ፈልግ

የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ - ግብጽ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ - ግብጽ   (AFP or licensors)

በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የቤተ ክርስቲያንን እርምጃ የሚያጠናክር ስብሰባ ተካሄደ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪነት ግብጽ ውስጥ ከተካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በመቀጠል ካቶሊካዊ ምዕመናን አካባቢያዊ ቀውስን ለመከላከል የሚያደጉትን ጥረት ከፍ ለማድረግ ያለመ የአውሮፓ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” እንቅስቃሴ አካል የበይነ መረብ ስብሰባ ማዘጋጀቱ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአውሮፓ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ኅብረት አካል የሆነው ቡድኑ፣ በበይነ መረብ አማካይነት የሚደረገው ስብሰባ ዓለማ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ጋር ድምጻቸውን በማስተባባር ፈለጋቸውን ለመከተል መሆኑን ቡድኑ ገልጿል። በአውሮፓ የሚገኝ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” አሊያንስ፣ ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ጋር በጥብቅ በመቆራኘት ፍትሃዊ የስነ-ምህዳር ጽንሰ-ሀሳብን የሚያበረታታ ድርጅት እንደሆነ ታውቋል።

ሥራቸው በሦስት መሠረታዊ ርዕሦች ላይ መመስረቱን የገለጹት የአውሮፓ "ውዳሴ ላንተ ይሁን” ንቅናቄ የፕሮግራም ዳይሬክተር ወ/ሮ ላውራ ሞሮሲኒ፣ ርዕሦቹም ሥነ-ምህዳራዊ መንፈሳዊነት፣ ተግባር እና ጥሪ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአየር ንብረት ቀውስ የቤተ ክርስቲያኑ ሚና

በአውሮፓ የውዳሴ ላንተ ይሁን ንቅናቄ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ክቡር አባ ኤድዋርዶ አጎስታ ሳካሬል፣ የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ከተካሄደበት ከግብጽ ሻርም ኤል ሸይክ ከተማ ባስተላለፉት መልዕክት እንደተናገሩት፣ ቫቲካን በአየር ንብረት ቀውስ ውይይት ላይ ያላትን ንቁ አቋም ጠቅሰው፣ የመጨረሻ ውሳኔዎች ከተፈረሙ በኋላ ለዓመታት የሞራል መመሪያ እና ጥቆማዎችን የመስጠት ግዴታ ያለባት ታዛቢ ሀገር መሆኗን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአካባቢያዊ ቀውስ ጋር በተያያዘ እ. አ. አ 2015 ዓ. ም. የጸደቀውን የፓሪስ ስምምነት ተከትሎ ቫቲካን በይፋ የዓለም አቀፉ ውይይት አካል መሆኗን ክቡር አባ ኤድዋርዶ ገልጸዋል።

አሁን የተግባር ወቅት ነው!

በዛምቢያ የኢየሱሳውያን ማኅበር የፍትህ እና ሥነ-ምህዳር ኔትወርክ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ክቡር አባ ቺሉፍያ የበርካታ አፍሪካውያንን ምሳሌ በማቅረብ ባሰሙት ንግግር፣ እንደ ጎርፍ፣ አውሎ ንፋስ እና የሙቀት ማዕበል በመሳሰሉ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች ሕዝቦች መጠቃታቸውን አስረድተዋል። ሁላችን ወንድማማቾች ነን የሚለውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በማስታወስ እንደተናገሩት፣ ያደጉት አገራት በማደግ ላይ ባሉት አገራት ላይ ያላቸውን ሃላፊነት በማጉላት፣ ከመጠን ያለፈ የኢንዱስትሪ መስፋፋት ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ገልጸው፣ የሥነ-ምግባር ጉዳይ መሆኑንም በማስረዳት “በዚህ ሁኔታ ሁላችንም እንዴት ጥሩ ሕይወት መኖር እንችላለን?” በማለት ጠይቀዋል።

እምነትን እና ተስፋን ማሳደግ

በቅርብ ዓመታት ውስጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ልትጀምረው የሚገባቸውን ተጨባጭ ተግባራት ለማሳየት የሞከረው ውይይቱ፣ እንደ ሃይማኖት መሪዎች እና ምዕመናን ተስፋችንን በማበረታታት፣ ነገሮችን ለመለወጥ የሚያስችል ታላቅ ኃይል እግዚአብሔር እንደሰጠን መገንዘብ አለብን በማለት ክቡር አባ ቺሉፍያ ተናግረው፣ “ካቶሊካዊ ምዕመናን በዚህ ጉዳይ ላይ ማሰብ፣ መፈላሰፍ እና መሞከር አለባቸው” በማለት አሳስበዋል። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መጀመሪያ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነገሮችን እንዴት መለወጥ እንደምንችል ማሰብ እንደሚገባ ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውሰው፣ አሁንም ቢሆን ሕዝብን ማስተባበር እና እምነታቸውን መጠበቅ እንደሚገባ ክቡር አባ ቺሉፍያ አሳስበዋል።

16 November 2022, 15:15