ፈልግ

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ ለኤኮኖሚ ተሃድሶ ተስፋ መሆኑ ተነገረ

በጣሊያን የአሲሲ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዶሜኒኮ ሶሬንቲኖ፣ በከተማቸው ከመስከረም 12-24/2015 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ስብሰባ በምጣኔ ሃብት ሥርዓት ላይ መሻሻልን እንደሚያመጣ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የተለያዩ አገራት ወጣት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች የቅዱስ ፍራንችስኮስን አርአያ በመከተል በዘመናችን የኤኮኖሚ ሥርዓት ላይ ተሃድሶ እንዲያደርጉ ወደ አሲሲ ከተማ መጋበዛቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ጣሊያንን ጨምሮ በሌሎች አንዳንድ አገራት ሰዎች ሀብታም ሲሆኑ በሌሎች አገራት ደግሞ በድህነት መሰቃየታቸውን አስታውሰው፣ ይህም "የምጣኔ ሃብት ሥርዓቱ በትክክል እየተጓዘ አለመሆኑን ይገልጻል” በማለት በጣሊያን የአሲሲ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዶሜኒኮ ሶሬንቲኖ አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሶሬንቲኖ በአሲሲ ከተማ  በመካሄድ ላይ ካለው የምጣኔ ሃብት ባለ ሙያዎች ስብሰባ አስቀድመው ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በግድ የለሽነት ምክንያት በዓለማችን ውስጥ በድህነት የሚሰቃዩ ሰዎች ቁጥር በርካት መሆኑን ተናግረዋል።

ወደ ምጣኔ ሃብታዊ እድሳት የሚወስድ መንገድ ማዘጋጀት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን፣ ሥራ ፈጣሪዎችን እና በዘርፉ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን ወደ መካከለኛው የጣሊያን ከተማ አሲሲ በመጋበዝ፣ በሕዝቦች የኑሮ አለመመጣጥን ላይ ትኩረት በማድረግ ውይይታቸውን እንዲያካሄዱ ጋብዘዋል።

የውይይታቸው ዓላማ ባለሞያዎቹ እውቀታቸውን በማስተባበር በምጣኔ ሃብት ዕድገት ውስጥ ድሃ የሆነውን የኅብረተሰብ ክፍል በማካተት ወደ አንድ የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚወስድ መንገድ እንዲያፈላልጉ ለማድረግ መሆኑ ታውቋል። “አዲስ የምጣኔ ሃብት ሥርዓት የሚገነባበት እና የኑሮ ዘይቤያችንን የምናድስበት ጊዜው አሁን ነው!” በማለት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዶሜኒኮ ሶሬንቲኖ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

“የምጣኔ ሃብት ሥርዓት ችግር በዋነኛነት የፖለቲካ ችግር መሆኑን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሶሬንቲኖ፣ በምድራችን ውስጥ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው የችግሩ ተጠቂ በመሆኑ መፍትሄን ለማግኘት በሚደረግ ጥረት ላይ የመሳተፍ እና የማገዝ ኃላፊነት አለበት” ብለዋል። የአሲሲ ከተማ የቅዱስ ፍራንችስኮስ የትውልድ ከተማ በመሆኗ፣ ወጣቶች በምጣኔ ሃብት ሥርዓት ላይ ተሃድሶ የሚደረግበትን መንገድ ለመቀየስ ድፍረት የሚያገኙባት ከተማ ተደርጋ ልትወሰድ እንደምትችል ተናግረዋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሶሬንቲኖ በማከልም፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣት የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎቹ ከስብሰባቸው መልስ በየአገሮቻቸው ሆነው ኅብረትን በመፍጠር በምጣኔ ሃብት ዘርፍ ፍሬያማ  ተግባራትን ለማከናወን የሚችሉበትን ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።     

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ በዓለም ዙሪያ ዕድሜያቸው ከ35 ዓመት በታች የሆኑ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን፣ ሥራ ፈጣሪዎችን እና ዘላቂ የኤኮኖሚ ሥርዓትን የሚያራምዱ ወጣቶችን የሚያስተባብር እንቅስቃሴ መሆኑ ይታወቃል። 

22 September 2022, 17:05