ፈልግ

የኅዳር 18/2015 ዓ. ም. ሰንበት ዘቅድስት (ዘአስተምሕሮ 2ኛ) የወንጌል አስተንትኖ የኅዳር 18/2015 ዓ. ም. ሰንበት ዘቅድስት (ዘአስተምሕሮ 2ኛ) የወንጌል አስተንትኖ  (ANSA)

የኅዳር 18/2015 ዓ. ም. ሰንበት ዘቅድስት (ዘአስተምሕሮ 2ኛ) የወንጌል አስተንትኖ

የዕለቱ ንባባት፥ ዮሐ. 5:16-27 ፣ ቆላ. 1: 12-29፣ 1ጴጥ. 1: 13-20፣ ሐዋ. 19: 21-40 

የዕለቱ ቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ፥ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚታይ የእግዚአብሔር ቃል ነው!”

አዘጋጅ ክቡር አባ ዳንኤል ኃይሌ

የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች እንደምን ሰንብታችኋል! በዚህች ሰዓት ፈቃዱ ሆኖ ቃሉን እንድንሰማ ላደረን አምላካችን ክብር እና ምስጋና ለስሙ ይድረሰው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው የወንጌል ቃል እንዲህ ይለናል፥ “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል፣ እኔም ደግሞ እሠራለሁ።”  እግዚአብሔር ዛሬም በቃሉ ያስተምረናል፣ ይመክረናል፣ ይገስጸናል፣ እውነተኛውን የሕይወት መንገድ ያሳየናል። የእግዚአብሔር ቃል ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም፣ ሁሌም አዲስ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዛሬ ለአይሁዳውያን ወይም ደግሞ በዚያ ጊዜ ለነበሩት የሃይማኖት መሪዎች፣ ለፈሪሳውያን እና ለጻፎች ቃሉን እንዴት በሕይወታቸው መተርጎም እና መኖር እንዳለባቸው ያሳስባቸዋል። ቅዱስ ዮሐንስ በጻፈው የክርስቶስ ወንጌል ሁለት መሠረታዊ ነጥቦችን ያነሳል። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን በማመን ሕይወትን ማግኘት እና የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ባለማመን የሚሰጥ ፍርድ መኖሩን ያመለክታል። ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም፤ ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም፤ ቃሌን የሚሰማ የላከኝን የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም። አብ ለልጁ ሁሉንም ስልጣን ሰጥቶታል። ሕይወት የሚሰጠው እርሱ መሆኑን እንደሁም ፍርድንም እንደሚሰጥ ያስረዳል። “እኔ እውነት፣ መንገድ፣ ሕይወት ነኝ።” (ዮሐ. 14:6) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነት ስለሆነ ብዙ ጊዜ ሲናገር “እውነት፣ እውነት እላችኋለሁ!” እያለ ያስተምራቸዋል። ስለዚህ አብ ሕይወትን እንደሚሰጥ ሁሉ ወልድም ሕይወትን ይሰጣል። “አብን የሚያከብር ወልድን ያከብራል።” (ሉቃ. 17:20)

“የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናት” ይላል። ክርስቶስ የእግዚአብሔር መንግሥት ነው። ኢየሱስ በመካከላቸው ቆሞ  የሚናገረውን አላመኑም ነበር። የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አልተቀበሉም። እግዚአብሔር አብ በላከው ልጁ አለማመን ወደ ፍርድ ይወስዳል። “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት።” (ማቴ. 17:5) ነገር ግን እርሱን ከመስማት ይልቅ ሊገድሉት አሰቡ። በዘመናችንም የክርስቶስን ባህሪ  በተመለከተ ክርክር እና  መለያየት አለ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ፈሪሳውያን እንዲያምኑ ምልክቶችን ተጠቅሟል። በብሉይ ኪዳን ውስጥ ስለ የኢየሱስ ክርስቶስ በብዛት ተጠቅሶ እናገኛለን። ኦሪት ዘጸአት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከባርነት ነፃ እንደሚያወጣ ይናገራል። የነቢያት ትምርት ሁሉ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያተኮሩ ናቸው። የብሉይ ኪዳን ተስፋዎች በኢየሱስ ክርስቶስ ፍፃሜን አገኝተዋል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከብሉይ ኪዳን እየጠቀሰ ያስተምራቸው ነበር። የክርስቶስ ተዓምራት ወይም ምልክቶች አቅጣጫን የሚያሳዩት ወደ እርሱ ነው። አይሁዳውያን መጥምቁ ዮሐንስን፥ “ይመጣል የተባለው አንተ ነህን?” ብለው በጠየቁት ጊዜ እርሱ ግን ክርስቶስ እንደሆነ ነገራቸው። “እኔ በበረሃ የምጮህ  ድምጽ ነኝ፤ እርሱ ግን ቃል ነው!” በማለት መሰከረ። ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ፥ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ነበረ፤ ቃልም  በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” በማለት ይናገራል። (ዮሐ. 1:1) እግዚአብሔር ዓለምን የፈጠረው በቃሉ ነው። በዘፍ. 1 ላይ የተገለጸው ይህ ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።

