ፈልግ

የመቁጠሪያ ጸሎት የመቁጠሪያ ጸሎት  (©robyelo357 - stock.adobe.com)

የመቁጠሪያ ጸሎት

በ1208 ዓ.ም. በአንዲት የፈረንሳይ አገር ከተማ ብርቱ መናፍቅነት ተነሳ። የቤተክርስቲያን ጠላቶች በጭካኔ ተነሳስተው ስትህተተኛ ትመህርታቸውን እየሰበኩ ገዳማትንና አብያተ ክርስቲያናትን አቃጠሉ፣ ካህናትን ገደሉ፣ መስቀሎችን ሰበሩ፣ መንፈሳዊ ቦታዎተንና መንበረ ታቦትን አረከሱ፡፡ ሕዝበ ክርስቲያን በዚህ አጸያፊ ድርጊት ተንቀጥቅጦ ወደ እግዚአብሔር ብርቱ ምህላ አደረገ፡፡ ዶመኒኮስ የሚባል አንድ ቅዱስ እነዚያን የሃይማኖት ጠላቶች በስብከቱና በጸሎቱ ለመቋቋም ተነሳ፡፡ ነገር ግን ፍሬ አላገኘም፡፡ በዚህ ምክንያት አዝኖ ሳለ እመቤታችን ድንግል ማርያም በእጅዋ መቁጠሪያ ይዞ ታየችው፡፡ በዚያን ጊዜ እነዚያ መናፍቃን የሚሸንፉበት የጦር መሣሪያ “የመቁጠሪያ ጸሎት”  መሆኑን ገለጠችለት፡፡ ቅዱስ ዶመኒኮስም ምክርዋን ተቀብሎ ብዙ የመቁጠሪያ ጸሎት ደገመ፤ ሌሎችንም እንዲጸለዩ አስተማረ፡፡ በዚህ ከፍተኛ የመቁጸሪያ ጸሎት አስደናቂ የሆነ ተአምር በመታየቱ መናፍቃን ተሸንፈው ድል ተመቱ፡፡ በሺህ የሚቆጠሩ መናፍቃን ወደ ቅድስት ቤተክርስቲያን ተመለሱ፤ በሕዝበ ክርስቲያኑም መካከል ሰላም ሰፈነ፡፡

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

እመቤታችን ድንግል ማርያም የመቁጠሪያ ጸሎት እንድናደርግ በመማጸን የመቁጠሪያ ጸሎት ትልቅ መሆኑን ለእኛም ከፍ ያለ ጸጋ የሚያስገኝ እግዜአብሔርንም የሚስደስትና ክብር የሚሰጠው ጸሎት መሆኑን አስረድታናለች፡፡ ስለዚህ ዘወትር እንድንደግመው ትመክረናለች፡፡

መቁጠሪያ የሕዝበ ክርስቲያን ትልቅ ጸሎት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህን የገለጠችው በገዛ ራሷ ታላቋ ቅድስት ድንግል ማርያም ናትና፡፡ እርሷ ከሥነ ፍጥረት ሁሉ በላይ ናት፡፡ እርሷ ራሷ የገለጠችልን ነው እንጂ ሌላ ሰው ወይ አንድ መልአክ፣ አንድ ቅዱስ የገለጠልን ጸሎት አይደለም፡፡ መቁጠሪያ ክቡር ጸሎት ነው፤ ምክንያቱም ይህ ጸሎት ከፍ ያለ የቤተክርስቲያን ጸጋ ያለበት ከመሆኑም በላይ ራሷ የአምላክ እናት የገለጠችልን ነው፡፡

“ጸሎተ ሃይማኖት” ቤተክርስቲያን ያስተማረችን ሲሆን “ጸጋ የሞላሽ ማርያም” … ግን ቅዱስ መልአከ ገብርኤልና ቅድስት ኤልሳቤጥ እንዲሁም ሊቅውንት ያስተማሩን ነው፡፡ “ስብሐት ለአብ … “ሰላም ለኪ …”፣ “ሊጣንያ”  … ፣ ቅድስት ቤተክርስቲያን ያስተማረችን ጸሎቶች ናቸው፡፡ በቅዱስ ገብርኤል ሰላምታ እመቤታችን ድንግል ማርያምን የምናከብርበትና የምንለምንበት ጸሎት ሲሆን “በሰማይ የምትኖር አባታችን …”  በሚለው ጸሎት ደግሞ እግዚአሔርን እናመሰግንበታን እንለምንበታለን፡፡

