ፈልግ

በጃፓን ሄሮሺማ እና ናጋሳኪ ከተሞች የተፈጸመውን የአቶሚክ ቦምብ ፍንዳታ በጃፓን ሄሮሺማ እና ናጋሳኪ ከተሞች የተፈጸመውን የአቶሚክ ቦምብ ፍንዳታ  (©lukszczepanski - stock.adobe.com)

የጃፓን ብጹዓን ጳጳሳት ሰላምን ማስፈን የሁሉ ሰው ግዴታ መሆኑን አስታወቁ

የጃፓን ካቶሊካዊ ምዕመናን ከሐምሌ 30 - ነሐሴ 9/2014 ዓ. ም. ዓመታዊ የሰላም ጸሎት በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል። የአገሪቱ ካቶሊካዊ ጳጳሳት የጸሎት ዝግጅቱን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሰላምን የሁሉ ሰው ሃላፊነት ያለበት እንደሆነ አስገንዝበዋል። በብጹዓን ጳጳሳቱ ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የቶኪዮ ሊቀ ጳጳስ በሆኑት አቡነ ኢሳኦ ኪኩቺ ተፈርሞ ይፋ የሆነው መልዕክቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዩክሬን እየተካሄደ ባለው ጦርነት ዙሪያ ያስተላለፉትን መልዕክት የሚያንጸባርቅ መሆኑ ተመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ሰላምን ማንገሥ ይቻላል፣ ሰላም የሁሉ ሰው ሃላፊነት ያለበት ነው” ያሉት የጃፓን ብጹዓን ጳጳሳት፣ ምዕመናኑ በዓመታዊው የሰላም ጸሎት ወቅት ስለ ሰላም ተግተው እንዲጸልዩ አደራ ብለዋል። በጃፓን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ተነሳሽነት የሚካሄደው ዓመታዊ የጸሎት ሥነ ሥርዓቱ በ 1937 ዓ. ም. ሄሮሺማ እና ናጋሳኪ በተባሉ ሁለቱ የጃፓን ከተሞች የተፈጸመውን የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት ለማሳታወስ እንደሆነ ታውቋል።

በቶኪዮ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኢሳኦ ኪኩቺ የተፈረመው የዘንድሮ የጉባኤው መልዕክት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ነሐሴ 27/2012 ዓ. ም. በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዕለት እና እንዲሁም ሚያዝያ 9/2014 ዓ. ም. ለመላው የዓለም ካቶሊካዊ ምዕመናን ባስተላለፉት የብርሃነ ትንሳኤ መልዕክት፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ያወጀውን ጦርነት በማስታወስ ለኒውክሌር ጦርነት እና ለዓለም አቀፍ ደኅንነት ስጋቶች ትኩረት የሰጡበትን መልዕክት ያስታወሰ መሆኑ ታውቋል።

ሩስያ በዩክሬን ላይ ያካሄደችው ወረራ የዓለምን ሰላም ያደናቅፋል

ር. ሊ. ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሁለት ዓመት በፊት ባቀረቡት የጠቅላላ ትምህርት ክርስቶስ አስተምህሮአቸው በዓለማችን ውስጥ ከፍተኛ ጉዳትን ካስከተለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመላቀቅ በመግባባት ላይ የተመሠረተ "ልዩነት እና አንድነት" ሊኖር እንደሚገባ ማሳሰባቸው ይታወሳል። ነገር ግን የጃፓን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በዓይናቸው የተመለከቱት፣  በልዩነት ላይ የተመሠረተ አንድነት ሳይሆን ግጭት፣ መገለል እና ብጥብጥ መሆኑን በመልዕክታቸው ገልጸዋል። ብጹዓን ጳጳሳቱ ይህን ሲያብራሩ፣ ሩስያ በዩክሬን ላይ ያካሄደችው ወረራ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የሰላም ጥረት የረገጠ ኃይለኛ የጥቃት እርምጃ መላውን ዓለም ያስደነገጠ መሆኑን ገልጸው፣ እርምጃው ሕይወትን ከአደጋ ለመከላከል እና ሰላምን ለማምጣት የሚፈልጉ የብዙ ሰዎች ፍላጎት ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።