እግዚአብሔር በተለያዩ ጊዜያት በነቢያቱ አማካይነት ቃሉን አስተላልፏል። ነገር ግን እስራኤላዊያን ትክክለኛውን የእግዚአብሔርን ቃል ሊኖሩበት አልቻሉም። ነብያትን ገደሉ፤ የቃሉ ባለቤት የሆነው ክርስቶስንም ለመግደል አስቡ። በነብያትና በመጥምቁ ዮሐንስ መካከል የ400 ዓመት ልዩነት አለ። ለ400 ዓመታት እግዚአብሔር ነቢያትን አልላከም ነበር። በእግዚአብሔር እና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት ተቋርጦ ቆየ። እግዚአብሔር የሚናገርበት ጊዜ አለ፤ እንዲሁም ዝምታን የሚመርጥበት ጊዜ አለ። ስለዚህ ወንድሞችና እህቶች ሆይ! እግዚአብሔርን ሲናገር ቃሉን ሰምተን ንስሐ ገብተን ወደ እርሱ መመለስ ይኖርብናል። ሰው ከሞተ በኋላ በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት አይሳተፍም፤ ምስጢር ንስሐንም መቀበል አይችልም። ስለዚህ እግዚአብሔር የሰጠንን የንስሐ ጊዜን በትክክል መጠቀም ይኖርብናል። ዕድሜያችንን ሁሉ ምድራዊ ነገሮች ብቻ እያሰብን፣ ሰማያዊውን ቤት እንዳናጣ ጊዜያችንን በከንቱ ማባከን  የለብንም። እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፤ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤  ክፉ ሰው መንገዱን በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥ ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ።” ይላል። (ኢሳ. 55:6)

በብሉይ ኪዳን ውስጥ 613 ሕጎች አሉ። ከእነዚህ መካከል 365ቱ አድርግ የሚሉ ሲሆን 240ው አታደርግ የሚል ነው። በአንድ ዓመት ውስጥ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ቀናት አሉ። ይህ ማለት በየቀኑ መልካም ሥራ መሥራት እንዳለብን፣ ለነፍሳችን የጽድቅ ሥራ ማዘውተር እንዳለብን እና ትእዛዛቱን በሕይወታችን እንድንተረጉም ያሳስበናል። ዛሬም በወንጌሉ የሰማነው፥ “ኢየሱስ ሰንበትን አላከበረም፤ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር አስተካከለ፤ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ አለ!” የሚሉ ተቃውሞዎች ነበሩ። ሰንበት ከአሥርቱ ትዛዛት መካከል ሦስተኛው ሲሆን እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሲና ተራራ ሰጣቸው። እግዚአብሔር ዓለምን በስድስት ቀናት ከፈጠረ በኋላ በሰባተኛው ቀን አረፈ። (ዘፍ. 2) ይህ ቀን እስራኤላዊያን ከግብጽ ውጥተው ማርና ወተት ወደሚፈስባት ከነዓን ምድር የገቡበትን ቀን የሚያስታስ ነው። ከባርነት ወደ ነጻነት የተሽገሩበት መታሰብያ ነው። በባርነት ዕረፍት የለም፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር ድንቅና ተዓምራዊ ዕረፍትን ያገኙባት ቀን ናት።

