ፈልግ

የአፍሪካ ጳጳሳት ከቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ጋር ውይይት ሲያካሂዱ የአፍሪካ ጳጳሳት ከቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ጋር ውይይት ሲያካሂዱ 

በዓመፅ የተከፋፈሉት አገራት ጳጳሳት ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር እንደሚተባበሩ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኮንጎ ዴሞክራሲዊት ሪፓብሊክ እና በደቡብ ሱዳን ከጥር 23 እስከ 28/2015 ዓ. ም. ድረስ ያካሄዱትን 40ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው መመለሳቸው ታውቋል። ከቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት በኋላ ሃሳባቸውን የገለጹት፣ በዓመፅ እና በጸብ የተከፋፈሉት አገራት ብጹዓን ጳጳሳት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር እንደሚተባበሩ የገለጹ ሲሆን፣ የኮንጐ ካርዲናል አቡነ አምቦንጎ፣ ይህን ለማድረግ ድፍረት እንደሚጠይቅ እና እራሳቸውን ለፖለቲካ መከፋፈል መፍቀድ እንደሌለባቸው የተናገሩ ሲሆን፣ የሩዋንዳው ካርዲናል አቡነ ካምባንዳም በበኩላቸው፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የይቅር ባይነት እና አቦር በሰላም የመኖር መልዕክት ልባቸው መነካቱን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በኪንሻሳ አቅራቢያ በሚገኝ የንዶሎ አየር ማረፊያ በመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባቀረቡት ስብከት፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሲሆኑ ዘወትር ይቅርታን የማግኘት ዕድል እንዳለ፣ ራስን፣ ሌሎችን እና ታሪክን ይቅር ለማለት የሚያስችል ጥንካሬ እንዳለ በመግለጽ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በይቅርታው ሊቀባን እንደሚፈልግ፣ ሰላምን እና ይቅርታን የማድረግ ድፍረትን እንደሚሰጠን እና ታላቅ ልባዊ ምሕረትን ለማድረግ የሚያስችል ድፍረትን እንደሚሰጠን ገልጸዋል።

በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ከቅዱስነታቸው ጋር የተፋላሚ አገራት ብጹዓን ጳጳሳት፣ የተፋላሚ ወገኖች መሪዎች፣ ሚሊሻዎች እና ዓማጺ ቡድኖች የተገኙ ሲሆን፣ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ብጥብጥ እና ጦርነት የሚካሄደው ከውጭ ኃይሎች ጋር ብቻ ሳይሆን ከውስጥም ጭምር መሆኑ ታውቋል። ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ጳጳሳት ጋር በመንበረ ታቦት እና በምሳ ሥነ ሥርዓት ላይ የሩዋንዳ ፣ የቡሩንዲ እና የኮንጎ ብራዛቪል ብጹዓን ጳጳሳት እንደ ነበሩ ተመልክቷል።

ቤተ ክርስቲያን የውይይት መንገድን እንደምትከተል የተናገሩት የኪንሻሳው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ በፖለቲካ ምክንያት ሳይለያዩ አንድ የሚሆኑበትን መንገድ መከተል እንደሚገባ አሳስበዋል። ፖለቲከኞች በሕዝቦች መካከል ጥላቻን፣ ልዩነትን እና አለ መተማመንን እንደሚያባብሱ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል አምቦንጎ፣ ብጹዓን ጳጳሳት እና ቤተ ክርስቲያን የተጠሩት የሰላም እና የአንድነት መንገድ እንዲጓዙ ስለሆነ ወደ ጥላቻ እና ልዩነት አመክንዮ መግባት እንደሌለባቸው ተናግረው፣ ከሩዋንዳ ለመጡት ብጹዓን ጳጳሳት ምስጋናቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ ይህን ለማድረግ እና የጋራ ተልዕኮን ለመወጣት ድፍረትን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “የይቅርታን መንገድ መጓዝ ያስፈልጋል” ያሉትን ያስታወሱት የኪጋሊ ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል አንትዋን ካምባንዳ፣ ቅዱስነታቸው ከሩዋንዳ ጋር በሚያዋስነው ድንበር ላይ ወደምትገኝ ጎማ ከተማ ለመሄድ እንደሚፈልጉ ያላቸውን ምኞት በማስታወስ፣ በአካባቢው በተፈጠረው ሁከት እና ግጭት ምክንያት አለመቻላቸውን ገልጸው፣ “ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ካስተላለፏቸው ስምንት የሰላም መልዕክቶች መካከል ስድስቱ ሁላችንንም ይመለከታል” ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል አንትዋን ካምባንዳ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1994 በአገራቸው በተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል በአንድ መቶ ቀናት ውስጥ ከ800 ሺህ የማያንሱ ሰዎች በጎሣ እና በፖለቲካ ግጭት ምክንያት የተገደሉበትን ሁኔታ አስታውሰው፣

