ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል  

ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ሦስት የጾም እና የጸሎት ቀናትን ይፋ አደረጉ

ለብጹዓን ጳጳሳት፣

ለክቡራን እንደራሴዎችና የሐዋርያዊ ሥራ አስተባባሪዎች፣

ለክቡራን ቆሞሳት፣ ለካህናት ለገዳማውያንና/ውያት፣

ለምዕመናን በሙሉ፤

ከሁሉ አስቀድሜ የጌታ ሰላም ይብዛላችሁ እያልኩ እንኳን ለፍልሰታ ለማርያም ጾም እና ሱባኤ ዋዜማ በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ።

ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት የተወጣጡ በጎ ፈቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን እናቶች በትውልድ ምድራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ በተነሱ በርካታ ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አለመግባባቶች ምክንያት በተፈጠሩ ሽኩቻዎች ለዘመናት በምድራችን ላይ ስለፈሰሰው ደም፣ ስለረገፈው አጥንት፣ ስለተዘራው ጥላቻና ቂም በቀል ካሳ ለትውልድ ሁሉ ፈጣሪያችን ምሕረትን እንዲያወርድልን እና በነዚህ ዘመናት ሁሉ የተጎዱ ወገኖቻችን ከሐዘናቸው መጽናናትን እንዲያገኙ እና በውዲቷ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እንደ ሀገር በጋራ ይቅርታን ለመጠየቅ እንችል ዘንድ ለሁሉም ሃይማኖቶች እና በጎ ፈቃድ ላላቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሰላም ጥሪ አቅርበውልናል።

እኛም እንደ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ይህንን የተቀደሰ ሃሳብ በመጋራት ከነሐሴ 1-3 ቀን 2014 ዓ. ም. በሁሉም ካቶሊካዊ አብያተ ክርስቲያናት እና በተቋሞቻችን የንስሐ እና የይቅርታ ትምህርት እየተሰጠ የምሕረት ጸሎት እንዲደረግ አውጀናል። ስለሆነም እንደ እምነታችን ሥርዓት ይህንኑ ጊዜ በጾም፣ በጸሎት እና በይቅርታ መንፈስ እናሳልፍ ዘንድ ብጹዓን አባቶች፣ የተከበራችሁ ቆሞሳት እና ካህናት እንዲሁም በየደረጃው የምትገኙ የቤተክርስቲያናችን አገልጋዮች ይህን የተቀደሰ የጸሎት ሃሳብ እንድታስተባብሩ እና የተጠቀሱትን ቀናት በቅንነት መንፈስ ከልባችን እንድንጸልይ እና የእግዚአብሔርን ምሕረት እና እርዳታ እንድንለምን በአጽንኦት እና በአደራ ጭምር ለማሳሰብ እንወዳለን።

እግዚአብሔር ለሀገራችን ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ይስጥልን።

†ካርዲናል ብርሃነየሱስ

ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካውያን

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት

04 August 2022, 18:02