ፈልግ

በዩክሬን ቲቭሪቭ ከተማ የተካሄደ የወጣቶች ዓመታዊ በዓል በዩክሬን ቲቭሪቭ ከተማ የተካሄደ የወጣቶች ዓመታዊ በዓል 

የዩክሬን ወጣቶች ተስፋ ጥላቻን እንደሚያሸንፍ ገለጹ

ጦርነት በቀጠለባት ዩክሬን ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ዓመታዊ በዓላቸውን አክብረው መዋላቸውን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት የደረሰን ዘገባ አመልክቷል። ለሦስት ቀናት የተካሄደውን ዓመታዊ የወጣቶች ፌስቲባልን በዩክሬን ውስጥ ቲቭሪቭ በተባለ አካባቢ ያዘጋጁት የእመቤታችን ንጽሕት ማርያም ማኅበርተኞች መሆናቸው ታውቋል። ፈስቲቫሉን የተካፈሉት ወጣቶች ወንድማማችነትን ለማሳደግ በሚረዱ ምክረ ሃሳቦች አስተንትኖ ያደረጉ ሲሆን ተስፋ ማንኛውንም ጥላቻ ማሸነፍ የሚችል መሆኑን መስክረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት እየተስፋፋ መሆኑ ይነገራል። የጦርነት አስከፊነት ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከቱት የአገሪቱ ነዋሪዎች የተለያዩ አስደንጋጭ ምስሎችን እና አሉታዊ ገጽታዎችን የያዙ ዜናዎች በየዕለቱ እንደሚደርሳቸው ተነግሯል። ቢሆንም ዜጎች አእምሮአቸውን የሚያሳርፉበት፣ ለነፍስም ሆነ ለሥጋ መጽናናትን የሚያገኙበትን ዕድል በማፈላለግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። በዩክሬን የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለምዕመናን፣

"እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበዳችሁ በሙሉ ወደ እኔ ኑ፥ እኔም አሳርፋችኋለሁ።" የሚለውን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በማሰማት ላይ እንደሆነች ታውቋል። በተለይም አቅመ ደካሞችን በመርዳት፣ መጠጊያ ለሌላቸው እና ለአደጋ የተጋለጡትን በመቀብል ዕርዳታ በማድረግ ላይ መሆኗ ታውቋል። የበጋ ወራትን ወጣቶች በመልካም ሁኔታ እንዲያሳልፉ በማቀድ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በየቁምስናዎች የተለያዩ ዝግጅቶችን በማቀድ፣ ደህነታቸውን በጠበቀ መልኩ መንፈሳዊ ንግደቶችን፣ ስብሰባዎችን እና አውደ ጥናቶችን ለሕጻናት እና ለወጣቶች እና ለአዋቂዎች ማዘጋጀቷ ታውቋል።

ወጣቶች በአስተንትኖ ጊዜ
ወጣቶች በአስተንትኖ ጊዜ

ቲቭሪቭ በተባለች መካከለኛው ዩክሬን ከሐምሌ 20 እስከ ሐምሌ 23/2014 ዓ. ም. ወጣቶች ዓመታዊ በዓላቸውን ማክበራቸው ታውቋል። “የሕይወት እስትንፋስ” በሚል መሪ ሃሳብ በዓሉን ያስተባበሩት በአገሪቱ ሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውን በመፈጽም ላይ የሚገኙ የእመቤታችን ንጽሕት ማርያም ሚሲዮናውያን ማኅበርተኛች መሆናቸው ታውቋል። የማኅበሩ አባል ክቡር አባ ቫዲም ዶሮሽ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ ዓመታዊ የወጣቶች ፌስቲቫሉ እ. አ. አ ከ 2009 ዓ. ም. ጀምሮ እንደሚከበር ገልጸው፣ ከ150 እስከ 200 የሚደርሱ ወጣቶች እንደሚካፈሉት አስረድተዋል። ዘንድሮ የተከበረውን ፌስቲባል ለማዘጋጀት በርካታ ውይይቶችን ማካሄዳቸውን የገለጹት አባ ቫዲም፣ ጸሎቶችን እና አውደ ጥናቶች በማዘጋጀት ወጣቶችን ማሳተፋቸውን ገልጸዋል። የወጣቶቹን ደህንነት ማረጋገጥ አስፈላጊ እንደነበር የገለጹት አባ ቫዲም፣ ዓመታዊ ፌስቲቫሉ እንዳይቀር ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን እና ከሌላው ዓመት በቁጥጥር አነስተኛ የሆኑ አባላትን በማሳተፍ ይበልጥ የጸሎት እና የአስተንትኖ ዝጅግጅቶችን ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

