ፈልግ

የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ስቃይ የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ስቃይ  (ANSA)

የኅዳር 11/2015 ዓ. ም. ዘአስተምሕሮ 1ኛ ሰንበት የወንጌል እና የመልዕክቶች አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት፥ ማቴ. 6:5-15፣ ሮሜ 5: 10-21፣ 1ዮሐ. 2: 1-17፣ ሐዋ. 22: 1-11

በክቡር አባ ዳንኤል ኃይሌ የተዘጋጀ

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንደምን ሰንብታችኋል። ስለማያልቀው ምሕረቱ የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን። በያላችሁበት ቦታ ሁሉ የእግዚአብሔር ፍቅርና ሰላም ይብዛላችሁ። ዛሬ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የማቴ. 6:5-15 ላይ ያለውን የቅዱስ ወንጌላ ቃል እንመለከታለን። በዚህ ቅዱስ ቃል ተባርከን በመልካም መሬት ላይ እንደወደቀው ዘር ሰላሳ፣ ስልሳ፣ መቶ ፍሬ እድናፈራ መንፈስ ቅዱስ ይርዳን።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው ወንጌል እንዴት መጸለይ እንዳለብንና ለምን መጸለይ እንዳለብን ያስተምረናል። ሁሉም ሰው ይህንን የጸሎት መሪህ ቢከተል ውጤታማ እንደሚሆን እገምታልሁ።ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን ጸሎት ሰለሆነ ይህ ጥቅስ የተወሰደው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የተራራው ስብከት (ማቴ. 5:7 ላይ ያለ ሲሆን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ጸሎት ያስተማረበት ሁለተኛው ክፍል ነው። በዚህ ክፍል ሰለ ጸሎት፣ ሰለ ምጽዋዕት እና ሰለ ጾም ይነግረናል።እነዚህ ሦስቱ ነገሮች ከሃይማኖት ጋር የተቆራኙ ናቸው። በሦስቱም ክፍሎች ላይ ያለው ሃሳብ አንድ ነው። ይሄውም የመልካም ሥራዎቻችን ዋጋ የምናገኘው ከሰው ሳይሆን ከእግዚአብሔር እንደሆነ፣ ከሰው ለማግኘት አስበን የምናደርግ ከሆነ ከእግዚአብሔር እደማናገኝ መሆኑን ያሳስበናል። በዚያ ዘመን የነበሩ የሃይማኖት መሪዎች ፈሪሳውያን እና የሙሴ ሕግ መምህራንን ጸሎት እያነጻጸረ ያስተምራቸዋል። እነዚያ ሰዎች ለራሳቸው የግል ጥቅም እና ክብር ብለው ከሰው ሙገሳን እና አድናቆትን ለማግኘት በሚጸልዩበት ጊዜ ሰው እንዲያይላችው በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆምው መጸለይን ይወዳሉ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ጸሎት ምን መምሰል እዳለበት ያስተምራቸዋል።