“የዘር ማጥፋት ወንጀሉ ከውጭ በመጡ ሌሎች ኃይሎች የተፈጸመ ሳይሆን በአንድ መንደር ውስጥ አብረው ይኖሩ በነበሩ ሩዋንዳውያን የተፈጸመ ወንጀል ነበር” ብለው፣ “የዘር ማጥፋት ወንጀል ካለፈ በኋላ እንዴት አብረን እንኖራለን? ብለን ዛሬ እራሳችንን መጠየቅ እንችላለን” ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል አንትዋን ካምባንዳ፣ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተናገሩትን በመጥቀስ “ይቅርታ አብሮ የመኖር መንገድ እንደሆነ፣ አብሮ ለመኖር እራስን ይቅር ማለት እንደሚገባ እና ይቅርታ የእግዚአብሔር ፀጋ እንደሆነ፣ ጥፋተኛ የሆነውን እያንዳንዱን ግለሰብ እና ቤተሰብ ጭምር የሚመለከት መሆኑን ተናግረው፣ አክለውም የይቅርታ መንገድ የሌላው ስቃይ ከራስ ስቃዬ ጋር የተያያዘ መሆኑን የሚያስገነዝብ እንዲሁም መስቀል የሚያስተምረን ትምህርት መሆኑን አስረድተዋል።

መታረቅ እና አንዱ ሌላውን በእንግድነት መቀበል ይገባል

የቡሩንዲ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የጊቴጋ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቦናቬንቱር ናሂማና፥ "እርቅ በጋራ ለመኖር፣ የሃይማኖት፣ የጎሳ እና የፖለቲካዊ ግጭቶችን ለመፍታት ቁልፍ ነው” ብለው፣ የብሩንዲ ቤተ ክርስቲያናት ሲኖዶሳዊ ሂደትም በዚህ ላይ ያተኮረው መሆኑን ተናግረዋል። በእውነት የመግባባት እና የወንድማማችነት ማኅበረሰብ እንዲኖረን በይቅርታ መኖር እንደሚገባ እና የውጭ አገር ዜጋ ቢሆንም በእንግድነት መቀበል እንደሚገባ አስረድተው፣ ቡሩንዲ ውስጥ በርካታ የኮንጎ ስደተኞች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ሁላችንም ሰላምን እንሻለን

ብጹዓን ጳጳሳት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የምዕመናን ልዑካን ቡድን ወደ ኮንጎ ኪንሻሳ መምጣቱን የገለጹት የኮንጎ ብራዛቪል ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የብራዛቪል ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቢዬንቨኑ ማናሚካ፣ የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት በክልሉ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ገልጸው፣ አገራቸው በኮንጎ ግጭት በቀጥታ ባይጎዳም ተሳታፊ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል። “ሁላችንም ሰላምን እንሻለን” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማናሚካ፣ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ በምስራቃዊ ክፍል እየተካሄደ ያለው ግጭት ሰላምን እንደማይሰጣቸው፣ ቀደም ሲል ያጋጠሙትን የጦርነት ጉዳቶች የሚያስታውሳቸው መሆኑን ተናግረዋል። አክለውም ጦርነቱ እንዳይባባስ ለሚያደርግ የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሰላም መልዕክት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሰላም መልዕክተኞች እንድንሆን ተጠርተናል!

የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሊቀ መንበር እና የኪሳንጋኒ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኡቴምቢ ታፓ፣ “ሁላችንም ሰላምን መገንባት አለብን፤ በይቅርታ አንድ የሚያደርገንን ማኅበረሰብ እንደገና የመገንባት ተልዕኮ አለብን” ብለው፣ የግል እና የተቋማት ይቅርታ የተሳሰሩ መሆናቸውን እራሳችንን ማሳመን ያስፈልጋል ብለዋል። “በጥምቀት የእግዚአብሔር ልጆች፣ ወንድሞች እና እህቶች እርስ በርሳችን ይቅር መባባልን መማር አለብን፤ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እዚህ ስለሚፈጸሙት ነገሮች ሁሉ ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ ጦርነት እና አመጽ ሰላምን አደጋ ላይ ይጥላል፣ የሚከተለው ችግርም መላውን አህጉር የሚመለከት ነው” ብለዋል።

 

06 February 2023, 17:33