በወጣቶች ፌስቲቫል ላይ የቀረበ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት

እውነተኛ የሕይወት እስትንፋስ

“ጦርነት ቢኖርም በበዓሉ ላይ ለመገኘት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ” ስትል የገለጸች የ25 ዓመቷ ወጣት ማሪያ ቴሬዛ፣ በዓሉን ማክበር ከጀመረች ዘንድሮ በቲቭሪቭ ከተማ የተገኘችበት አራተኛ መሆኑን ገልጻለች። አስቸጋሪ በሆነበት በዚህ ወቅት በበዓሉ ላይ ከነበሩ ወጣቶች ጋር ለመገናኘት መቻል የሕይወት እስትንፋስን ለማግኘት እጅግ አስፈላጊ እንደነበር ገልጻ፣ በመስዋዕተ ቅዳሴ እና በውዳሴ ጽሎቶች ወደ እግዚአብሔር ዘንድ መቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ማርያ ቴሬዛ አስረድታለች። በማከልም እንደ እነዚህ ያሉ ዝግጅቶች በአስቸጋሪ ጊዜያትም ጭምር መከናወን እንዳለባቸው ተናግራ፣ እግዚአብሔር ሁል ጊዜ አሸናፊ መሆኑን እንድናምን፣ ተስፋና እምነት እንዲንኖረን ይረዳናል በማለት ገልጻለች። የፍቅር እና የጓደኝነት እሴቶች ክፋትን እንደሚያሸንፉ፣ ጦርነት እና ሞት በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ መሸነፋቸውንም ወጣት ማርያ ቴሬዛ አክላ ገልጻለች።

የሚያነሳሳን ፍቅር እንጂ ጥላቻ መሆን የለበትም

ከጸሎት እና ስፖርታዊ ጨዋታዎች በተጨማሪ የበዓሉ አዘጋጆች ለወጣቶች የተለያዩ አውደ ጥናቶችንም ማዘጋጀታቸው ታውቋል። ይህም በጦርነት ስጋት እና ጭንቀት ውስጥ ለሚገኙት ወጣቶች ብርታትን እና መጽናናትን እንደሚሰጣቸው ክቡር አባ ቫዲም አስረድተዋል። በዩክሬን ውስጥ ጦርነቱ በስፋት ከተካሄደባቸው አካባቢዎች የመጡት በርካታ ወጣቶች በዓሉ ላይ መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ወጣቶች በስፖርታዊ ጨዋታዎች ሲሳተፉ
ወጣቶች በስፖርታዊ ጨዋታዎች ሲሳተፉ

ጭካኔ የተሞላበት ጦርነት ሲካሄድ በሰዎች ውስጥ ቁጣ መሰማቱ የማይቀር ነው ያሉት ክቡር አባ ቫዲም፣ ከዚህ የተነሳ ልባችን በጥላቻ ሊሞላ እንደሚችል ገልጸው፣ በበዓሉ ወቅት በቀረበው አስተምህሮ እና ውይይት አማካይነት ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት፣ ግርፋት እና ነፍሱን አሳልፎ ስለ መስጠት መነጋገራቸው አስታውሰው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ ‘ጌታ ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው’ ማለቱን አስታውሰዋል። ይህም ለወጣቶቹ እንዲነገር የተፈለገ ዋና መልዕክት እንደነበር ገልጸው፣ የበደለውን ይቅር ማለት የጥላቻ ስሜትን አስወግዶ ፍቅርን ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን በዩክሬን የእመቤታችን ንጽሕት ማርያም ሚሲዮናውያን ማኅበር አባል የሆኑት ክቡር አባ ቫዲም ዶሮሽ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። 

04 August 2022, 16:37