ፈልግ

ከወጣት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ስብሰባ ተካፋዮች መካከል አንዷ ከወጣት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ስብሰባ ተካፋዮች መካከል አንዷ 

የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ጠቃሚ ሃሳብ ወደ መላው ዓለም የሚደርስ መሆኑ ተገለጸ

በጣሊያን፣ አሲሲ ከተማ ከመስከረም 12-24/2015 ዓ. ም. ድረስ በተካሄደው ወጣት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ስብሰባ ላይ የተገኙ ወጣቶች የቀሰሙት ልምድ ወደ መላው ዓለም የሚደርስ መሆኑ ተገልጿል። ይህ የተገለጸው ስብሰባውን በማስመልከት የቫቲካን ሬዲዮ ባቀነባበራቸው የተለያዩ ዝግጅቶች በኩል ሲሆን፣ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስም ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 14/2015 ዓ. ም. በተጠናቀቀው ስብሰባ ላይ መገኘታቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሐሙስ መስከረም 12/2015 ዓ. ም. በተጀመረው ስብሰባ ላይ የተገኙት የልዩ ልዩ አገራት ወጣቶች በቅዱስ ፍራንችስኮስ የትውልድ ከተማ አሲሲ ተገናኝተው ልዩ ልዩ አውደ ጥናቶችን እና ውይይቶችን መካፈላቸው ታውቋል። በስብሰባው መጀመሪያ ቀን በተለያዩ የዓለም ክልሎች በተግባር የዋሉ ፕሮጀክቶች በአርዓያነት መቅረባቸው ታውቋል። ወጣቶቹ በከተማው ውስጥ በተዘጋጁ ልዩ ልዩ አካባቢዎች በመገኘት ውይይቶችን ያካሄዱ ሲሆን፣ ዓርብ መስከረም 13/2015 ዓ. ም. በነበራቸው መርሃ ግብር ቅዱስ ፍራንችስኮስ የነበረባቸውን ሥፍራዎች ጎብኝተው የግል ጸሎት እና አስተንትኖ ማድረጋቸው ታውቋል። ወጣቶቹ በዓለማችን ውስጥ አዲስ የምጣኔ ሃብት ሥርዓትን የሚያሳድጉ ፍሬዎች እንደሚሆኑ ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ተስፋ ማድረጋቸው ታውቋል።

ሁለቱን የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኖችን ማለትም “ውዳሴ ላንተ ይሁን” እና “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚሉ ቃለ ምዕዳኖችን መሠረት ያደርገው ስብሰባው በመጀመሪያ ቀኑ በእርሻ እና በፍትህ ላይ ተወያይቶ እንዲሁም የኃይል አቅርቦት እና ድህነትን መዋጋት በሚሉት ርዕሠ ጉዳያዮች ላይም ውይይቶችን ማካሄዱ ታውቋል። የስብሰባው ሁለተኛ ቀን የተገባደደው ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የመላዕክት ንግሥት ባዚሊካ በተደረገው ጉብኝት መሆኑ ታውቋል። ለስብሰባው በወጣው መርሃ ግብር መሠረት ቅዳሜ መስከረም 14/2015 ዓ. ም. ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በአሲሲ ከተማ ተገኝተው ከስብሰባው ተካፋዮች ጋር ከተገናኙ በኋላ ወጣቶቹ በስብሰባቸው ማጠቃለያ ላይ ይፋ ያደርጉትን ጠቅላላ ስምምነት በፊርማቸው ማጽደቃቸው ታውቋል። በጣሊያን፣ አሲሲ ከተማ ከመስከረም 12-14/2015 ዓ. ም. ድረስ ሲካሄድ በቆየው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ስብሰባ ላይ የተገኙት ወጣቶች ከ 120 አገራት የመጡ ሲሆን ቁጥራቸውም ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች መሆናቸው ታውቋል።    

ከአሲሲ ከተማ ባሻገር

መሠረት በጣለው የቅዱስ ፍራንችስኮስ የምጣኔ ሃብት ሥርዓት ማሻሻያ ስብሰባ ላይ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፤ ሥራ ፈጣሪዎች እና ቀጣይነት ያለውን ልማት ለማምጣት የሚያግዝ ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን ያቀረቡ የምጣኔ ሃብት ባለ ሙያዎች መካፈላቸው ታውቋል። የቅዱስ ፍራንችስኮስ የምጣኔ ሃብት ሥርዓት ማሻሻያ እንቅስቃሴ ከአሲሲ አልፎ ልማት እና እድገት ወደሚናፍቃቸው የዓለማችን አካባቢዎች የሚዳረስ እንደሚሆን ተገልጿል።   

በጣሊያን ውስጥ ከላዚዮ ክፍለ ሀግረ የመጣው የስብሰባው አስተባባሪ ወጣት ሊቪዮ ላ ማቲና ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደተናገው፣ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን የሚያስተባብሩ እና እንቅስቃሴውን ለማሳደግ እና ፕሮጀክቶችን ለማበረታታት ቁርጠኛ የሆኑ 50 የሚደርሱ ወጣቶች መመደባቸውን ገልጿል። በየአገራቱ የሚገኙ ሥራ ፈጣሪዎችም የምጣኔ ሃብቱ ሥርዓት ተሃድሶ ተዋናዮች መሆናቸውን ወጣት ሊቪዮ ላ ማቲና ገልጾ፣ "ግሪንሃውስ" የተሰኘ የጸሐይ ኃይል ተጠቃሚ ድርጅት በጥምረቱ ውስጥ እንደሚገኝ ገልጾ ከ “ግሪንሃውስ” መሥራቾች መካከል አንዷ የሆነችው ማሪያንጄላ ላንቼሎታ፣ የተግባር መርሃ ግብራቸው የግብርና እንቅስቃሴን ሊያግዝ እንደሚችል አስረድታለች።

የቅዱስ ፍራንችስኮስ የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ እቅዶስ በጋዜጦች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከመላው ዓለም ለተውጣጡ ወጣት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች እና ሥራ ፈጣሪዎች መጋቢት 23/2011 ዓ. ም. በላኩት መልዕክት፣ የጋራ ስምምነት በማድረግ በምጣኔ ሃብት ሥርዓት ዓለም አቀፍ ለውጥን ለማስተዋወቅ እንዲዘጋጁ መጋበዛቸው ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው “የምዕራባውያን የካፒታሊስት ፈተና ተጀምሯል” ማለታቸውን “ኢል ጆርናሌ” የተሰኘው የጣሊያን ዕለታዊ ጋዜጣ በሐምሌ 15/2011 ዓ. ም. እትሙ ማስነበቡ ይታወሳል።

24 September 2022, 16:58