ፈልግ

የኅዳር 25/2015 ዓ.ም ዘአስተምህሮ 3ኛ ዕለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ የኅዳር 25/2015 ዓ.ም ዘአስተምህሮ 3ኛ ዕለተ ሰንበት የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ  (ANSA)

የኅዳር 25/2015 ዓ. ም. ዘአስተምሕሮ 3ኛ ዕለተ ሰንበት የወንጌል አስተንትኖ፤

የዕለቱ ንባባት፥ ማቴ 8፣23-34፣ ዕብ. 12: 25-29፣ ያዕ. 3: 4-12፣ ሐዋ. 21: 27-40

የዕለት ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ፥ “ነፋስና ባሕር እንኳ የሚታዘዙለት፥ ይህ ሰው ማን ነው?" እያሉ ተደነቁ።

አዘጋጅ፥ ክቡር አባ ዳንኤል ኃይሌ

“የተከበራችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንደ ምን ሰንብታችኋል! ቅዱስ ቃሉን ሰምተን በኑሮአችን እንድንተረጉመው እግዚአብሔር በጸጋው ይርዳን!  የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕዝቡን ስለ መንግሥተ ሰማያት ካስተማረው ከተራራው ስብከት ቀጥሎ ያለው ነው። ይህም ስለ እግዚአብሔር መንግሥት፣ ስለ ምሕረት፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ ሰላም፣ ስለ እውነተኛ ጸሎት፣ ስለ ጾም እና ስለ ምጽዋዕት ያስተማረበት ነው። ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙሴ ጋር ያነጻጽራል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዲሱ ሙሴ እንደሆነ (ዘጸ. 19)፥ ሙሴ በሲና ተራራ አሥርቱን  ትዕዛዛት ከእግዚአብሔር ተቀብሎ ለእስራኤላውያን እንደሰጣቸው እና ሕዝቡም የተሰጣቸውን ሕግ በተግባር በመተርጎም የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ እንደሚችሉ ያብራራል።

ቀጥሎ ያለው ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተራራው ሰብከት በኋላ የታመመውን ሰው ሲፈውስ፣ አጋንትንም ሲያስወጣ እንመለከታለን። (ማቴ. ምዕ. 8) በተለይም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ከአይሁዳውያን ወገን በለምጽ በሽታ እና በዘር ምክንያት ለተገለሉት የአህዛብ ወገኖች ቅድሚያን ሲሰጥ እና የመቶ አለቃውን አገልጋይ ሲፈውስ እንመለከታልን። ማቴዎስ ወንጌሉን ለአይሁዶች ቢጽፍም ክርስቶስ ለአሕዛብም ጭምር ትኩረት መስጠቱን አመልክቷል። የመቶ አለቃው የሮማውያን የጦር መኰንን ነበር።  ሮማውያን ወታደሮች በአይሁዶች ዘንድ የተጠሉ ቢሆንም የመቶ አለቃው ግን በሕዝቡ ዘንድ እጅግ የተከበረ ነበር። የመቶ አለቃውን አገልጋይ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ለፈውስ ያመጡት አይሁዶች ነበሩ። ከአሕዛብ ወገን ቢሆንም በክርስቶስ ያመነና ከአብዛኞቹ አይሁዳዊያን የተሻለ ነበር። አይሁዶች “እንረክሳለን!” ብለው ስለሚፈሩ ወደ አሕዛብ ቤት አይሄዱም ነበር። የመቶ አለቃውም ክርስቶስ ወደ ቤቱ እንዳይመጣ ከለከለው። ይህን ያደረገበት ምክንያት ራሱን እንደ ኃጢአተኛ ስለሚቆጥር ነበር። ነገር ግን ክርስቶስ አንድ ቃል ቢናገር አገልጋዩን እንደሚፈውሰው ሙሉ እምነት ነበረው። የመቶ አለቃው ክርስቶስ ታላቅ ኃይል እንዳለውና ወደ ቤቱ መምጣት እንደሌለበት አመነ።  የዚህን ሰው እምነት ታላቅነት የምንገነዘበው፣ ስለ ክርስቶስ ኃይልና ከእግዚአብሔር ጋር ስላለው ግንኙነት በማወቁ ብቻ ሳይሆን፥ ክርስቶስ ከሩቅም ሆኖ አገልጋዩን ሊፈውሰው እንደሚችል በማመኑ ነው።

