ፈልግ

ኢየሱስ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ፈወሰ ኢየሱስ ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ፈወሰ 

የታኅሳስ 2/2015 ዓ. ም. ዘመፃጒዕ (ዘአስተምሕሮ 4ኛ) ዕለተ ሰንበት ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት፥ ዮሐ. 9: 1-41፣ 1ኛ ቆሮ. 2: 1-16፣ 1ኛ ዮሐ. 5: 1-5፣ ሐዋ. 5: 34-42

የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ፥ “ክርስቶስ የዓለም ብርሃን ነው!”

በክቡር አባ ዳንኤል ኃይሌ የተዘጋጀ፥

"የተወደዳችሁ ምእመናን እንዲሁም በጎ ፈቃድ ያላችሁ ሁሉ እንደምን ሰንብታችኋል! በማያልቀው ምሕረቱ እስከዚች ሰዓት የጠበቀን አምላካችን ስሙ የተመሰገነ ይሁን። ቅዱስ ቃሉን ሰምተን ምስክሮቹ እንድንሆን መንፈስ ቅዱስ ይርዳን። ዛሬ የምንካፈለው የቅዱስ ወንጌል ቃል ከዮሐ. 9: 1-41 የተወሰደ ነው። ከዚህ በፊት በቀረበልን የቅዱስ ወንጌል ክፍል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በሽተኞችን ሲፈውስ እና አጋንትን ሲያስወጣ ፈሪሳዊያንና የሙሴ ሕግ መምህራን ይቃወሙት እንደነበር ተመልክተናል። ፈሪሳዊያን የተቃወሙበት ምክንያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተዓምራትን የሚያደርገው በሰንበት ቀን ስለ ነበር ነው።

በዛሬው ወንጌልም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሰንበት ቀን ዐይነ ስውር ሆኖ የተወለደውን ሰው እንደፈወሰው እንመለከታለን። ይህ ዐይነ ስውር መንገድ ዳር ተቀምጦ የሚለምነው ወደ ምኩራብ የሚገቡ ሰዎችን ነበር። ምክንያቱም ዐይነ ስውራን እና የአካል ጉዳተኞች አዘውትረው ይህን ሥፍራ ይመርጡ ነበር። የሚመርጡትም ሕይወታቸውን የሚያቆዩበት ሌላ የተሻለ ሥፍራ ስለሌላቸው እና ኑሯቸውንም በምኩራብ አከባቢ ማድረግ ስላለባቸው ነው። 'ኢየሱስም በመንገድ ሲያልፍ ዓይነ ስውሩን ሰው ስላየ ወደ እርሱም ሄደ' ይላል ቃሉ።

ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወታችን፣ በልባችን እና በቤተሰባችን መካከል ሲያለፍ ጭለማው መንገዳችን ወደ ብርሃን ይለወጥል። የዛሬው የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ድሃን መርዳት መልካም ተግባር መሆኑን ያስገነዝበናል። የእኛን ዕርዳታ የሚፈልጉትን እያየን እንዳላየ፣ እየስማን እንዳልሰማ ማለፍ እንደሌለብን ያሳስበናል። ለድሃ መስጠት ለእግዚአብሔር እንደ ማበደር ነው። ምክንያቱም መልስው መክፈል ስለማይችሉ እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ሃላፊነት ይወስዳል። ደቀ መዛሙርትም አብረውት ስለ ነበሩ፥ 'ይህ ሰው ዐይነ ስውር የሆነው በራሱ ኃጢአት ነው ወይስ ከቤተሰብ የወረስው ኃጢአት ነው?' ብለው ኢየሱስን ጠይቁት። ኢየሱስም የራሱም ሆነ የቤተሰቡ ኃጢአት እንዳልሆነ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ክብር በእርሱ እንዲገለጥ መሆኑን ነገራቸው። ምክንያቱም በአይሁዳውያን እምነት ማንኛውም ዓይነት በሸታ ወይም በሰውነት ላይ የሚወጣ ለምጽ የኃጢአት ውጤት እንደሆነ ስለሚያምኑ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በዓለም ሳለሁ የዓለም ብርሃን ነኝ ካለ በኋላ ምራቁን መሬት ላይ እንትፍ አለና ከአፈር ጋር ለውሶ የዕውሩን ዐይኖች ከቀባ በኋላ ሰሊሆም መጠመቂያ ሄደህ ታጠብ አለው። እርሱም ሄዶ ታጥቦ እያየ መጣ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዕውሩን ዐይን ምራቅና አፈር ቀብቶ ያዳነበት ምስጢር ወደ የሰው ልጅ አፈጣጠር ይወስደናል። 'እግዚአብሔር አምላክም ሰውን ከምድር አፈር አበጀው። በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ።' (ዘፍ. 2፣7)