የመቁጠሪያ ጸሎት ቁም ነገር ብዙ በመሆኑ ታላቅም ነው፡፡ የካቶሊካዊት ቤተክርስቱያን የበላይ አባት የነበሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ኡርባኖስ 4ኛ “በመቁጠሪያ ጸሎት አማካይነት በሕዝበ ክርስቲያን ላይ የቡራኬ ዝናም ይወርዳል”  ብለዋል፡፡ እንዲሁም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን 13ኛ በበኩላቸው “በዚያች የሰማይ ንግሥት የመቁጠሪያ ጸሎት አማካይነት ከፍ ያለ መንፈሳዊ ኃይል እንደሚገኝ ማመን አለብን”  ብለዋል፡፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 5ኛም “የመቁጠሪያ ጸሎት በዓለም ላይ መስፋፋት በጀመረበት ጊዜ ክርስቲያኖች በእርሱና በምስጢራት ጸሎትም በመጠቀም ኑሮአቸውን ለውጠው የመናፍቃን ጨለማ ገፎላቸው የሃይማኖት ብርሃንም ፈነጠቀላቸው”  ብለዋል፡፡ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሲክስቶስ 4ኛ የተባሉ ደግሞ “እግዚአብሔርን እመቤታችን ድንግል ማርያምን የሚያስከብር መቁጠሪያ ነው፤ ከዓለም መዓት፣ ቅጣትና መቅሰፍትንም የሚያስወግድ ነው”  ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ስለ መቁጠሪያ ጸሎት ፍሬና ጥቅም ብዙ መናገር ይቻላል፡፡ የመቁጠሪያ ጸሎት ከእግዚአብሔር ጸጋንና ምሕረትን ያወርዳል የደኀንነት መሰላልም በመሆኑ በችግራችን ጊዜ ይረዳናል ብርታትንም ይሰጠናል፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ጥቅሞች ስላሉት እመቤታችን ድንግል ማርይም እንዚህን መንፈሳዊያን ጥቅሞች እንድናገኝና እንድንጠቀምባቸው አደራ ትለናለች፡፡ እንደ ኤውሮጳ አቆጣጠረ በ1916 ዓ.ም. የፋጡማ እመቤታችን ድንግል ማርያም ለሶስቱ ልጆች ስትታያቸው “ጦርነት አብቅቶአል፡፡ በዓለም ሰላም እንዲነግሥ በየቀኑ የመቁጠሪያ ጸሎት ድገሙ”  እያለች ተማጥናለች፡፡ በመቀጠልም “መቁጠሪያ በመድገም የአምላክ ድጋፍና ዕርዳታ ከሰማይ ወደ ምድር ይወርዳል”  አለቻቸው፡፡

የሮም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮን 13ኛ ስለ መቁጠሪያ ጸሎት ጥቅም ከተናገሩ በኋላ “እኛ ይህ መንፈሳዊ ጸሎት ዘወትር እየተስፋፋ እንዲሄድ ሕዝበ ክርስቲያንም ሁሉ በየቀኑ በሁሉም ስፍራ የሚደግመው ጸሎት እንዲሆን ፈቃዳችን ነው”  እያሉ በጥብቅ አደራ ብለዋል፡፡ ስለዚህ የእመቤታችን የድንግል ማርያምንና የቤተክርስቲያንን አደራ በጥልቅ ስሜት ተቀብለን በተግባር እንድናውለውና የመቁጠሪያ ጸሎት ወዳጆች እንድንሆነ ቁርጥ ፈቃድ እናድርግ፡፡ የመቁጠሪያ ጸሎት ሳንደግም አንዲት ቀንም እንኳ እንዳናሳልፍ እንወስን፡፡

27 May 2022, 14:08