ፈልግ

የአውሮፓ ሲኖዶሳዊ ሂደት አህጉራዊ ውይይት በፕራግ የአውሮፓ ሲኖዶሳዊ ሂደት አህጉራዊ ውይይት በፕራግ 

የአውሮፓ ሲኖዶሳዊ ሂደት አህጉራዊ ውይይት በፕራግ ተጀመረ

በአውሮፓ አገራት ሲካሄድ የቆየው ሲኖዶሳዊ የምክክር ሂደት ተጠናቆ ወደ አህጉራዊ ደረጃ መድረሱ ተነግሯል። በአውሮፓ አገራት በሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን መካከል ሲካሄድ የቆየው ሲኖዶሳዊ ሂደት አህጉራዊ የምክክር ሂደቱን ጥር 27/2015 ዓ. ም. በቼክ ሪፓብሊክ ዋና ከተማ ፕራግ በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መጀመሩ ታውቋል። እስከ እሑድ የካቲት 5/2015 ዓ. ም. ድረስ በሚቆየው እና ከየአገራቱ በተሰበሰቡት የሲኖዶሳዊ ሂደት ውጤት ላይ ሁለት መቶ ልኡካን ውይይት እንደሚያካሂዱበት ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኮንጎ ዴሞክርሲያዊት ሪፓብሊክ እና በደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ሲመለሱ እንዳስገነዘቡት፣ በሲኖዶሳዊነት ውስጥ የጳጳሳት ሚና የመንግሥት ወይም የጎሳ መሪዎች ሚና ሳይሆን የሐዋርያዊ እረኝነት ሚና መሆን እንደሚገባ ያስታወሱ ሲሆን፣ በፕራግ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የአውሮፓ አህጉራዊ ሲኖዶሳዊ የምክክር ሂደት ዋና ዓላማም ይህን መሠረታዊ ጽንሰ-ሀሳብ እንደገና ለማረጋገጥ ነው ተብሏል።

ሰባቱ አህጉራዊ ስብሰባዎች

በሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2021-2024 ዓ. ም. የሚካሄዱ የአንድነት፣ የተሳትፎ እና የሐዋርያዊ ተልዕኮ ሂደቶች በተለያዩ ደረጃዎች እንደሚካሄዱ ታውቋል። በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በመካሄድ ላይ የሚገኘው ሲኖዶሳዊ ሂደት በመላው ዓለም የሚገኙ አገራት ባካሄዱት የምክክር ሂደት ተጠናቅቆ ዛሬ በሁለተኛው እና አህጉራት በሚያካሂዱት የምክክር ሂደት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። በዚህም መሠረት በአህጉራት ደረጃ የሚካሄድ ስብሰባ ለኦሺኒያ አህጉር በፊጂ ደሴቶች ዋና ከተማ ሱቫ ላይ እሁድ ጥር 28/2015 ዓ. ም. የተጀመረ ሲሆን፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ በቤሩት ዋና ከተማ ሊባኖስ ከየካቲት 5-11 /2015 ዓ. ም. ድረስ፣ ለሰሜን አሜሪካ በኦርላንዶ (ፍሎሪዳ) ከየካቲት 6-10/2015 ዓ. ም.፣ ለእስያ አህጉር በታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ ከየካቲት 16-20/2015 ዓ. ም.፣ ለአፍሪካ አህጉር በኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ከየካቲት 22-27/2015 ዓ. ም.፣ ለላቲን አሜሪካ አህጉር በኮሎምቢያ ዋና ከተማ ቦጎታ ላይ ከመጋቢት 8-14/2015 ዓ. ም. እንደሚካሄድ ይጠበቃል።

ከመላው አውሮፓ የመጡ ሁለት መቶ ልዑካን

የአውሮፓ አህጉር ሲኖዶሳዊ የምክክር ስብሰባን ቅዳሜ ጥር 27/2015 ዓ. ም. በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ያስጀመሩት የፕራግ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ያን ግራብነር ሲሆኑ፣ እስከ እሑድ የካቲት 5/2015 ዓ. ም. እና የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ያስጀመሩት የድህረ ሲኖዶስ ምክር ቤት 20ኛ ዓመት መታሰቢያ ድረስ የሚቆይ ስብሰባ ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ የመጀመሪያው ሲኖዶሳዊነትን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን እና የሚኖሩትን ዕድሎች ለመዘርዘር ከ 39 የአውሮፓ አገራት ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች የተወጣጡ ወደ 156 የሚጠጉ ልዑካን እና ሌሎች 44 ተጋባዥ እንግዶች የሚገኙበት መሆኑ ታውቋል።ሁለተኛው ከየካቲት 4-5/2015 ዓ. ም. ድረስ የሚቆይ እና ከውይይቶቹ የሚገኙ አስተያየቶችን የሚመለከቱ እና እስከ መጋቢት ወር ድረስ ተዘጋጅቶ ለሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት የሚላከውን ምክረ ሃሳብን የሚወስኑ 39 የአገራት ፕሬዚዳንቶች ብቻ የሚሰበሰቡበት እንደሚሆን ታውቋል። ከሰባቱም አህጉራት የሚቀርቡ የመጨረሻ ምክረ ሃሳቦች ስብስብ እስከ ሰኔ ወር 2015 ዓ. ም. ድረስ ብቸኛውን የተግባር ሰነድ አዘጋጅቶ በማቅረብ ይጠናቀቃል።

የሲኖዶሳዊ ውይይት ፍሬዎችን ከየአገራት መሰብሰብ

በአንድ የተወሰነ ክልል በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት መካከል በተካሄዱ ውይይቶች ወደ አንድ ምዕራፍ ላይ ለመድረስ እና በኅብረት ለመጓዝ የሚረዳ አገራዊ ምክረ ሃሳብ ወደ አህጉራዊ መድረክ ሲቀርብ የተግባር ሰነድን ለማዘጋጀት እንደሚጠቅም በመላው ዓለም የሚገኝ የእግዚአብሔር ሕዝብ በሲኖዶሳዊ ሂደት መጀመሪያ ዓመት መናገሩ ይታወሳል። በሲኖዶሳዊ ሂደት ላይ ማስተዋል እንዲኖር የሚያስችል ትክክለኛ መመሪያ በሦስት ጥያቄዎች ላይ የተመሠረተ ሲሆን እነርሱም፥ የሲኖዶሳዊነት ግንዛቤዎች ጎልተው የሚታዩባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? በሚቀጥሉ የሲኖዶሳዊ ጉዞ ደረጃዎች ላይ መቅረብ ያለባቸው ጥያቄዎች የትኞቹ ናቸው? በጥቅምት ወር 2016 ዓ. ም. በሚካሄደው የመጀመሪያ ዙር የሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ቅድሚያ የሚሰጥባቸው የውይይት ጭብጦች እና የተግባር ጥሪዎች የትኞቹ ናቸው? የሚሉት ይገኙባቸዋል። 

06 February 2023, 17:23