ፈልግ

መልካም ለመሥራት አንታክት መልካም ለመሥራት አንታክት  (ANSA)

መልካም ለመሥራት አንታክት

እኛ ሰዎች በመልካምና በክፉ በኃጢያትና በጽድቅ መካከል እንኖራለን፡፡ መልካም ሆነ ክፉ በየበኩላቸው ይስቡናል፣ ከሁለቱም አንዱን እንድይዝ ግድ ነው፣ ኃጢአትን ማድረግ እንወዳለን የጽድቅ ሥራ ግን ያስጠላናል፣ ከመልካም ነገር ክፉ ሥራ ይስበናል፣ ኃጢአት የሚጐዳን መሆኑን እያወቅን እናደርገዋለን፣ ይህም በአዳም ኃጢአት የተበላሽ ባሕርያችን ወደ ክፉ በኃይል ሰለሚጐትተን ነው፡፡ ጽድቅን ግን ለነፍሳችን ጠቃሚ መሆኑን እያወቅን አናደርገውም፡፡ ምክንያቱም የተበላሸው ባሕርያችን ጽድቅን ስለሚጠላ ነው፡፡ ስለዚህ ሁኔታ ኦቪዲዮ የሚባል ከዝነኞቹ ሮማውያን ጸሐፊዎች አንዱ «መልካም ነገርን ስመለከተው እወደዋለሁ፣ ግን ክፋውን እከተላለሁ´ ይል ነበር፡፡ በእርግጥ ክፋውን ማድረግ ደስ የሚልና ቀላል ነገር ነው፡፡ እንድናደርገው ራሱ ይስበናል፡፡ ባሕርያችንም ይወደዋል፣ ጥሩ ነገር ማድረግ ግን ያስጠላናል፣ ከባድ ነገር ሆኖ ይታየናል፡፡

ባሕርያችን ኃጢአትን ስናደርግ ተስማምቶ ይሄዳል ምንም አይታወቀንም፡፡ የጽድቅ ነገር የምናደርግ ሲሆን ግን በኃይል የተገደደ ዓይነት ተቃራኒ ነገር ሆኖ ይሰማዋል፡፡ ጥሩ ሥራ ማድረግ አቀበት መውጣት ይሆንበታል፣ ክፋትን ማድረግ ቁልቁለት እንደመውረድ ቀላል ይሆንለታል፡፡ መልካም ሥራ ስለሚከብድ ያስጠላናል፣ በስንፍና እናፈገፍጋለን፡፡ «ተስፋ ሳንቆርጥ በትዕግስት ከጸናንና በወቅቱ መልካም ፍሬ ስለምናጭድ መልካም ሥራን ከመሥራት አንስነፍ´ (. ገላ. 6፣9) እያለ ጰውሎስ ያበረታታናል፡፡ በዚህ ሁኔታ በመልካም ምግባር ትጉዎች እንጂ ሃኬተኞች እንዳንሆን ይመክረናል፡፡ መልካም ለማድረግ መታከት የለብንም፡፡ ምክንያቱም ይህ የአምላክ ፈቃድ ነው፡፡ እንዲሁም ለተፈጥሮአችን ዓላማ እና ለዘለዓለማዊ ደስታና ቅድስና በጣም አስፈላጊ ነው፡፡

መልካም ሥራ በምድር ሆነ በሰማይ ያሰደስተናል፤ ከዚያም አልፎ ክብር ይሆንልናል፡፡ በነዚህ በጠቀስናቸው ምክንያቶች መልካም ሥራን ጠልተን መተው አይገባንም፡፡ ምንም እንኳን የሚከብደን ነገር ቢሆንም ዋና ሥራችን መሆኑን ተገንዘበን ለራሳችን ጥቅም ብለን ልንይዘው ይገባናል፡፡ ወደ ጽድቅ የሚገፋፋን ዋና ምክንያት ግን በሰማይ የሚጠብቀንን ነገር በማሰብ ነው፡፡ «በትዕግስት ብንጸና በወቅቱ ስለምናጭድ መልካም ሥራን ከመሥራት አንስነፍ´ የገበሬው ኑሮ ጥረትና ትግል ልፋት የተሞላበትን ነው፡፡ ይህ ጥረትና ትግል ግን በመጨረሻ ጣፋጭ ፍሬ ያለው ስለሆነ ገበሬው ሰነፍ ወይም ሃኬተኛ ሆኖ ሥራውን አይተውም፤ በደስታ ይሠራል እንጂ፡፡ «እህል አገኛለሁ፣ ዘንድሮ ከአምና የበለጠ እሰበስባለሁ´ በሚል ተስፋ በየዓመቱ በስንት ድካም ይሠራል? እንደተመኘውም ደግሞ የድካሙን ፍሬ ያገኛል እህሉን ያፍሳል፡፡ በክረምት የዘራውን በመከር ወቀት ያጭዳጭ፡፡ በዝናም ወቅት ይሠራል፣ ይደክማል የመከር ወቀት ሲደርስ እፎይ ብሎ ያርፋል፣ ይደሰታል፡፡

መልካም ሥራ ማድረግ ደግሞ እንደዚሁ ከባድና አስቸጋሪ ነው፡፡ ነገር ግን በመጨረሻ ማለትም ከሞት በኋላ ይህ ነው የማይባል የደስታን ፍሬ ይሰበስባል፡፡ ክፋ ሥራ ግን በመጀመሪያው ደስታ የሚልና ቀላል ነው፡፡ በመጨረሻው ግን የሚዘገንን የኩነኔ ውጤት ያስገኛል ከባድ ስቃይ አለው፡፡ እንደ ገበሬው በክረምት ጊዜ በድካምና በጥረት ዘርተን በመከር ማጨድን በማስታወስ ለመልካም ሥራ አንታክት፡፡ በምድር ጥሩ ሥራን እንደዘር ከዘራን በሰማይ የጽድቅን ፍሬ እንሰበስባለን፡፡

የእግዚአብሔር የቤተክርስቲያን ትዕዛዝ መፈጸም ሲያስጠላንና በክርስቶስ መንገድ መጓዝ ሲከብደን በሰማይ የተዘጋጀልንን ደስታ እናሰታውስ፡፡ ጸሎት ተጋድሎ የሆነ መልካም ሥራ ሁሉ ለመሥራት ሃኬት ከተሰማን በሰማይ የምናገኘውን የጽድቅ አክሊል እናስብ፡፡ ጥሩ ሥራ ሲገኝ «በዛብኝ፣ ከባድ ነው፣ አልችለውም፣ በፊት ያደረግሁት ይበቃኛል´ የሚል ደካማ መንፈስን ሲያወላግደን ያ የደስታን ሀገር ሰማይን እንመልከት፡፡ ይህን ተመልክተን ሃኬትንና ስንፍናን አሸንፈን በትጋትና በልግስና መልካም ተግባር እንፈጽም፡፡

 

08 August 2022, 15:38