በመስዋዕተ ቅዳሴያችን ላይ፥ “ጌታ ሆይ ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ አይገባኝም፤ ግን አንዲት ቃል ብትናገር ነፍሴ ትድናለች!” በማለት የምንደግመውን ጸሎት ያስታውሰናል። አዎ! ክርስቶስ ወደ እኛ እንዲመጣ የተገባን አይደለንም፤ ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን። በፊቱ ተንበርክከን ራሳችንን ዝቅ ማድረግ አለብን። እግዚአብሔር ትሁታንን ከፍ ያደርጋልና። ሮማዊው መቶ አለቃ በሕዝብ ዘንድ የተከበረ ቢሆንም፣ ለቤተ ክርስቲያን ማሠሪያ ገንዘብ ቢያዋጣም በዚህ አልተመካም። የነገሥታት ንጉሥ ወደ ሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ፊት ራሱን ዝቅ አድርጎ ቀረበ። በክርስቶስ የማዳን ኃይል አመነ።  እኛም በክርስቶስ ፊት እንዴት መቅረብ እንዳለብን፣ ስጋውና ደሙን እንዴት መካፈል እንዳለብን ትልቅ መልዕክት ያስተላልፍልናል።

ሌላው፣ በማቴ. ምዕ. 8 ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የጴጥሮስን አማት እና ሌሎች ሰዎችን እንደፈወሰ ይናገራል። ማቴዎስ በዚህ ታሪክ ውስጥ ትኩረት የሰጠው፣ የብሉይ ኪዳን ትንቢት በክርስቶስ ፍፃሜን ማግኘቱን እና ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ዓይነት ሕመም የመፈወስ ኃይል እንዳለው ነው። እነዚህ ሦስት ተዓምራት የእግዚአብሔር መንግሥት በዓለም ውስጥ የማይጠቅሙ ተብለው ለሚቆጠሩት ሰዎች እንደሆነች ያመለክታል። የመጀመሪያው በለምጽ በሽታ ምክንያት ከኅብረተሰቡ የተገለለው ሲሆን፥ ሁለተኛው በአይሁዳውያን ዘንድ የተናቀ የአሕዛብ ወገን ነበር። ሦስተኛዋ በጾታ ምክንያት በማኅበረሰቡ ውስጥ ዝቅተኛ ቦታ የተሰጣት ሴት ነበረች።

የዛሬ ቅዱስ ወንጌል ቅደም ተከተል፥ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ላይ ሆኖ ሕዝቡን ካስተማረ በኋላ ወደ ተግባር መግባቱን ያሳየናል። የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ብቻ ሳይሆን በሕይወት መተርጎም እንዳለብን የሚጠቁመን ነው። “ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል፤ ዝናብም ወረደ፣ ጎርፍም መጣ፣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት ገፋው፤ በዓለት ላይም ስለ ተመሠረተ አልወደቀም።  ይህን ቃሌን ሰምቶ የማያደርገው ሰው ሁሉ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰነፍ ሰውን ይመስላል ዝናብም ወረደ ጎርፍም መጣ ነፋስም ነፈሰ ያንም ቤት መታው፥ ወደቀም፥ አወዳደቁም ታላቅ ሆነ።” (ማቴ. 7:24-27)