ብዙን ጊዜ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርት ሲያሰተምር “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁ” ይላቸው ነበር። (ማቴ. 16:6) በዚህ ጊዜ ያስጠነቀቃቸው እንጀራ ውስጥ ስለሚጨመረው እርሾ ሳይሆን ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን ትምህርት መሆኑ ገባቸው። በማቴ. 23 ላይ ስለ እነርሱ ሥራ ይናገራል። ያዘዝኋችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም። ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ።  ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፥ እነርሱ ግን በጣታቸው ስንኳ ሊነኩት አይወዱም። ለሰውም እንዲታዩ ሥራቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለምትዘጉ፥ ወዮላችሁ እናንተ አትገቡም፤ የሚገቡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በጸሎት ርዝመት እያመካኛችሁ የመበለቶችን ቤት ስለምትበሉ፥ ወዮላችሁ፤ ስለዚህ የባሰ ፍርድ ትቀበላላችሁ። እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ስለምታጠሩ፥ ወዮላችሁ። ልብሶቻቸውን ያረዝማሉ በስብሰባዎች እና ግብዣ ላይ የክብር ቦታዎችን ይፈልጋሉ። ፈሪሳዊያን ወግ አጥባቂዎች ናቸው። በሙሴ ሕግ ላይ አቋማቸው የፀና ነው። ሕግ መጠበቃቸው ምንም ክፋት የለውም፤ ነገር ግን የተወቀሱበት ምክንያት ለሰው እያስተማሩ ሰላልኖሩበት ነው። ሕይወታቸው የማስመሰል ሰለ ነበር ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴ. 5:17፥ እኔ ሕግንና ነቢያትን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ለመፈጸም እንጂ ለመሻር አልመጣሁም። እኔ ግን እንዲህ እላችኋለሁ” እያለ በተለያዩ ቦታዎች ሲያስተምር እንመለከታለን። ለምሳሌ የሙሴ ሕግ አትግደል ይላል፤ ቅጣቱም ተመሳሳይ ነው፤ ዓይን ለዓይን፣ እጅ ለጅ። ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ይላል፥ ሰውን የሰደበ ገሃነም ይገባዋል። ስለዚህ ውጭ የሚታየውን ኃጢአት ሰው ሊያወግዘው ይችላል። ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልብና ኩላሊትን የሚመረምር አምላክ ስለሆነ ሰው የሚጠይቀው በውጭ በሚታይ ነገር ብቻ ሳይሆን በልብ ውስጥ ባሰበው ሃሳብ ጭምር እንደሆነ ይናገራሉ። ስለዚህ የኛ ጸሎት ሰዎች እንዲያዪልን ወይም ለማስመሰል መሆን የለበትም። ምናልባት የኛ ጸሎት የዘገየበት ወይም ደግሞ ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረሳው ለምን ይሆን? ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስትጸልዩ እንደ ግብዞች አትጸልዩ ይለናል። ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና። እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል። አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ፤ በርህን ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ። በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃ። ይህ ማለት በሰዎች ፊት መልካም ሥራ አትሰሩ ማለት አይደለም።  “ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ” ተብለናል። (ማቴ. 5:16) የቃል ብቻ ሳይሆን የሕይወት ምስክርነት ይጠበቅብናል።  

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ፥ ስትጸልዩ እንደ ግብዞች አትሁኑ ይላቸዋል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዝ የሚለውን ቃል በብዙ ቦታዎች ተናግሮአል። ግብዝ የሚለው ቃል የግሪክ ቋንቋ ሲሆን ፍቺው ተዋናይ፣ ለሕዝብ ድራማ ወይም ቴያትር የሚያሳይ ማለት ነው። አንድ ተዋናይ ለሕዝብ ቴያትር ወይም ድራማ ሲያሳይ ዓላማው ሕዝብን ለማስደሰት ወይም ለማዝናናት ነው። ጥሩ አድርጎ በሠራ ቁጥር ጭብጭባና ሙገሳን ያገኛል። ዓላማው ሰውን ለማስደስት ነው። ዛሬም እያንዳንዳችን በዚህ ቃል መሠረት የጸሎት ሕይወታችንን እድናይ ኢየሱስ ይጋብዘናል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእልፍኝህ ግባ ሲል አዲስ ሕግ እያወጣ ሳይሆን በርህን ዝጋ፣ ሐሳብህን ሰብስብ፣ አላማህን  ወደ እግዚአብሔር አድርግ ማለቱ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በግልም ሆነ በአደባባይ ብዙ ጊዜ ጸሎት አቅርቧል።

