ፈልግ

የሲኖዶሳዊ ሂደት አህጉራዊ ጉባኤ ፕሬዚደንቶች እና አስተባባሪዎች ስብሰባ የሲኖዶሳዊ ሂደት አህጉራዊ ጉባኤ ፕሬዚደንቶች እና አስተባባሪዎች ስብሰባ  

በሂደት ላይ ያለው ሲኖዶሳዊ ጉዞ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንደሚያጠናክር ተገለጸ

አዲሱ የአሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ብሮሊዮ በአገራቸው በመካሄድ ላይ ያለውን ሲኖዶሳዊ ሂደት በማስመልከት አስተያየታቸውን አጋርተዋል። ሲኖዶሳዊ ሂደቱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታዩ ልዩነቶች በማስቀረት የአቅመ ደካሞችን እና ከማኅበረሰቡ መካከል የተገለሉ ወገኖች ድምጽ የሚደመጥበት መልካም አጋጣሚ መሆኑን አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለአገሪቱ ጦር ሠራዊት የሚሰጠውን ሐዋርያዊ አገልግሎትንም የሚያስተባብሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጢሞቴዎስ ስለ ሲኖዶሳዊ ሂደት አህጉራዊ ደረጃን በተመለከተ ማክሰኞ ኅዳር 20/2015 ዓ. ም. ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። የአሜሪካ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን በፕሬዚደንትነት እንዲመሩ በቅርቡ የተመረጡት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጢሞቴዎስ በሮም የተካሄደውን የሲኖዶሳዊ ሂደት አህጉራዊ ጉባኤ ፕሬዚደንቶች እና አስተባባሪዎች ስብሰባ ተካፍለዋል። ይህን ስብሰባ በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት በኩል ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ሲኖዶሳዊ ሂደቱ የአቅመ ደካሞች እና ከማኅበረሰቡ የተገለሉ ወገኖች ድምጽ እንዲደመጥ እንዲሁም በአሜሪካ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚንጸባረቁ የሃሳብ ልዩነቶችን ለማስታረቅ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል።

በሮም የተሳተፉበት ስብሰባ ጠቃሚ እንደነበር የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ በስብሰባው ላይ ለውይይት ከቀረቡት ርዕሠ ጉዳዮች አንፃር እያንዳንዱ አህጉራዊ ቡድን በአህጉራዊ ውይይቱ ላይ እንዴት እንደቀረበ፣ ሁሉም አህጉራት የተለያዩ እውነታዎቻቸውን በተለያዩ መንገዶች ማቅረባቸው ትኩረት የሳበ እንደነበር ገልጸዋል። የአሜሪካ እና የካናዳ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በአገራቱ ስፋት እና በሎጂስቲክስ ጥያቄ ምክንያት ውይይቱን በበይነ መረብ አማካይነት ማካሄዳቸውን ያስታወቁት አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ይህን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ አቀራረቦችን መመልከቱ ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸዋል። በአህጉራዊ ስብሰባዎች ላይ የሚቀርቡ ልዩ ልዩ ሃሳቦችን እና አስተያየቶች በተግባር ማዋሉ ቀላል እንደማይሆን የገለጹት አቡነ ጢሞቴዎስ፣ በዚህ ረገድ የአስተባባሪዎች ሚና አስፈላጊ እንደሚሆን፣ የማዳመጥ እና ያዳመጡትን አንድ ላይ የማሰባሰብ ችሎታን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል።

ከሁለቱ አገራት ማለትም ከሰሜን አሜሪካ እና ከካናዳ መልካ ምድር ስፋት አኳያ አኅጉራዊ ውይይቱን በበይነ መረብ አማካይነት እንደሚያካሂዱ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ ጢሞቴዎስ፣ በዚህ መንገድ እንዲካሄድ የወሰኑበት ምክንያት ምዕመናኑን በውይይቱ ላይ ለማሳተፍ በሚል ዓላማ ወደ ሩቅ ቦታ እንዲሄዱ ላለማስገደድ፣ የተገለሉትንና የጉዞ ወጪን መሸፈን የማይችሉትን በቀላሉ ለማግኘት ስለተፈለገ መሆኑን አስረድተዋል። በአኅጉራዊ ውይይቱ ላይ የሁለቱም አገራት ተወካዮች የሚሳተፉበትን ዕድል እንዳመቻቹ ገልጸው፣ ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ አካባቢ አምስት ተወካዮች፣ ከፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ አካባቢ ሁለት ተወካይ እና ከስፓኒሽ ቋንቋ ተናጋሪ አካባቢ ሦስት ተወካዮች እንዲሳተፉ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

ምዕመናን በዚህ የውይይት እና የማስተዋል ሂደት ውስጥ ሌላውን ለማዳመጥ ካላቸው ፍላጎት ጋር ለመደማመጥ የተሰጠው ትኩረት ትልቅ እገዛ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። በቤተ ክርስቲያን ደረጃ ምን ያህል የተስፋፋ እንደሆነ ባያውቁም በአጠቃላይ በአሜሪካ ኅብረተሰብ ዘንድ የሚታይ አንዱ ገጽታ ሌላውን ማዳመጥ አለመቻል መሆኑን ገልጸዋል። “ከእይታ አንጻር መስማት ምትፈልገውን የሚነግርህን ብቻ ነው የምታዳምጠው፤ ካልተስማማህ አትሰማውም!” ያሉት አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ሲኖዶሳዊ ሂደቱን በሚሳተፉት ካቶሊካዊ ምዕመናን መካከል የመንፈስ ቅዱስ መሪነት መኖሩን ተናግረው፣ ይህ ማለት ያመኑበትን ዓላማ ለማስቀየር ሳይሆን የሌላውን ሰው ሃሳብ ሰምቶ ምላሽ የሚሰጡበት ጊዜ እና የሰዎችን እይታ በመጋራት አንድ ላይ ለመሰባሰብ የሚሞክሩበት ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል።

በካናዳ ከሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር አብረው መሥራት ያስደሰታቸው መሆኑን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ የሁለቱ አገራት ሕዝቦች የሚጋሯቸው ባሕላዊ እና ሃይማኖታዊ እሴቶች መኖራቸውንም ተናግረው፣ ሁለቱ አገራት ኅብረታቸውን የሚገልጹባቸው በቂ እውነታዎች እንዳሉ እና ያም አንዱ ወደ ሌላው በመሄድ፣ እርስ በእርስ በመደማመጥ ግንኙነታቸውን የሚያሳድጉበት መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል።

ስለዚህም በሁለቱ አገራት መካከል የሚፈጠረው ከፍተኛ ትውውቅ በቤተ ክርስቲያን በኩል አድናቆት እንደሚሰጠው ገልጸው ከዚያም ወደ ድምዳሜው ሲደረስ በሰሜን አሜሪካ የምትገኘው ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለጠቅላላው ሲኖዶሳዊ ሂደት ማበርከት ያለባት ነገር መኖሩ አስደሳች እንደሚሆን፣ አዲሱ የአሜሪካ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ብሮሊዮ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።  

01 December 2022, 16:41