ፈልግ

የሕንድ ሴቶች በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው የሕንድ ሴቶች በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው  

የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ዕቅድ ለአካባቢ ጥበቃ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑ ተገለጸ

ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተወጣጡ ወጣት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ከመስከረም 12-14/2015 ዓ. ም. ድረስ በጣሊያን አሲሲ ከተማ ስብሰባቸውን ሲያካሄዱ ቆይተዋል። ይህን ስብሰባ ከተካፈሉት እንግዶች መካከል አንዱ የሆኑት የ “ፍጥረት ጥበቃ” መርሃ ግብር አስተባባሪ ክቡር አቶ ጁሴፔ ላንዚ፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መሠረት በማድረግ ለስብሰባው ተካፋዮች ገንቢ የሆኑ ተጨባጭ ድጋፎችን ከማካፈል በተጨማሪ በተደጋጋሚ ሊገለገሉበት እና ተመልሶ ከአፈር ጋር ሊቀላቀል የሚችሉ ቁሳቁሶችን በስጦታ ለሰብሰባው ተካፋዮች አድለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የ “ፍጥረት ጥበቃ” መርሃ ግብር፣ በቅዱስ ፍራንችስኮስ የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ዕቅዶች መካከል የተቃጠለ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ የተወጠነ መርሃ ግብር መሆኑን የገለጹት የመርሃ ግብሩ አስተባባሪ ክቡር አቶ ጁሴፔ ላንዚ፣ ከወጣት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ስብሰባ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ተጨባጭ ሃሳቦችን ለስብሰባው ተካፋዮች አቅርበዋል። ለስብሰባው ተካፋዮች በምሳሌነት ካቀረቧቸው ተጨባች መንገዶች መካከል አንዱ የላስቲክ ጠርሙሶችን ከመጠቀም ይልቅ በምትኩ የውሃ መያሻ ኮዳዎችን ማደላቸውን እና ለስብሰባው ተካፋዮች የቀረቡት ምግቦች በጣሊያን ኡምብሪያ ክፍለ ሀገር የመሬት መንቀጥቀጡ በተከሰቱባቸው አካባቢዎች የተዘጋጁ ምግቦች መሆናቸው ገልጸዋል። ዓላማውም በመሬት መንቀጥቀጥ የተጎዱ የአካባቢው ነዋሪዎችን ለመርዳት መሆኑን ገልጸው፣ እንቅስቃሴው በአካባቢ ጥበቃ ላይ ያለውን ተፅእኖ ለመቀነስ ጠቃሚ እሴት መሆኑን አስረድተዋል።

የቅዱስ ፍራንችስኮስ የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ የሚያግዝ ሥነ-ምህዳራዊ ቁሳቁስ

በጣሊያን፣ አሲሲ ከተማ ከመስከረም 12-14/2015 ዓ. ም. ድረስ የተካሄደውን ወጣት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ስብሰባን ለተካፈሉት አባላት ልዩ ሥነ-ምህዳራዊ ቁሳቁሶች ተዘጋጅተው መቅረባቸውን የገለጹት የ “ፍጥረት ጥበቃ” መርሃ ግብር አስተባባሪ ክቡር አቶ ጁሴፔ ላንዚ፣ ቁሳቁሶቹ የሚታጠቡ እና እንደገና ጥቅም ላይ መዋል የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረው፣ በስብሰባው ቀናት ውስጥ በጎ ፈቃደኞች ተሰማርተው ወጣቶቹ የቆሻሻ አሰባሰብ አመክንዮ እንዲገነዘቡ ማገዛቸውን ገልጸዋል። ክቡር አቶ ጁሴፔ ላንዚ በማከልም እያንዳንዱ ወጣት ይህን ተገንዝቦ ቆሻሻን በትክክል የመለየት ሃላፊነት ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዛፎች በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚደርስ ተፅእኖን ይቀንሳሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ያደረጓቸው “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” እና “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚሉ ሁለቱ ቃለ ምዕዳኖች ለ “ፍጥረት ጥበቃ” መርሃ ግብራቸው መሠረት መጣላቸውን የገለጹት ክቡር አቶ ጁሴፔ ላንዚ፣ በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚደርስ ተፅእኖን ለመቀነስ ሙከራ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ የዛሬውን ግዙፍ ስብሰባ ጨምሮ ሌሎች ማኅበራዊ ዝግጅቶች በዚህ መልኩ ክብደት ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል። ከሌሎች ዝግጅቶች በተለየ መንገድ በስብሰባው ወቅት ወደ ከባቢ አየር የሚገባውን የተቃጠለ ጋዝ ልቀትን መጠን በሳይንሳዊ መሣሪያ መለካት ያስደነቃቸው መሆኑን ገልጸዋል።  

ይህን ማድረግ አይቻለንም ብለን ሙሉ በሙሉ ከመተው ይልቅ በመኖሪያ አካባቢያችን ላይ የሚደርሱ ተፅዕኖችን ለመቀነስ ዛፎችን መትከል እንደሚቻል፣ በዘላቂነት ሪፖርቶችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ይህ ተግባር ሊከናወን የሚገባው በቤተ ክርስቲያን አካባቢ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ መንግሥታዊ እና ባሕላዊ ዝግጅቶች በሚቀርቡባቸው ቦታዎች ሁሉ መከወን እንዳለበት የ “ፍጥረት ጥበቃ” መርሃ ግብር አስተባባሪ የሆኑት ክቡር አቶ ጁሴፔ ላንዚ አሳስበዋል።  

24 September 2022, 16:51