እነርሱ ቃላት ሰለደጋገሙ እግዚአብሔር የሚሰማ ይመስላቸዋል። ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የቃላትን ድግግሞሽ እየተቃወመ ሳይሆን እምነት የጎደለ ጸሎት መሆኑን ሊያሳየን ፈልጎ ነው። ጸሎት ያለ እምነት በወንፊት ውሃ እንደ መቅዳት ነው። ከጸሎት በፊት እምነት ይቀድማል። አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃልና፣ ይህ ማለት እግዚአብሔር የፈለግነውን ነገር ሳንጠይቀው ይሰጠናል ማለት አይደለም። ለእኛ የሚያስፈልገውን ነገር እግዚአብሔር ቢያውቅም እኛም መጠየቅ ልንጠይቀው ይገባል። ጠይቁ ይሰጣችኋል፣ ፈልጉ ታገኛላችሁ፣ በር አንኳኩ ይከፈትላችኋል ብሎናል። ሉቃ 18: 7-8 ሳንታክት መጸለይ እዳለብን ይነግረናል። ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የምገናኝበት ዋናው መንገድ ነው። የክርስቲያኖች ሕይወት የጸሎት ሕይዎት መሆን አለበት። አለ በለዚያ ለፈተና እንጋለጣለን። ክርስቲያን ከጸሎት ውጭ ሊኖር አይችልም። ጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግኙነት በየቀኑ ያድስልናል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ ይለናል፥ በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ሰምህ ይመስገን፣ ስንጸልይ በምሰጋና እድንጀምር፣ ምስጋና ስለሚገባው ምስጋናን እድንሰጥ፣ ውዳሴ ስለሚገባው ውዳሴን እድንሰጥ፣ ከሁሉም ከፍ ያለ ሰለሆነ በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ! እንላለን። ይህ ማለት ክብርን ያመለክታል እንጂ እግዚአብሔር ከእኛ ሩቅ ነው ማለት አይደለም። ፈጣሪ ስለሆነ ከአንደበታችን ምስጋናን ይፈልጋል፣ ውዳሴን ይፈልጋል። በስማይ ላለው እግዚአብሔር በምድር ምላሽ መስጠት ይገባል። ልጆችም ስለ ሆናችሁ እግዚአብሔር አባ አባት ብሎ የሚጮኽ የልጁን መንፈስ በልባችሁ ውስጥ ላከ” (ገላ. 4:6) እርሱ ይወደናል እኛ አናብረዋል፤ እርሱ ይጠብቀናል እኛ እኖራል። አባ ማለት የጠለቀ ወዳጅነትን ያመለክታል፤ የቅርብ ግንኙነትን ያመለክታል። ከእኛ በላይ ለእኛ የሚቀርበን እርሱ ብቻ ነው። የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን ስንል ለነገ መጨነቅ እደሌለብን፣ በርሱ መደገፍ እንዳለብን፣ ስሙን በየዕለቱ መጥራት እንዳለብን፣ በየቀኑ እንድናመሰግነው ስለሚፈለግ ነው። ሕይወታችን በእርሱ እጅ ላይ ናት። እግዚአብሔርን የምንፈልገው በችግራችን ጊዜ ብቻ መሆን የለበትም።

ሌላው እግዚአብሔርን መጠየቅ ያለብን ነገር ቢኖር የዕለት እንጀራን ብቻ ሳይሆን ምሕረትንም መጠየቅ እዳለብን ቃሉ ይናገራል። ክርስቲያን የአንድ ጊዜ ድህነት ሳይሆን የዕለት ተዕለት የሕይወት ጉዞ ነው። በየቀኑ የእግዚአብሔርን ምህረትን መጠየቅ ያስፈልጋል። ለራሳችን ምሕረት ከፈለን ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ምሕረት መስጠት ልንሰጥ ያስፈልጋል። ምሕረትን የሚያደርጉ ብጹአን ናቸው፣ ምህረትን ያገኛሉና።  ምሕረት የእግዚአብሔር ባህሪ ነው። ስለዚህ ለወንድሞቻችን ምሕረት ካደረግን የእርሱን ባሕሪይ እንከተላለን ማለት ነው። “ቁጣቸሁ ሳይበርድ ፀሐይ አይጥለቅባችሁ፣ ለዲያብሎስ ቦታ አትስጡ” ይለናል። (ኤፌ. 4: 26-27) ትንሽ ኃጢአት በምሕረት ካልጥፋች ሞትን ታመጣለች። ምክንያቱም የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና። ምሕረት እርቅን፣ ፍቅርን እና ሰላምን ታወርዳለች። የእግዚአብሔርን ምሕረት የምንፈልግ ከሆነ ለሌሎች ምሕረት ማድረግ ይኖርብናል። በማቴ. 18:24፥ አሥር ሺህ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው አመጡለት። መክፈል ስላልቻለ ጌታው ከሚስቱ ጋር ልጆቹና ያለውን ሁሉ እንዲሸጥና እንዲከፍል አዘዘ። ከዚያም ባሪያው በፊቱ መሬት ላይ ወድቆ “ታገሰኝ! ሁሉንም እከፍልሃለሁ” አለው። ጌታውም ለባሪያ አዘነለትና ፈታው፤ ዕዳውንም ይቅር አለው። “ከወጣ በኋላ ያ ባሪያ አንድ መቶ ብር ዕዳ ያለበትን፣ ከባልንጀራው ባሪያ አንዱን አገኘ። ከዚያም ጉሮሮውን ያዘውና “የተበደረከውን ክፈለኝ” እያለ ያንቀው ጀመር። በዚያን ጊዜ ባልንጀራው ባሪያ መሬት ላይ ወድቆ “ታገሠኝ! እኔም እከፍልሃለሁ” ብሎ ለመነው። እርሱ ግን ፈቃደኛ አልሆነም። ይልቁንም ዕዳውን እስኪከፍል ድረስ ወደ ወህኒ ጣለው። "እያንዳንዳችሁ ወንድማችሁን ከልባችሁ ይቅር ካላላችሁ፥ የሰማዩ አባቴ እንድሁ ያደርግባችኋል” (ማቴ. 18፡35) እኛስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትልቁን ዕዳችንን ይቅር ካለ የወንድሞቻችን ትንሽዋን ኃጢአት እንዴት ይቅር ማለት ይከብደና?

