ፈልግ

ከአህጉራዊ የሲኖዶሳዊነት ስብሰባ ተሳታፊዎች መካከል ጥቂቶቹ ከአህጉራዊ የሲኖዶሳዊነት ስብሰባ ተሳታፊዎች መካከል ጥቂቶቹ  

የአፍሪካ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት፣ ሁሉ አቀፍ ነው ተባለ

በአዲስ አበባ ከየካቲት 22/2015 ዓ. ም. ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኝ የአህጉራዊ ምዕራፍ የሲኖዶሳዊነት ስብሰባ ተሳታፊዎች፣ ከሲኖዶሳዊ ሂደቱ እስካሁን ያገኙትን ልምድ በማስታወስ አድናቆታቸውን ገለጹ። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከጥቅምት 2021 ዓ. ም. ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ሂደት፣ እያንዳንዱን የቤተ ክርስቲያን ክፍል በማሳተፍ ላሳየው መልካም ተግባር፣ በአዲስ አበባ አህጉራዊ የሲኖዶሳዊነት ሂደት ስብሰባን በመካፈል ላይ የሚገኙ የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ልኡካን አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአሥር ቡድኖች ተመድበው ውይይት ያደረጉት፣ ካርዲናሎች፣ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ ጎልማሳ እና ወጣት ምእመናን በአንድ ዓመት ከግማሽ የሲኖዶሳዊነት ሂደት ውስጥ ያጋጠሟቸውን እና የተማሩትን ልምድ አካፍለዋል። ሲኖዶሳዊነት በአፍሪካ አህጉር ከዚህ በፊት የሚሰራበት መንገድ እንደሆነ፣ በአፍሪካ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀባይነትን ያገኘ መሆኑን እንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ አገራትን የሚውቅል አንድ ቡድን አስታውቋል።

አካታችነት እና መለወጥ

ከዚሁ ጎን ለጎን የሲኖዶሳዊነት ሂደት ቤተ ክርስቲያን ሁሉን ለማቀፍ የምታደርገውን ጥረት የሚያበረታታ በመሆኑ ምስጋና ቀርቦለታል። ይኸው ቡድን አክሎም፣ “ቤተ ክርስቲያን የተዘነጉትን በተለይም ሴቶችን፣ ወጣቶችን እና አካል ጉዳተኞችን ማካተት እንዳለባት ይሰማናል” ብሏል። “በአንዳንድ የእምነት ተቋማት ብዙ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን አጥተናል” ያለው ቡድኑ፣ በዚህ ክስተት ላይ በጥልቀት መመርመር እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።

ሲኖዶሳዊ ሂደቱ በኅብረት የመጓዝ እና የአንድነት ልምምድ በመሆኑ በለወጥ ስሜት ሊበረታታ እንደሚገባ ተገልጿል። “በሲኖዶስዊነት ሂደቱ በአፍሪካ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ከወጣቶች፣ ከሴቶች እና ከአካል ጉዳተኞች ጋር  በኅብረት እንድንራመድ የመንፈስ ቅዱስ ጥሪ እንደሆነ ተሰምቶናል” ያለው ቡድኑ፣ ከዚህም በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓትን በተመለከተ የሲኖዶሳዊነት ጉዞ ቤተ ክርስቲያን የሁላችን እንደሆነች ማስገንዘቡን ቡድኑ አስታውሷል። በመሆኑ ምእመናን ኃላፊነትን በመሸከም ቤተ ክርስቲያንን ለማሳደግ እና ተነሳሽነቶችን ለመውሰድ ነፃ መሆናቸውን ቡድኑ ገልጾ፣ በእርግጥ ይህ ቀጣይ ሂደት መሆኑን ብንገነዘብም፣ በአፍሪካ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን የመሆን መንገድ መሆን አለበት” በማለት ሌሎች ሁለት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ አገራት ቡድኖች ተናግረዋል።