እግዚአብሔር በቃሉ ዓለምን ፈጠረ። በቃሉ ሕይወት አለ። በቃሉ በሽተኞችን ፈወሰ። በቃሉ ሙታንን አስነሳ። በቃሉ የእውሮችን ዓይን አበራ፤ ደንቆሮዎች መስማት ቻሉ። ዲዳዎች መናገር ቻሉ። ያ ቃል ማዕበሉንም ጸጥ አደረገ። ኢየሱስ ክርስቶስ በበሽታ እና በአጋንት ላይ ኃይል እዳለው ሁሉ በተፈጥሮም ላይ ኃይል እንዳለው ያሳያል። ፍጥረታት ይታዘዙለታል። ምክንያቱም እግዚአብሔር አብ ለልጁ ኢይሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ስልጣን ሰጥቶታልና። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ ነፍሱ ከሥጋው ስትለይ ፀሐይ ብርሃኗን  ከለከለች፤ አለቶች ተሰነጣጠቁ፤ ምድርም ተንቀጠቀጠች። ምክንያቱም እግዚአብሔር ፈጣሪያቸው ስለሆነ ሞቱን ማየት አልፈለጉም።

እስራኤላውያን ከግብጽ ሲወጡ ቀይ ባሕር ከፍሎ ያሻገራቸው እግዚአብሔር፣ ዛሬም በአንዲት ትእዛዝ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን እና ታንኳይቱን ሊያወድም የመጣውን ማዕበል ጸጥ አደረገ። ባሕር ሰው ሊቆጣጠረው የማይችለው ግዙፍ ኃይል ያለው ነው። ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ክርስቶስ በታንኳይቱ ውስጥ አብሯቸው እያለ በፍርሃት መውደቃቸው ያለማመናቸው የሚያመላክት ነበር። ኢየሱስም፥ “እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ስለምን ትፈራላችሁ?” አለ። (ማቴ. 8:26) እምነታቸው ትንሽ ነበር። እነ ጴጥሮስ በዓሣ ማጥመድ ዘዴ የተካኑ፣ ዋናን የሚችሉ፣ አደጋ ቢያጋጥም እንኳ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ጠንቅቀው የሚያውቁ ነበሩ። ነገር ግን ከአቅማቸው በላይ የሆነ ከባድ ፈተና ገጠማቸው፥ ማዕበሉ ታንኳይቱን አናወጣት። ይህም በዕውቀታችን እና በገንዘባችን መመካት እንደሌለብን፣ እምነታችንን የሁሉ ቻይ በሆነው እግዚአብሔር ላይ ማድረግ እንዳለብን ያሳስበናል።

በብሉይ ኪዳን ባሕር የመጥፎ መንፈስ ምልክት ነው። የዚህ ባሕር ትርጉም ሰዎች ክርስቶስን በመከተላቸው የሚደርስባቸው መከራና ስደት ሊሆን ይችላል። በፈተና ጊዜ በእምነታችን መጽናት እንዳለብን፥ “እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ!” ያለን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬም በቅዱስ ሥጋውና በክቡር ደሙ ከኛ ጋር እንዳለ ያሳስበናል።  በዚያን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታንኳ ውስጥ ተኝቶ ነበረ። ደቀ መዛሙርት፥ “ልንጠፋ ስንል እንዴት ዝም ትለናለህ?” ብለውት ቀሰቀሱት። ክርስቶስም አብሯቸው የሚሰምጥ እና የሚሞት መሰላቸው። ሞት እግዚአብሔርን ሊያሸንፍ አይቻልም። የፍጥረታት ጌታ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በውሃ ላይ ተራምዶ እንደነበር ዘነጉ። ክርስቶስን መከተል መከራ እንዳለው እና እርሱን ስንከተል እምነታችን ጎደሎ በሆን እንሌለብት ያስጠነቅቀናል። ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ ተኝቶ ነበር” ሲል፣ ኢየሱስ ፍጹም ሰው፣ ከኃጢአት በስተቀር የሰው ሥጋ የለበሰ መሆኑን ያመለክታል እንጂ እግዚአብሔር የሚሆነውን አይመለከትም ማለቱ አይደለም። ቅዱስ ማቴዎስ ክርስቶስን የሰው ልጅ እያለ በብዙ ቦታዎች ላይ ጠቅሷል። ኢየሱስም፥ “ለቀበሮዎች ጉድጓድ፣ ለሰማይም ወፎች ጎጆ አላቸው፤ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት ሥፍራ የለውም።” (ማቴ. 8:20)