 ኢየሱስ ለ38 ዓመታት ሙሉ የታመመውን ሰው በሰንበት ቀን ስላዳነ አሳደዱት፤ ሊገድሉትም ፈለጉ። “የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ እንዴት በሰንበት ቀን ያልተፈቀደውን ያደርጋል?” አሉ። በዚያን ጊዜ ኢየሱስ በሰንበት ቀን በእርሻ መካከል ያልፍ ነበርና ደቀ መዛሙርቱ ተርበው ስለነበር እሸት እየቀጠፉ ይበሉም ጀመር። ፈሪሳውያንም ይህን አይተው፥ “እነሆ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ማድረግ ያልተፈቀደውን ያደርጋሉ” አሉት። እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፥ “ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩት በተራቡ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዲገቡ ያደረጋቸው ካህናትን ብቻ ነበረ። እርሱና ከእርሱ ጋር የነበሩት ሊበሉት ያልተፈቀደውን የመሥዋዕቱን ኅብስት እንደ በላ አላነበባችሁምን? ነገር ግን እላችኋለሁ፥ ከመቅደስ የሚበልጥ ከዚህ አለ፤ መሥዋዕትን ሳይሆን ምሕረትን እወዳለሁ! ያለው ምን እንደሆነ ብታውቁስ ኃጢአት የሌለባቸውን ባልኰነናችሁም ነበር፣ የሰው ልጅ የሰንበት ጌታ ነውና።” (ማቴ. 12)

 ኢየሱስም ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ሰውዬው ወዲያው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ይህም የሆነው በሰንበት ቀን ነበር። ስለዚህ አይሁዳውያን የተፈወሰውን ሰው፥ “ሰንበት ነው፣ አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም” አሉት። እርሱ ግን “ያ ያዳነኝ ሰው አልጋህን ተሸክመህ ሂድ!” አለኝ ብሎ መለሰላቸው። (ዮሐ. 5:8-10) ተቃውሞው “ለምን በሰንበት ቀን ይፈውሳል? እንዴት በሰንበት ቀን አልጋውን እዲሸከም ፈቀደ? ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውየውን ለምን በሰንበት ቀን መፈወስ ፍለገ? ለምን ሌላ ቀን አልመረጠም? የሚል ነበር። ሰንበትን የመረጠበት ምክንያት ኢየሱስ ክርስቶስ ከኃጢአት ባርነት ነጻ እንደሚያወጣ እና የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን እንዲያምኑ ነው። በነቢዩ ኢሳያስ የተነገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ! (ኢሳ. 35:5-7) በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል፤ የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል፤ አንካሳ እንደ ሚዳቆ ይዘላል፤ የዲዳም ምላስ ይዘምራል፤ በምድረ በዳ ውሃ፣ በበረሀም ፈሳሽ ይፈልቃልና።

ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት በኩል ሲናገር፥ “ሁሉን ወራሽ ባደረገው፣ ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” ይላል። (ዕብ 1:1) እውነተኛውን ሰንበት፣ እውነተኛውን ጸሎት፣ እውነተኛውን ምጽዋዕት፣ እውነተኛውን መንገድ፣ እውነተኛውን ሕይወት እና እውነተኛውን ምሕረት የሚያሳየን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ። ሰንበት የተፈጠረው ለሰው ልጅ ነው እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም። (ማር. 2:27) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለጥያቄዎቻቸው መልስ ሲመልስ እንዲህ አለ፥ “እስቲ ከእናንተ በጉ በሰንበት ቀን ጉድጓድ ውስጥ ቢገባበት የማያወጣ ማን ነው?” ኢየሱስም የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው።” አለ። (ዮሐ. 4:34) ሰው ከሰንበት ይበልጣል፤ ክርስቶስ የተላከበት ዋና ዓላማ ነፍስን ለማዳን ነው። እግዚአብሔር በጊዜ አይወሰንም፤ ትላንትም ዛሬም ሁሌም ይሠራል። በሰንበት ቀን እግዚአብሔር ሕይወትን ይሰጣል፣ ይፈጥራል። ሰው በሰንበት ቀንም ይወለዳል። “ዓይኖቼን ወደ ተራሮች አነሣሁ፤ ረዳቴ ከወዴት ይምጣ? ረዳቴ ሰማይና ምድርን ከሠራው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። እግርህን ለመናወጥ አይሰጠውም፤ የሚጠብቅህም አይተኛም፤ እነሆ እስራኤልን የሚጠብቅ አይተኛም አያንቀላፋምም። እግዚአብሔር ይጠብቅሃል፤ እግዚአብሔርም በቀኝ እጅህ በኩል ይጋርድሃል፤ ፀሐይ በቀን አያቃጥልህም ጨረቃም በሌሊት እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል፤ ነፍስህንም ይጠብቃታል፤ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ዘለዓለም እግዚአብሔር መውጣትህና መግባትህን ይጠብቃል።” (መዝ. 121)