የበለጠ አሳታፊ እና የአድማጭነት ሞዴል

የቤተ ክርስቲያን መዋቅር ለአዲሱ እና የበለጠ አሳታፊ ለሆነ የቤተ ክርስቲያን አድማጭነት ሞዴል ዕድል መስጠት እንዳለበት የጠቆመው በአፍሪካ የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋር አገራት ቡድን በበኩሉ፣ የሲኖዶሳዊነት ሂደት እንደ ቤተ ክርስቲያን የአኗኗር ዘይቤ ሊወሰድ እንደሚገባ አሳስቦ፣ በሂደቱ የምእመናን ተሳትፎ የግድ መሆኑን አስገንዝቧል። የሲኖዶሳዊነት ሂደት ማዕቀፍ ሁላችንም የወንጌል ልኡካን ለመሆን የሚጠራን እና ይህም በተሰጠን ተልዕኮ ተጠያቂነት እንዳለብን የሚገልጽ ነው” ብሏል። የቤተ ክርስቲያን ዘይቤ የሆነው ሲኖዶሳዊነት፣ በሕዝቦች መካከል የእርቅ ሂደትንም ሊያመጣ እንደሚችል ተነግሯል። እንዲህ ያለው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር በሲኖዶሳዊነት መንፈሱ፣ እንደ ምስጢረ ጥምቀት እና ምስጢረ ቁርባን ያሉ ምስጢራትን እንዳይቀበሉ ለተከለከሉት ክርስቲያኖች አገልግሎቱን ክፍት ማድረግ እና ሊሻሻል እንደሚችል ገልጿል።

የሴቶች እና የወጣቶች ሚና

የሲኖዶሳዊነት ሂደቱ በወደፊቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሴቶች እና ወጣቶች የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ አንዳንድ ግንዛቤዎችን መስጠቱን የስብሰባው ልኡካን በአንድ ድምጽ ተናግረዋል። “ሴቶች የቤተ ክርስቲያኑ ቁልፍ አባላት ናቸው” ያለው ቡድኑ፣ በቤተ ክርስቲያን እና በኅብረተሰብ ውስጥ የተዘንጉ፣ ነገር ግን ያላቸውን ስጦታ እንዲያካፍሉ የሚፈቀድላቸው ብዙ ሴቶች መኖራቸው ገልጾ፣ “በዚህ ረገድ ወጣቶችም ቤተ ክርስቲያን የተስፋ ምንጭ መሆኗን ይገነዘባሉ” ብሏል። ወጣቶች ሃሳባቸውን የሚገልጹበት ዕድል እንዲሰጣቸው እየጠየቁ መሆኑን ገልጾ፣ “በሕይወታቸው ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ አሉታዊ ኃይሎች መሸነት የለባቸውም” ብሏል።

ሁሉም ሰው የሚያበረክተው እገዛ አለ!

በአፍሪካ ውስጥ የሲኖዶሳዊነት ልምድ ከተመለከታቸው ሌሎች ጉዳዮች መካከል የኅብረት መንፈሳዊነትን የማስተዋወቅ ፍላጎት እንደሆነ የጠቀሱት የስብሰባው ልኡካን፣ የቤተ ክርስቲያን መዋቅሮችን በትናንሽ የክርስቲያን ማኅበራት እና መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የባለቤትነት ስሜትን ማጎልበት እንደሆነ፣ በዚህም ቤተ ክህነት ሥልጣንን መከታ የማድረግ አደጋን ማስወገድ የሚቻል መሆኑን ገልጸዋል። “ይህ በሙሉ አዲስ ዘዴ ያስፈልገዋል” ያሉት ልዑካኑ፣ እንደተነገረው አብሮ በኅብረት መጓዝ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ከባድ እንደሆነ እና መታደስን የሚያመጣ ትዕግስትን ይጠይቃል” በማለት ሌላው ቡድን አስረድቷል። ቡድኑ አክሎም፣ "ሁሉም ሰው ለቤተ ክርስቲያኑ የሚያበረክተው አገዛ እንዳለው እና ሲኖዶሳዊነት የማያቋርጥ ግንኙነትን የሚጠይቅ፣ እርስ በርስ በመደማመጥ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ሃላፊነት ከካህናት ጋር በኅብረት መወጣት ያስፈልጋል" ብሏል። ልዑካኑ የመጀመሪያ ቀን ውይይታቸውን ሲያጠናቅቁ በቀሪዎቹ ሦስት የስብሰባው ቀናት ውስጥ ተጨማሪ መንፈሳዊ ማስተዋል እንዲኖራቸው የሚያስችል መሠረት መጣላቸው ታውቋል።

04 March 2023, 16:28