ፈልግ

ቅዱስ አጎስጢኖስ ቅዱስ አጎስጢኖስ   (©Renáta Sedmáková - stock.adobe.com)

ከእኛ በላይ ፈልገው

ቅዱስ አውጉስጢኖስ ከእግዚአብሔር ርቆ የአረመኔነት መንገድ ይከተል በነበረበት ጊዜ በልቡ በመጨነቅ ዕረፍት እና እንቅልፍ በማጣት ይሰቃይ ነበር። በዚህም ተጨንቆ ከፍጥረቶች ውስጣዊ ቁስሉን የሚፈውስለትን መድኃኒት ለሕሊናው ዕረፍት፣ ሰላምና እርጋታ የሚሰጥለትን ይፈልግ ነበር። ግን እነዚህ ከስቃዩ ሊያሳርፉት ምኞቱን ሊያረኩለት አልቻሉም «በምድርና በእርስዋ ላይ የሚገኙ ፍጥረቶችን እናንተ ናችሁን የልብ ዕረፍት የምትሰጡኝ; ብሎ ሲጠይቃቸው «እኛ አይደለንም ከእኛ በላይ የሆነ ፈልግ´ ብለው መለሱለት።

«ባሕሮችን፣ ገደላ ገደሎችን፣ እንስሳትን ጠይቄ እኛ አይደለንም ከእኛ በላይ ፈልግ ሲሉ መለሱልኝ፡፡ ሰማይና ምድርን ፀሐይን ጨረቃን እና ክዋክብትን ጠይቄ የለም ከእኛ በላይ ፈልግ እንጂ እኛስ አይደለንም ሲሉ ተመሳሳይ መልስ ሰጡኝ´ ከእነርሱም አልፎ ወደ ላይ ከፍ አለ የፈለገውንም የሰላም አምላክ አገኘ ልቡም አረፈ።

ሰው ፈጣሪውን ካላገኘ ልቡ አያርፍም፤ በተለይም በጭንቀቱ ጊዜ ወደ አምላኩ ሲቀርብ የሚፈልገውን ዕርዳታ ያገኛል፡፡ ወደ ፍጥረቶች ቢጠጋ ግን በጉጉት ይቀራል፡፡ ይህንን እያወቀ ስንት ጊዜ ወደ ፍጡራን ብቻ ይመለከታል ወደ ሰማይ ከሰማብ ይልቅ ወደ ምድር ያሰባል። እምነቱን በፍጥረቶች ላይ ይጥላል የሞኝነቱን ፍጻሜ እነዚያ ይመልሱለታል። ሀብታም ደስታውን በሀብቱ ላይ ያደርጋል ግን እርሱም «አንተን የማስደሰት እኔ አይደለሁም ከእኔ በላይ ፈልግ´ ይለዋል። አዋቂው ደስታውን በእውቀቱ ላይ ያኖረዋል በእርሱ ሁሉ የሚያስፈልግህ ፈጣሪ እንጂ እኔ አይደለሁም። ስለዚህ ወደ ላይ ፈልግ የሚል ሹክሹክታ ይሰማናል። ኃይልኛ በትልቅነቱ ክብር ደስታና ብፅዕና ሊያገኝ ያስባል፡፡ ግን አይደለም ከእኛ ላይ አምላክ ያዘዘውን ፈልግ እንጂ እና አይደለንም የሚል ቃል ይሰማዋል፡፡

ፍጥረታት ሁሉ «የምትፈልገውን ዕረፍትና የደስታ ፍጻሜ ከእኛ አታገኝም እኛ እንዳንተው ፍጥረቶች ነን ከእኛ ከፍ ብለህ ወደ ላይ ውጣ ፈጣሪን ራሱን አግኝ፤ ምኞትህ ይፈጸምልሃል፣ ሙሉ ደስታ ታገኛለህ እያሉ ይመክሩናል´ «አልዕሉ አልባቢክሙ፣ ልባችሁን ከፍ አድርጉ ብነኀበ አግዚአብሔር አምላክነ ልባችንም በእግዚአብሔር አምላካች ዘንድ ነው´፡፡ እንግዲህ ከምድር ከፍ እንበል፤ አሸቅበን ወደ መንግሥተ ሰማያት እንመልከት ፍጥረቶችን ትተን ፈጣሪን ብንማጸን ልባችን በአምላካችን ያርፋል፡፡ ፈጣሪን ብንፈልግ የማያስፈልገንን ሁሉ እናገኛለን ለሕይወታችን ቁስል ሁሉ ፈውስ መድኃኒት የሚሆነንን እናገኛለን፤ ውስጣችንም ተደስቶ ያርፋል፡፡

30 June 2022, 13:34