እዚህ ላይ እግዚአብሔር ሰውን እንደገና መፍጠሩን እንመለከታለን። የመጀመሪያው ሰው አዳም ትዕዛዛቱን በማፍረስ ጸጋውን እንደተገፈፈ ይነግረናል። እንዲሁም፥ 'ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።' (2ኛ ቆሮ. 5:17) በሰሊሆም ውሃ መታጠብ የጥምቀት ምሳሌ ነው። በጥምቀት አዲስ ፍጥረት እንሆናለን። ጸጋውን እንለብሳለን፤ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን እንጠራለን። በመንፈስ እደገና እንወለዳለን። እንዲሁም ኢየሱስ ኒቆዲሞስን፥ 'እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም።' አለው። ኒቆዲሞስም፥ “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን?” አለው። ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፥ 'እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም።' አለ። (ዮሐ. ምዕ. 3)

የእግዚአብሔርን ምስጢር እና ጥበብ ያለ ክርስቶስ ልንረዳው አንችልም። ኒቆዲሞስ የተረዳበት መንገድ በስጋዊ ዐይን ነበር። ዐይነ ስውሩ ለክረስቶስ በመታዘዝ መዳኑ እኛም የመዳን ድርሻ እንዳለን ያሳስበናል። የመዳናችን ማረጋገጫ ዕለት ተዕለት በምናደርገው የክርስትና ጉዞ ይወስናል። ዓይነ ስውሩም በሰሊሆም ውሃ ከታጠበ በኋላ እያየ ሲመለስ ያዩት ጎረቤቶቹ ይህን እውነት ማመን አልፈለጉም። ለእነርሱም እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፥ 'እኔ ነኝ፣ ያዳነኝም ነቢይ ነው።' በማለት መለሰላቸው። እነርሱም ይህ ተዓምር የተደረገው በስንበት ቀን ሰለ ነበር ዐይነ ስውሩን ወደ ሙሴ ሕግ አዋቂዎች አመጡት። ፈሪሳዊያንም እንዴት እንደዳነ ወላጆቹን ጠየቁ። እነርሱም እንዲህ አሉ፥ 'ይህ ልጃችን ዕውር ሆኖ እንደ ተወለደ እናውቃለን፤ ዳሩ ግን አሁን እንዴት እንዳየ አናውቅም፥ ዐይኖቹን ማን እንዳበራለት እኛ አናውቅም፤ እርሱን ጠይቁት፣ ሙሉ ሰው ነው አሉ።' ይህን ያሉበት የመጀመሪያው ምክንያት አይሁዶችን ስለፈሩ እና ማንም ሰው በክርስቶስ ስም ከመሰከረ ከምኩራብ እንደሚባረር፣ ሁለተኛው ምክንያት የአይሁዳዊያን ልጆች ከ13 ዓመት በላይ ሲሆኑ የሙሴን ሕግ መማርና ማክበር እንደሚጀምሩ ስለሚያውቁ ነው። ፈሪሳውያንም ዐይኑ እንዴት እንደበራ ጠየቁት። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ 'ለምን ደጋግማችሁ ትጠይቁኛላችሁ? እውነት ነገርኳችሁ ልታምኑኝ አልወዳችሁም፤ አሁን ለምን ለመስማት ፈለጋቸሁ? እናንተም የእርሱ ደቀመዝሙር መሆን ትፈልጋለሁን?' አላቸው። እነርሱም፥ 'አንተ የእርሱ ደቀመዝሙር ነህ! እኛ ግን የሙሴ ደቀመዝሙር ነን?' አሉት። እርሱም እንዲህ አላቸው፥ 'እግዚአብሔር የሚሰማው የእርሱን ፈቃድ የሚፈልጉትን እንጂ ኃጢአተኞችን አይደለም' አላቸው። እነርሱም በዚህ አነጋገር ተናደው ከምኩራቡ አባረሩት። ዓይነ ስውሩም ውጪ ኢየሱስን አገኘ። ኢየሱስም፥ 'በእግዚአብሔር ልጅ ታምናለህ?' አለው። ዐይነ ስውሩ፥ 'እንዳምነው እርሱ ማነው?' አለው፣ ኢየሱስም 'አይተሄዋል፤ አንተን እያነጋገረ ያለው ነው' አለው። ዐይነ ስውሩ ኢየሱስን አመነ፤ ሰገደለትም።

