ፈልግ

ካርዲናል ማቴዎ፣ በሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ ካቴድራል ውስጥ በተካሄደ ጉባኤ ላይ ካርዲናል ማቴዎ፣ በሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ ካቴድራል ውስጥ በተካሄደ ጉባኤ ላይ 

ካርዲናል ማቴዎ፣ ከሞዛምቢክ ተሞክሮ ሰላምን ማምጣት ዘወትር እንደሚቻል ገለጹ

በጣሊያን የቦሎኛ ከተማ ሊቀ ጳጳስ እና የጣሊያን ብጹዓን ጳጳስ ጉባኤ ፕሬዝደንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ይህን የገለጹት፣ በሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ በመንግሥት እና በተቃዋሚ ቡድን መካከል የተደረሰ የሰላም ስምምነት 30ኛ ዓመትን ለማክበር በተካሄደ ጉባኤ ላይ መሆኑ ታውቋል። በሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ በሚገኝ ካቴድራል ውስጥ ነሐሴ 5/2014 ዓ. ም. የተካሄደውን ጉባኤ በማስመልከት ሮም የሚገኝ የቅ. ኤጂዲዮ ማኅበርሰብ እንዳስታወቀው፣ የሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ትልቁ ምኞት በሞዝምቢክ ውስጥ ሰላም እንዲወርድ ብቻ መሆኑን አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እ. አ. አ. እሑድ ጥቅምት 4/1992 በወቅቱ የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ዮአኪም ቺሳኖ እና የሽምቅ ተዋጊው መሪ የነበሩት አቶ አፎንሶ ድላካማ ጠቅላላ የሰላም ስምምነት መፈራረማቸው ሲታወስ፣ ለ17 ዓመታት የዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ከመሆኑ በላይ ወደ 4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን በማፈናቀል ለስደት መዳረጉ ይታወሳል። በሁለቱ ወገኖች መካከል የተካሄደውን ረጅም የሰላም ድርድር ሂደት ያገዘው ሮም የሚገኝ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር መሆኑ ይታወሳል።

በግጭት ውስጥ የነበሩ ሁለት ወገኖችን በማደራደር ከፍተኛ ሚናን የተጫወቱት በሮም የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር መሥራች ይሆኑት ክቡር አቶ አንድሬያ ሪካርዲ እና በወቅቱ በክኅነት ማዕረግ ሲያገለገሉ የነበሩ፣ ዛሬ የቦሎኛ ከተማ ሊቀ ጳጳስ እና የጣሊያን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሊቀ መንበር የሆኑ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ እንደነበሩ ይታወሳል። ሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ ከደረሱባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል አንዱ የጦር መሣሪዎቻቸውን ለተባበሩት መንግሥታት ኃይሎች ማስረከብ ሲሆን፣ ከሁለቱም ወገኖች በጦርነቱ ላይ የተሳተፉትን በሙሉ ከመደበኛው የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጋር ማዋሃድ እንደነበር ይታወሳል። ይህ ሂደት በኋላ ላይ በገጠራማ አካባቢዎች የተቀበሩ ፈንጂዎችን በማውጣት እና በማረጋጋት ሂደት ላይ ችግሮችን ፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል። በሞዛምቢክ የተካሂደውን የሰላም ድርድር ሂደት በማተባበር እና በማገዝ የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር በሁለቱ ወገኖች መካከል ሰላምን እና እርቅን በማውረድ ከፍተኛ ሚናን መጫወቱ አይዘነጋም።

ወደ እርቅ የተደረገ ጉዞ

በአገሪቱ ለ17 ዓመታት የዘለቀው አስከፊ ጦርነት ቆሞ ሰላም የወረደበት 30ኛ ዓመት ለማስታወስ በሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ ነሐሴ 5/2014 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በ11 ሰዓት ላይ ጉባኤ መካሄዱ ታውቋል። እ. አ. አ በ1984 ዓ. ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሞዛምቢክ መጓዛቸውን የገለጹት ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ፣ ወቅቱ አገሪቱ በከፍተኛ ድርቅ እና ጦርነት ውስጥ የነበረችበት ጊዜ እንደበር አስታውሰዋል። የሞዛምቢክን ሕዝብ ስቃይ በቅርብ ይከታተል የነበረው የቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር ከአገሪቱ መንግሥት ጋር ግንኙነቶችን አጠናክሮ ውይይቶችን በማካሄድ በመጀመሪያ ጥረቱ በአገሪቱ ውስጥ የነበረውን ረሃብ ለማጥፋት በቅድሚያ የረሃብ ምክንያቶችን በመለየት የሰላም መንገዶችን ማመቻቸት እንደነበር ብጹዕ ካርዲናል ማቴው አስረድተው፣ ከሞዛምቢክ ተሞክሮ በመነሳት ሰላምን ማምጣት ዘወትር እንደሚቻል ገልጸዋል።

ከድርድር ወደ ሰላም

በሞዛምቢክ ዋና ከተማ ማፑቶ በሚገኝ ካቴድራል ውስጥ ነሐሴ 5/2014 ዓ. ም. የተካሄደውን ጉባኤ በማስመልከት የቅ. ኤጂዲዮ ማኅበርሰብ እንዳስታወቀው፣ የሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ዓላማ በሞዝምቢክ ሰላምን ማውረድ እንደሆነ አስታውቋል። በሁለቱ ወገኖች መካከል የተካሄደው የሰላም ድርድሩ ለሁለት ዓመታት እንደዘለቀ የገለጸው ማኅበሩ፣  ሁለቱም ወገኖች በመካከላቸው የነበረውን ችግር ለመቅረፍ ከልብ ይፈልጉ እንደ ነበር አስረድቷል። ወሳኙ እውነታ መንግሥትም ሆነ ሬናሞ ተዋጊ ቡድን በቅዱስ ኤጂዲዮ ማኅበር ላይ እምነት ማኖር እንደነበር አስረድቷል። ችግሮች ቢኖሩም ከጥረቶቹ መካከል አንዱ ሁለቱም ወገኖች የአንድ ቤተሰብ፣ የሞዛምቢክ አካል መሆናቸውን ግልጽ ማድረግ እንደነበር እና ይህም በሰላም ድርድሩ የተሳካ ውጤት ለማግኘት እውነተኛ ቁልፍ መሆኑን የጣሊያን ብጹዓን ጳጳስ ጉባኤ ፕሬዝደንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ አስምረውበታል። ካርዲናሉ አክለውም ሁለቱ ወገኖች የሰላም ስምምነትን የፈረሙበት እ. አ. አ. እሑድ ጥቅምት 4/1992 ዓ. ም. መላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ፍራንችስኮስን ዓመታዊ ክብረ በዓል ያከበረችበት ዕለት እንደነበር አስታውሰዋል።

13 August 2022, 16:39