል። አባ ኦሮባቶር በመቀጠልም፣ የስብሰባው ተሳታፊዎች በሙሉ ሃሳባቸውን በግልጽ እና በታማኝነት እንዲገልጹ የሚያስችለው የመንፈሳዊ ውይይት ዘዴ ልብ፣ “ጸሎት እና ጽሞና ነው” መሆኑን አስታውሰዋል።

አባ ኦሮባቶር በመቀጠልም፥ በትን. ኢሳ. 54:2 ላይ፥ “ ‘የድንኳንሽን ሥፍራ አስፊ’፥ መጋረጃዎችሽንም ይዘርጉ፤ አትቆጥቢ፤” የሚለውን በመጥቀስ፣ ከነቢዩ ኢሳይያስ መጽሐፍ የተወሰደው የድንኳን ምስል፥ በጣሪያው፣ በግድግዳው እና በማዕከላዊ ምሰሶው፣ ከአፍሪካዊው ዳስ ጋር ሊመሳሰል የሚችልበትን መንገድ አስረድተዋል። “ድንኳንም ሆነ ዳስ ቤት፣ ያለ በር ሊሰፉ እንደሚችል ሁሉ፣ ቤተ ክርስቲያንም ራሷን ለሌሎች ዝግ የምታደርግባቸው በሮች የሌላት፣ ነገር ግን ዙሪያዋ ያለማቋረጥ የሚሰፋ ነው” በማለት አስረድተዋል። “ቤተ ክርስቲያንም፣ ሁሉም ሰው ሥፍራን የሚያገኝባት እና እንደ ቤተሰብ የሚኖሩባት ድንኳን ናት” ብለዋል። የአፍሪካ እና ማዳጋስካር የኢየሱሳውያን ማኅበር ፕሬዚደንት እና የነገረ መለኮት ሊቅ አባ ኦሮባቶር በመጨረሻም “የእግዚአብሔር መንፈስ መርቶን በአንድነት የተሰበሰብንበት ጊዜ በመሆኑ እግዚአብሔርን ልናመሰግነው ይገባል” ብለዋል። “ይህ የምንደሰትበት ጊዜም ነው” ያሉት አባ ኦሮባቶር፥ “እንክርዳዱ እንዲያደናቅፈን ዕድል መስጠት የለብንም” ብለው፣ “መንፈስ ቅዱስ ወደ ፊት እንዲመራን ልንፈቅድለት ይገባል” ብለዋል።

04 March 2023, 16:21