ፈልግ

ብጹዕ አቡነ ኤድዋርድ ኩሳላ በሀገረ ስብከታቸው ጉብኝት ሲያደርጉ ብጹዕ አቡነ ኤድዋርድ ኩሳላ በሀገረ ስብከታቸው ጉብኝት ሲያደርጉ 

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የደቡብ ሱዳን ጉብኝት የሰላም ተስፋ መሆኑን ተነገረ

ከመጭው ሰኔ 28 - 30\2014 ዓ. ም. ድረስ በደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን የሚያደርጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በአገሪቱ ለዓመታት የዘለቀው የእርስ በእርስ ግጭት አብቅቶ ሰላም እና እርቅ የሚወርድበትን ተስፋ እንደሚያስገኙ፣ በደቡብ ሱዳን የቶምቡራ-ያምቢዮ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤድዋርድ ሂቦሮ ኩሳላ ተናግረዋል። ብጹዕ አቡነ ኤድዋርድ፣ በአገሪቱ በሚገኙ ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ጸሎት እንዲደረግ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ መጠየቁን ገልጸው፣ በጁባ ከተማ ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚቀርብበት ሥፍራ ግንባታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሰኔ 28 – 30/2014 ዓ. ም. ድረስ በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ከዚህ በፊት በደቡብ ሱዳን ያልታየ ታሪካዊ ጉብኝት እንደሚሆን ብጹዕ አቡነ ኤድዋርድ ገልጸው፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲያደርጉ የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጉብኝት የመጀመሪያው መሆኑን ገልጸዋል። ምዕመናን በየሀገረ ስብከቶቻቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ብጹዕ አቡነ ኤድዋርድ ገልጸው፣ በአገሪቱ በሚገኙ ሁሉም ቁምስናዎች በየዕለቱ ጸሎት እንዲደረግ የአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጥሪ ማድረጉን ገልጸዋል።

የእንግዳ አቀባበል ዝግጅት ተጀምሯል

በዋና ከተማ ጁባ ውስጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚያልፉባቸው አውራ ጎዳናዎች እና የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚቀርብበት መንበረ ታቦት እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል። በአገራቸው ውስጥ ለክርስቲያኖች አንድነት የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ እንደሆነ የተናገሩት ብጹዕ አቡነ ኤድዋርድ፣ ከደቡብ ሱዳን ሕዝብ መካከል ዘጠና ከመቶ በላይ የክርስትና እምነት ተከታይ መሆኑን አስታውቀው፣ በክርስቲያኖች መካከል አንድነትን የሚያሳድግ የጋራ ውይይት ሊበረታታ እንደሚገባ ገልጸዋል። ይህም ሰላምን መልሶ ለመገንባት በጋራ መሥራት እንደሚገባ ያስረዳል ብለዋል። በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች አንጻራዊ ሰላም መኖሩን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ኤድዋርድ፣ አማፂያን ባሉባቸው ቦታዎች አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ጥቃቶች ቢኖሩም የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ዜና ሰላምን  እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ሁከትን የለመዱት ሳይቀር ሁሉንም እንዳስደነቀ ብጹዕ አቡነ ኤድዋርድ ገልጸው፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የሰላም መልዕክት የሚያዳምጡት በሙሉ ልባቸውን ከፍተው ለሰላም እንደሚቆሙ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፣ ይህም ለደቡብ ሱዳን ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ እና ለዓለም ምሳሌ ይሆናል ብለዋል።

18 May 2022, 16:47