ስንጸልይ “ከክፉ ሁሉ ሰውረን፣ ወደ ፈተናም አታግባን” እንላለን። እግዚአብሔር በፈተና እድንወድቅ አይፈልግም። ማንም ሲፈተን በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም፣ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል። (ያዕ. 1: 13-14) ከዚህ በኋላ ምኞት ጸንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፤ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወልዳለች። እምነታችን ከጎደለና ተጠራጣሪዎች ከሆንን በፈተና ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን። ይህንን አንቀጽ በደንብ ለመረዳት የቅዱስ ጴጥሮስን ታሪክ እደ ምሳሌ ማየት እንችላለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ሌሎች እንኳን ቢክዱህ እኔ አልክድህም” ብሎ ነበር (ማቴ. 26:33) ነገር ግን ከትንሽ ሰዓታት በኋላ አላውቅህም አለ። እደማያውቀው በጠንካራ ቋንቋ ተናገረ። አዳምም ገነትን የመሰለ ቦታ ያጣው በፈተና ስለወደቀ ነው። የተፈቀደውን ትቶ ያልተፈቀደውን ስላደረግ ነው። በእግዚአብሔር ቃል ስላልጸና ነው። ፈተና ሁሉ ጊዜ ወደ ሕይወታችን ሲምጣ ትንሽ ነገር መስሎ ነው። ነገር ግን ድክመታችን ከገባው ሕይወታችንን ወደ ገደለ ይከተዋል። ጻድቁ ኢዮብ በሰይጣን ተፈትኗል። ሰይጣንም ስለ ኢዮብ ለእግዚአብሔር ጥያቄ አቀረበ። ኢዮብ ላንተ የታዘዘው ቤቱን እና በዙሪያው ያለውን ሁሉ ስለባረክለት ነው። የእጁን ሥራ ስለባረከለት ነው። ይህን ሃብቱን ብትመታ አንተን ይስድባል፣ ይክዳል አለው። ኢዮብ ልጆች ኃጢአት ሲሠሩ መስዋዕት ያቀርብ ነበር። ነገር ግን ለራሱ አያቀርብም ነበረ። (ኢዮ. 9:9-11) ነገር ግን ሃብት ንብረቱን እና ልጆቹን ባንድ ጀንበር አጣ። ኢዮብ በእምነቱ ጸና፣ እግዚአብሔርን አመስገነ፣ እግዚአብሔር ሰጠ፣ እግዚአብሔር መለሶ ወሰደ። ስለዚህ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን! አለ። ይህ በጣም ትልቅ እምነት ነው። ትልቅ ጸሎት ነው። ማነው ከእኛ ንብረቱ ወድሞ ልጁ ሞቶበት እግዚአብሔርን የሚያመሰግን? ወንድሞቼ እና እህቶቼ እግዚአብሔር ከችግሮቻችን በላይ ነው። እርሱ ለእኛ ከኛ በላይ ያስባል። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች በላከው የመጀመሪያ መልዕክቱ፥ 10:12 ላይ “የቆመ የሚመስል እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ!” እያለ ይመክረናል። ስለዚህ ወደ ፈተና እዳንገባ ተግተን መጸለይ ያስፈልገናል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን “አባታችን ሆይ!” ጸሎት መዝጊያው ስሙን በማክበር ነው። መንግሥት፣ ክብር፣ ሃይል ያንተ ናትና። ጸሎት በምስጋና ተጀምሮ በምስጋና ማለቅ ያለበት። በውስጡ ብዙ ልመናዎች ቢኖሩም በልምና አይጀመርም። መጀመርያ ሰጭውን ማመስገን እዳለብን፣ መንግሥቱን ማስቀደም እንዳለብን ያሳስበናል። ሁሉ በእጁ ነው። እርሱ አልፋና ኦሜጋ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካችን ልክ እንደ ጻዲቁ ኢዮብ እድናመስገነው ጸጋውን ያብዛልን። ቃሉን በልቦናችን ውስጥ ያቆይልን፤ የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን። አሜን።

19 November 2022, 18:22