ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ በፖምፔይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ በፖምፔይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ 

ብጹዕ ካርዲናል ግሬሽ፣ ሰዎች ሰላምን እንዲያደርጉ እና እንዲጠብቁት ጠየቁ

የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ፣ ሚያዝያ 30/2014 ዓ. ም. በደቡብ ጣሊያን ውስጥ በሚገኝ የፖምፔይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ተገኝተው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎትን መርተዋል። የጎርጎሮሳውያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉት ምዕመናን ዘንድ የግንቦት ወር መጀመሪያ እሑድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለብጹዕ ባርቶሎ ሎንጎ በሰጠችው ተስፋ መሠረት፣ በመላው ዓለም የሚገኙ ምእመናን በየዓመቱ የመቁጠሪያ ጸሎትን የሚጀምሩበት ቀን መሆኑ ይታወቃል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት፣ "እግዚአብሔር የሰው ልጆችን ከሚያጋጥማቸው ክፉ ነገሮች ሁሉ መታደጉን ዛሬም ቀጥሏል” ብለው፣ የዩክሬንን ሕዝብ ጨምሮ በዓለማችን ውስጥ በተለያዩ ስቃዮች ውስጥ የሚገኙትን ሕዝቦች በሙሉ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፊት እናቀርባለን ብለዋል። አክለውም፣ እኛም እግዚአብሔርን በመምሰል፣ ሰላምን መገንባት እና መከላከል እንድንችል የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት እንጠይቃለን ብለዋል።

ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ለሰው ልጆች ሰላምን ትመኛለች

በአውሮፓ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ደም አፋሳሽ የሆኑ የጦርነት፣ የአመጽ እና የጥላቻ ሀዘን እና ጭንቀት ወደ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልብ ፊት እናቅርብ በማለት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬሽ በስብከታቸው አሳስበዋል። እመቤታችን ማርያም የሲኖዳሳዊነት ምሳሌ እንደሆነች የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ግሬሽ፣ በሲኖዶስዊት ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ሁለት ነገሮች እንዳሉ እነርሱም ጸሎት እና ልግስና መሆናቸውን አስረድተዋል። በመሆኑም ብጹዕነታቸው በፖምፔይ እመቤታችን ቤተ መቅደስ ውስጥ ከበርካታ ምዕመናን ጋር ሆነው ባቀረቡት ጸሎት፣ ከሁለት ወራት በፊት በሩሲያ በተወረረች የምስራቅ አውሮፓ አገር ዩክሬን እና በአሰቃቂ ጦርነት ውስጥ ለሚገኙት ሕዝቦች በሙሉ ሰላም እንዲወርድ የእመቤታችንን አማላጅነት ለምነዋል።

ወደ እመቤታችን የሚቀርብ ጸሎት ዝግጅት

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለብጹዕ ባርቶሎ ሎንጎ በሰጠችው ተስፋ መሠረት፣ እ. አ. አ በየዓመቱ ሚያዝያ እና ጥቅምት ወር መጀመሪያ እሁድ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የሚቀርብ ጸሎት ምዕመናን በኅብረት ማቅረባቸው ታውቋል። ከሚያዝያ 21 እስከ ሚያዝያ 28/2014 ዓ. ም. በነበሩት ቀናት ውስጥ ምዕመናን በኅብረት ጸሎታቸውን አቅርበው፣ በደቡብ ጣሊያን ፖምፔይ ከተማ የሚገኝ የመቁጠሪያ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ የታንጸበት 83ኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓልንም ያከበሩ ሲሆን በበዓሉ ላይ በርካታ ምዕመናን ተካፋይ ሆነዋል።