ስለዚህ ወንድሞቼና እህቶቼ ሆይ! የሰንበትን እውነተኛ ሕይወት እንድንኖር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቃል ያሳስበናል። እግዚአብሔርም፥ “ከመስዋዕት ይልቅ ምሕረትን፥ ከሚቃጠልም መስዋዕት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ እወዳለሁና።” (ሆሴ. 6:6) በሰንበት ቀን ለወንድሞቻችን ምሕረት ሳንሰጥ ለእግዚአብሔር ገንዘብ፣ ሻማ እና እጣን ከጸሎታችን ጋር ብናቀርብ አይቀበለንም። ሰው ፊትን ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ይመለከታል። የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ቃል በቃል መፈጸም ብቻ ጽድቅን አያስገኝም። ለምሳሌ “አትግደል፣ አታመንዝር፣ አትስረቅ” ይላል። አንድ ሰው ያልገደለ፣ ያላመነዘረ፣ ያልሰረቀ፣ የሌላን ያልተመኘ እና የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ጠብቂያለሁ ብሎ ሊያስብ ይችላል። የንስሐ ጸሎት ስንጸልይ፥ በማሰብ፣ በመናገር፣ በማድረግም እንላለን። ኃጢአት  የሚጀመረው   ከማሰብ  ነው። ልባችን ክፉ ነገርን፣ ተንኮልንና ቂምን ሊመኝ ይችላል። ይህ እንደ ኃጢአት እንደሚቆጠር ጌታችን ኢየሱስ  ክርስቶስ ተናግሯል። በልብ ውስጥ የተጠነሰሰ ክፉ ሃሳብ ከልብ ሲወጣ ወደ ጠብ፣ ክርክር እና ግዲያም ይመራናል።

በዛሬው ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልባቸው ለተዘጋባቸው የአይሁድ የሃይማኖት አባቶች እና ለእኛ እንዲህ በማለት ያሳስበናል፥ “መስማት ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትን ታያላችሁና አትመለከቱም።” (ማቴ. 13:13)  በዓይናቸው እንዳያዩ፥ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፥ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፥ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአልና፤ ጆሮአቸውም ደንቁሮአል፣ ዓይናቸውንም ጨፍነዋል የሚል የኢሳይያስ ትንቢት በእነርሱ ይፈጸማል። ወንድሞችና እህቶቼ! እግዚአብሔርን የምናይበት መንፈሳዊ ዓይናችን ልብ ነው። ልብ ከታወረ እግዚአብሔርን ማየት አንችልም። ልብ ከታወረ የወንድሞቻችን መልካም ነገር ማየት አንችልም። ልብ ከታወረ ለወንድሞቻችን ይቅርታ ማድረግ ይከብደናል። “ልበ ንጹሖች ብፁዓን ናቸው፥ እግዚአብሔርን ያዩታልና።” (ማቴ.5:8)  

ስለዚህ ወንድሞቼና እህቶቼ! ዛሬ እግዚአብሔር እውነተኛ ክርስቲያናዊ ኑሮ እንድንኖር ያሳስበናል። ሰንበት የኃጢአት ባሪያ የምንሆንበት ቀን ሳይሆን ነፍሳችን ከኃጢአት ነፃ የምትሆንበት ቀን ነው። በሰንበት የእግዚአብሔርን ቃል የምንሰማበት፣ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ስጋውና ክቡር ደሙን በመካፈል ሕይወት የምናገኝበት ዕለት ናት። ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ በትንሣኤው ኃጢአትን ያሸነፈበት ቀን ነው። ሰንበት የምሕረት ቀን ናት። ሰንበት በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ያለው የጥል ግድግዳ የፈረሰበት ቀን ናት። በአይሁድና በግሪክ፣ በባሪያና በነፃ ሰው፣ በወንድና በሴት መካከል ልዩነት የለም፤ ሁላችሁም በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ናችሁና።” (ገላ.328)  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ይላል፥ “እናንተ ሸክም የከበደባችሁ ወደ እኔ ኑ፥ እኔ ዕረፍት እሰጣችኋለሁ፤ ቀንበሬን ተሸከሙ ከእኔም ተመሩ፣ እኔም በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና።” (ማቴ. 11:2830) ስለዚህ ከትዕዛዛቶች ሁሉ በላይ የሆነውን፥ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ፣ በፍጹም ኃይል፣ በፍጹም ነፍስ እንድንወደው እና ባልንጀሮቻችንን እንደራሳችን እንድንወዳቸው እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልን! የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ከሁላችን ጋር ይሁን። አሜን።

26 November 2022, 10:40