ደቀ መዛሙርት በሰው ሕይወት ውስጥ ረሃብ፣ በሽታ፣ ሞት፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ጎርፍ፣ ማዕበል እንዲሁም የሰዎችን ሕይወት የሚያስጨንቁ፣ መናፍስት በዓለም ውስጥ እንዳሉ ተገንዝበዋል። ክርስቶስ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ከእኛ ጋር ያለ አማኑኤል መሆኑን ማስታወስ አለብን።  እኛም እንዲህ ባለ ሁኔታ ብንሸበር፣ አንድም ክርስቶስ ከእኛ ጋር መሆኑን፥ አልያም እርሱ የሕይወት ማዕበሎችን ሁሉ እንደሚቆጣጠር መዘንጋት የለብንም። በእንዲህ ዓይነት ጊዜ ከእኛ የሚጠበቀው በፍርሃት መረበሽ ሳይሆን እምነታችንን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ መጣል እንዳለብን ያሳስበናል።

ቀጥሎም ኢየሱስ ክርስቶስ በአጋንንት የተያዘውን ሰው ፈወሰ። እዚህ ላይ የመናፍስት ዓለም መኖሩን እንገነዘባለን። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም የመጣው አስፈሪውን የሰይጣን መንግሥት ለማፍረስ ነው። ሰዎችን ከአጋንንት ቁጥጥር ሥር ነፃ ማውጣቱ በሰይጣን ላይ ሥልጣን እንዳለው ያስገነዝባል። ያለ እርሱ ሌላ ማንም ሰው ሰይጣንን ሊቆጣጠረው አይችልም። አይሁዳውያንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሲገናኙ በአጋንንት ላይ ሥልጣን እንዳለው ተገነዘቡ። መለኮታዊና ሙሉ የእግዚአብሔር ሥልጣን ያለው «የእግዚአብሔር ልጅ» መሆኑን አወቁ። አጋንንቱም የኋላ ኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚሸነፍ እና ተፈርዶባቸውም ወደ ሲኦል እንደሚወርዱ ያውቁ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ አጋንንቱ ወደ እሪያዎች እንዲገቡ አዘዛቸው። እሪያዎቹም ወደ ባሕር ውስጥ ገብተው ሰጠሙ። ነገር ግን የሚገርመው የአካባቢው ነዋሪዎች ለእሪያዎቹ ሳስተው ክርስቶስ እንዲሄድላቸው ጠየቁት። የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የመናፍስት ዓለም መኖሩን ማወቅ አለባቸው። ሁል ጊዜ ሊያስታውሱት የሚገባው መርህ፥ “በዓለም ካለው ይልቅ በእኛ ያለው ይበልጣል” የሚለውን ነው። (1ኛ ዮሐ. 4፡4) አማኑኤል የሆነው ክርስቶስ ከእኛ ጋር እንዳለና የመናፍስት ዓለም ማሸነፉን ማስታወስ ይገባል። (ዮሐ 16፡33)

ስለዚህ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ትኩረቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስልጣን ላይ ነው። አይሁዳውያንም፥ “ነፋስ እና ባሕር የሚታዘዙለት ይህ እንዴት ያለ ሰው ነው?” እያሉ ተደነቁ። እግዚአብሔር የፍጥረታት ሁሉ ባለቤት ነው። የሚታየውን እና የማይታየውን የሚቆጣጠረው እርሱ ብቻ ነው። በኦሪ. ዘፍ. ምዕ. 7 ላይ፣ በኖኅ ዘመን እግዚአብሔር ለእርሱ የማይታዘዙትን በጥፋት ውሃ ቀጣቸው። እኛም እንደ ነቢያት እና ቅዱሳን ለቃሉ ታዛዦች እንድንሆን፣ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ምስክሮቹ እንድንሆን እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልን! የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን። አሜን።”

03 December 2022, 09:03