ፈልግ

በኮንጎ ውስጥ ቤን ግዛት ጥቃት የደረሰበት ቤተ ክርስቲያን በኮንጎ ውስጥ ቤን ግዛት ጥቃት የደረሰበት ቤተ ክርስቲያን   (AFP or licensors)

"ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በኮንጎ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለአገሪቱ መባረክ ነው!"

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሐምሌ 25-28/2014 ዓ. ም. ድረስ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለአገሪቱ መባረክ ይሆናል ሲሉ፣ የኪኪዊት ሀገረ ስብከት ጳጳስ፣ ብጹዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ቦዲካ፣ በመከራ እና ስደት ውስጥ ለምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ለሚያደርግ አንድ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ገልጸው፣ በእርስ በእርስ አመጽ የቆሰለው መላው የገሪቱ ሕዝብ ከቅዱስነታቸው የእርቅ መልዕክት በመጠበቅ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ሲነገረን የተሰማን ደስታ ወሰን የለውም” ያሉት፣ ብጹዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ እንደ ሐዋርያዊ እረኛነት ወደ ኮንጎ የሚመጡት በእምነት ሊያበረታቱን በመሆኑ መባረክ እንደሚሰማቸው፣ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ፣ የኪኪዊት ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ቦዲካ፣ ሮም ከሚገኝ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

የምእመናኑ መጠበቅ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ አገሪቱን ከጎበኟት ከ 37 ዓመታት በኋላ ሲሆን፣ የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት በአገሪቱ ለሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን ታላቅ የደስታ ጊዜ መሆኑ ተነግሯል። ለቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ቦዲካ፣ ታጣቂ ወገኖች በሕዝቡ ላይ በሚያደርሱት ስቃይ እና መፈናቀል ምክንያት አገሪቱ በውጥረት ውስጥ እንደምትገኝ ገልጸው፣ ከእያንዳንዱ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በኋላ ዜማዎችን በመለማመድ፣ ለቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ጉብኝት እራሳችንን በተሻለ ሁኔታ በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

“የኮንጎ ሕዝብ ታረቅ!”

በቆዳ ስፋቱ ግዙፍ እና በጣም ሀብታም የሆነችው ዲሞክራሲያዊት ሮፐብሊክ ኮንጎ፣ በሕዝቦቿ መካከል ሰፊ  ስቃይ እንዳለበት ይታወቃል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኮንጎ ውስጥ ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉት አገሪቱ በጣም በተጨነቀችበት ጊዜ እንደሆነ የገለጹት የኪኪዊት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጢሞቴዎስ አክለውም፣ አገሪቱ በተፈጥሮ ሃብት የተባረከች ብትሆንም ፣ ራስ ወዳድነትን እና ሽብርን የሚያራምዱ በርካታ የታጠቁ ኃይሎች መኖራቸውን አስረድተዋል።

ለምእመናን ዋጋን መስጠት

ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር በሚያደርጉት ውይይት አንዳንድ የኮንጎ ቤተ ክርስቲያን ባሕሪያትን ለማሳወቅ ዕድል እንደሚያገኙ የገለጹት ብጹዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ አስተምህሮን ተከትሎ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የምእመናንን ተሳትፎ ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን አስረድተው፣ በኮንጎ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የምዕመናን ሐዋርያዊ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ በመሆናቸው፣ ወጣቶችን ጨምሮ የመላውን ምዕመናን ሕይወት ወደ ቅዱስነታቸው ፊት እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል። 

19 May 2022, 18:14