ሐዋርያዊ እንክብካቤን የሚያሳድግ የእርስ በእርስ ግንኙነት እና የመረዳዳት ዘዴ ሊኖር ይገባል ተባለ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በመካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ ሲካሄድ የቆየው የእርስ በእርስ ጦርነት በ2013 ዓ. ም. በይፋ ያበቃ ቢሆንም፣ በመንግሥት እና የአማፂ ቡድኖች መካከል ግጭቶች በዘላቂነት ሲከሰቱ መየታቸው ይታውቋል። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ አማጺ ቡድኖች መካከል፣ በተለይም የአማፂያን ምሽጎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ዛሬም ግጭቶች መኖራቸው ታውቋል።
ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙ ልዩ ልዩ ሐይማኖታዊ ተቋማት ተደጋጋሚ የእርስ በእርስ ግጭቶች እንዳስፋፉ ለመከላከል ከፍተኛ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። የመካከለኛው አፍሪካ ብጹዓን ጳጳሳት በሰኔ ወር 2014 ዓ. ም. በባምባሪ ባደረጉት ምልአተ ጉባኤ፣ በአገሪቱ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ለምዕመናኖቻቸው የሚሰጡትን ሐዋርያዊ እንክብካቤ፣ ርህራሄ፣ ቅርበት እና አንድነት ለማሳደግ መጠራታቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ማህበራዊ ትስስርን ማጠናከር
ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በቤተክርስቲያን ውስጥ ያለው አንድነት ማጠናከር እንደሆነ የገለጹት የቧር ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሚሮስሎው ጉክዋ፣ ጥረታቸው በቅድሚያ በብጹዓን ጳጳሳት መካከል ያለውን አንድነት በማጠናከር፣ ከዚያም ለምዕመናን እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ሰዎች ተመሳሳይ የአንድነት መልእክት በማስተላለፍ ማኅበራዊ ትስስርን ማሳደግ እና ማጠናከር እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህን ዓላማ ለማሳካት በመካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ በሁሉም ሀገረ ስብከቶች እና ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ሕዝቦች ተገናኝተው በአካባቢያቸው ስላጋጠማቸው ተግዳሮቶች እንዲነጋገሩ ለማድረግ ሃይማኖታዊ መድረኮችን ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በእነዚህ መድረኮች አማካይነት የሃይማኖት ግጭቶች እንዲቀንሱ፣ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ችግሮች ሙሉ በሙሉ እንዲወገዱ መደረጋቸውን ከምስጋና ጋር ገልጸዋል። ለዚህም የመካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ ብጹዓን ጳጳሳት፣ ኅብረተሰቡ አብሮ የመኖር ፍላጎት ስላለው የሃይማኖት መሪዎች ማኅበራዊ ትስስርን እና ሰላምን የሚያበረታታ ቋንቋ መናገር እንዳለባቸው አሳስቧል።
ድምፅ ለሌላቸው ድምፅ መሆን
በአገሪቱ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ማኅበራዊ ትስስርን ወደ ነበረበት ለመመለስ መወሰኗን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ጉክዋ፣ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ ውስጥ እስከ ዛሬ የሚታዩ እኩይ ተግባራትን፣ ሙስናን፣ ደህንነት ማጣትን፣ የተጋላጭ ሰዎች ብዝበዛን አውግዘው፣ ድምፅ የሌላቸው እነርሱም እርሻቸው የተዘረፈባቸው እና የወደመባቸው ገበሬዎች፣ የጥቃት ሰለባ የሆኑ ልጃገረዶች እና በጦርነት ምክንያት ወላጅ አልባ የሆኑትን እንደሚያጠቃልል ገልጸዋል።
በአገሪቱ ከሚገኝ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት እና ሌሎች መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በኩል በሚያገኙት ገንቢ ሃሳብ በመታገዝ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳስሳት፣ ምእመናን እና ዜጎች የተቸገሩትን እንዲረዱ ለማድረግ ግንዛቤን የማስጨበጥ ሥራ እያከናወኑ መሆናቸው ታውቋል። በመካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ የቡዋር ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሚሮስሎው ጉክዋ በማከልም፣ የአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት የጸሎት ኃይል የሰዎችን ልብ በመለወጥ በዓለማችን ውስጥ ስላምን ማንገሥ እንደሚችል በጽኑ ያምናሉ ብለዋል።