ሰላም በሁከት አይመጣም      

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተሞክሮ ትምህርት እንዳገኙ የገለጹት የጃፓን ብጹዓን ጳጳሳቱ፣ እርስ በእርስ መደጋገፍ እና መተሳሰብ ሕይወትን ከአደጋ ለመጠበቅ እና ለመንከባከብ ከሁሉ የተሻለው መንገድ መሆኑን አስረድተው፣ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራን ካካሄደች በኋላ ዓለም “ሰላም በዓመፅ ሊገኝ ይችላል” በሚል ስሜት ውስጥ ቢገኝም፣ ይህ ስሜት ሰላም ይረግጣል እንጂ እውነተኛውን ሰላም ሊያመጣ አይችልም” በማለት አስጠንቅቀዋል። “ሕይወትን ተነፍገው በጦርነቱ የተጎዱትን በርካታ ሰዎች ስንመለከት ልባችን አዝኗል” ያሉት ብጹዓን ጳጳሳቱ፣  በጦርነቱ ተጎጂዎች ፊት የሚታየው ፍርሃት እና ቁጣ የርኅራሄ እና የድጋፍ ስሜትን የቀስቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።

የጦርነት መዘዝ መላውን የሰው ልጅ ይጎዳል

ከባድ ጦርነት፣ ሌሎች ከሰው ልጆች ሕይወት ጋር የተያያዙ፣ ችላ የተባሉ ጉዳዮችን ማለትም ድህነትን፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከትውልድ አገራቸው እንዲሰደዱ የተገደዱ ሰዎችን ከግንዛቤ ውስጥ እንዳናስገባ ያደርጋል በማለት ብጹዓን ጳጳሳቱ በመልዕክታቸው አስረድተዋል። የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የብርሃነ ትንሳኤ መልዕክት የጠቀሱት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኪኩቺ፣ “እያንዳንዱ ጦርነት መላውን የሰው ልጅ የሚጎዳ ውጤት እንደሚያስከትል፣ ከሐዘንና ለቅሶ ጀምሮ እስከ ስደተኞች መከራ፣ የኢኮኖሚ ቀውስ እና የምግብ እጥረትን ያስከትላል” ማለታቸውን አስታውሰዋል። በጃፓን የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሄሮሺማ እና በናጋሳኪ ከተሞች የተፈፀመውን የአቶሚክ ቦምብ ጥቃት በምታስታውስበት በዚህ ወቅት ምዕመናኑ በጸሎታቸው በልዩ ልዩ አቅጣጨዎች በማሰብ ሰላምን እንዲያነግሡ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል። የጃፓን ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት እና የቶኪዮ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኢሳኦ ኪኩቺ የጉባኤውን መልዕክት ሲያጠቃልሉ ሰላምን ያለ አመጽ ማምጣት እንደሚቻል ገልጸው፣ ምዕመናኑ በአሥር ቀናት የሰላም ጸሎት ሰላምን የሚፈጥር አብሮነት ለመመሥረት እርምጃን እንዲወስዱ ጠይቀዋል።  

የአሥር ቀናት የሰላም ጸሎት ተነሳሽነት

በጃፓን ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሲካሄድ የቆየው የአሥር ቀናት የሰላም ጸሎት እንቅስቃሴ የተጀመረው  በአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት ተነሳሽነት በ1974 ዓ. ም. ሲሆን ሃሳቡ የፈለቀው የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በ1973 ዓ. ም. በጃፓን ሂሮሺማ ከተማ ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ተከትሎ መሆኑ ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስም በጥቅምት ወር 2012 ዓ. ም. በጃፓን ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት “የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤትነት ሥነ ምግባር የጎደለው ነው” በማለት መኮነናቸው ይታወሳል።

11 August 2022, 16:58