እ. አ. አ. በ2020 ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ምዕመናን አልነበሩም

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጣሊያን ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በተስፋፋበት እ. አ. አ. በ2020 ዓ. ም. በፖምፔይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ የሚቀርብ የመቁጠሪያ ጸሎት በ137 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለ ምዕመናን ተሳትፎ የተካሄደ ሲሆን፣ ከዚያን ጊዜ በፊት ከመላው ጣሊያን እና ከዓለም ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን በቤተመቅደሱ በሚካሄድ የመቁጠሪያ ጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ይገኙ እንደነበር ታውቋል። ይሁን እንጂ በወረርሽኙ ምክንያት የብጹዕ በርቶሎ ሎንጎ ሥራ መቀጠል እንዳለበት በማሳሰብ የጸሎት ሥነ ሥርዓቱን ብፁዕ ካርዲናል ክሬሼንዚዮ ሴፔ ሳያቁርጡ ሲመሩት መቆየታቸው ታውቋል። ብፁዕ ካርዲናል ሴፔ፣ በፖምፔይ የሚገኝ የእመቤታችንን ቤተ መቅደስን በማስታወስ ለምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፣ ወደ እመቤታችን ማርያም ፊት በኅብረት ለጸሎት መቅረባችን የአንድ ቤተሰብ አባላት ያደርገናል ብለው፣ የእመቤታችን ማርያም ቤተ መቅደስ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤት መሆኑን በማስረዳት ምዕመናን በሙሉ በችግር እና በመከራ ወቅት ወደ እመቤታችን ማርያም ዘንድ የመቁጠሪያ ጸሎትን እንዲያቀርቡ አሳስበዋል።

የብጹዕ ባርቶሎ ሎንጎ ቃላት ዛሬም ሕያው ናቸው

የፖምፔይ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ሞንሲኞር ቶማሶ ካፑቶ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት የሚደረግ ልመና ትርጉም በማብራራት፣ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱ ጭንቀቶችን በሚያስታውሱ የብጹዕ ባርቶሎ ሎንጎ ጸሎትን በማስታወስ አስተያየታቸውን አካፍለዋል። በመከራ ወቅት በነፍስ እና በሥጋ ላይ የሚደርስ አደጋ መኖሩን በመግለጽ፣ የሰው ልጅ በታሪክ ውስጥ ከመከራ እና ጭንቀት ነፃ የሆነበት ጊዜ የለም ብለው፣ “እምነታችን፣ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘንድ የሚቀርብ ጸሎት እና በዚህም እምነትን ማግኘት፣ ከወረርሽኙም ሆነ ከማንኛውም ችግር እግዚአብሔር ሕይወታችንን እንዲጠብቅ የምናቀርበው ጸሎት ፍሬ አለው” ብለዋል።

ብጹዕ ባርቶሎ ሎንጎን መምሰል ያስፈልጋል

በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮችን የሚከታተል ጳጳስዊ ምክር ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ፣ የወረርሽኙ መከላከያ ደንቦችን ተከትሎ የቀረበውን የአምና የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በፖምፔይ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ቤተ መቅደስ ተገኝተው በመሩበት ጊዜ ባቀረቡት ስብከት፥ በወረርሽኙ ምክንያት የተፈጠረውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መቋቋም እንዲቻል ብጹዕ ባርቶሎ ሎንጎ የጀመረውን ተመሳሳይ የበጎ አድራጎት ተግባራትን መጀመር እንደሚያስፈልግ ምዕመናንን አበራተው፣ ለባልንጀራ የምናደርገው በጎ ተግባር፣ እምነታችን እንደሚያስረዳን፣ “ለተቸገሩት እፎይታን የሚሰጥ የምሕረት ሥራ መሆኑን በማስረዳት፣ በችግር ውስጥ እግዚአብሔር እንደሚያጽናናን መርሳት እንደሌለብን እና እምነትንም ማዳበር እንደሚያስፈልግ አደራ ብለዋል። በእምነት በመኖር የእግዚአብሔርን ዕቅድ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ታሪኮችንም በመረዳት ሁልጊዜ የግል መልስን መፈለግ እንዳለብን አሳስበው፣ የፖምፔይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ መስራች የሆነው ብጹዕ ባርቶሎ ሎንጎ፣ ብዙ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እንዲጀምር የገፋፋው ይህ መሆኑን በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች የሚከታተል ጳጳስዊ ምክር ቤት አስተባባሪ፣ ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ አስረድተዋል።  

10 May 2022, 16:40