ስለዚህ ወንድሞቼና እህቶቼ! ከዚህ ቃል ምን እንማራለን? ኢየሱስ ክርስቶስ ዐይነ ስውሩን እንደፈወሰው ሰምተናል። ምናልባት በሕይወታችን ውስጥ ችግር፣ መከራ እና ስደት ሊያጋጥመን ይችላል። የእግዚአብሔር ክብር በእኛ እንዲገለጥ ከፈለግን እግዚአብሔር በእኛ ሊሠራ ይችላል። እውነትን ይዘን ከሰዎች በኩል መከራ ሊደርስብን ይችላል። በእነርሱ ልንጠላም እንችላለን። ነገር ግን ክርስቶስ ከእኛ ጋር መኖሩን መዘንጋት የለብንም። ክርስቶስ የዓለም ብርሃን ነው። 'ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱም ይህ ነው። ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር መከናወኑ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።' (ዮሐ፤ 3: 19-21)

ውድ ወንድሞቼና እህቶቼ! በክርስቶስ ብርሃን እንመላለስ። ጨለማ ሕወታችንን ወደ ክርስቶስ እናምጣ! የተደበቀ ማንነታችን እና ኃጢአቶቻችንን ወደ ክርስቶስ ፊት እናቅርብ። ክርስትና ያለ ክርስቶስ፣ ቤተ መቅደስ ያለ ቤተ መቅደሱ ባለቤቱ እንዴት ሊሆን ይችላል? ዓይነ ስውሩ ከቤተ መቅደስ ተባርሮ ውጭ በወጣ ጊዜ ኢየሱስን አገኘ። በዓለማችን፣ በአገራችን፣ በቤተሰባችን እና በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ክርስቶስን እንዳናይ የጋረዱን ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ክርስትና እውነት እና ብርሃን ነው። ማንም ሰው ከእግዚአብሔር መደበቅ አይችልም። ማንም ሰው እግዚአብሔርን መዋሸት አይችልም። ምክንያቱም እግዚአብሔር ብርሃን ነውና። 'ነገር ግን እግዚአብሔር አስቀድሞ ከዘመናት በፊት ለክብራችን የወሰነውን፥ ተሰውሮም የነበረውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር እንናገራለን። ከዚችም ዓለም ገዢዎች አንዱ እንኳ ይህን ጥበብ አላወቀም፤ አውቀውስ ቢሆኑ የክብርን ጌታ ባልሰቀሉትም ነበር፤ ነገር ግን እንደተጻፈው፥ ‘ዐይን ያላየውን፤ ጆሮም ያልሰማው፤ በሰውም ልብ ያልታሰበው፤ እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው’' ተብሎ ተጽፏል። (1ኛ ቆሮ. 2:7)

ክርስቶስ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ 'እንደ ህፃናት ካልሆናችሁ መንግሥተ ሰማያት አትገቡም!' ብሎአልና። ይህም ክርስትና የትህትና መንገድ መሆኑን ያስረዳል። ሁሉም ዕውቀት ከክርስቶስ በታች ነው። ክርስትናችን ስም ሳይሆን በክርስቶስ ማመን እና ለእርስ መታዘዝ ነው። የክርስቶስን ምሳሌ መከተል ነው።በመጽ. ሲራ. 10:12 ላይ፥ 'የትዕቢት መነሻው እግዚአብሔርን መክዳት፣ ልቦናንም ከፈጣሪ ማራቅ ነው' ይላል። የኃጢአት ሁሉ እናት ትዕቢት ናት። ትዕቢት ውድቀትን ትቀድማለች። ሳጥናኤል ራሱን ከእግዚአብሔር እኩል ለማድረግ ስላሰበ በትዕቢቱ ወደቀ። አዳም እግዚአብሔርን ለመምሰል ያልተፈቀደውን በማድረግ በትዕቢቱ ወደቀ። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በምስጋና ጸሎቷ፥ 'በልባቸው የሚታበዩትን በትኖአል፤ ግዥዎችን ከዙፋናቸው አውርዶአል፤ ትሑታንንም ከፍ አድርጎአል።' (ሉቃ. 1: 51-52)

ዛሬም በሕይወታችን የገነባናቸው ማንነት ክርስቶስን እንዳናይ የሚያደርጉ የልባችን አዳማዊ ዝንባሌዎችን ትተን ወደ ብርሃን እንድንመጣ የዛሬው ቃል ያሳስበናል። ዓይነ ስውሩ ክርስቶስን ካለማወቅ ወደ ማወቅ፣ ካለማመን ወደ ማመን፤ ከስጋዊ ፈውስ ወደ መንፈሳዊ ፈውስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከዘላለማዊ ሞት ወደ ዘላለማዊ ሕይወት እንደተሸጋገረና እምነቱ እንዳደገ ሁሉ የእኛም እምነት እና ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት በየቀኑ ማደግ እንዲችል እግዚአብሔር አምላካችን በጸጋው ይርዳን። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም በአማላጅነቷ ትርዳን። አሜን።"

10 December 2022, 08:38