ፈልግ

እህት ፓትሪሲያ፥ ዓለማችን ደፋር መሪዎች በተለይም ሴቶች እንደሚያስፈልገው ገለጹ

በስዊዘርላንድ ዳቮስ ከተማ ግንቦት 15/2014 ዓ. ም. በተካሄደው ዓለም አቀፍ የኤኮኖሚ ፎረም ላይ የምጣኔ ሃብት ጠበብትን እና የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎችን ያሳተፈ ውይይት ተካሄዷል። ውይይቱን ዓለም አቀፍ የገዳማውያት ጠቅላይ አለቆች ኅብረት ዋና ጸሐፊ እህት ፓትሪሲያ ማሬይ የተካፈሉት ሲሆን፣ ለውይይቱ ተሳታፊዎች ባሰሙት ንግግር፣ ዓለማችን ደፋር መሪዎች፣ በተለይም ሴቶች እንደሚያስፈልገው የገለጹ ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ በርካታ የእምነት እና የወዳጅነት ልምዶች እና ምስክርነቶች ቀርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የገዳማዊያት ሕይወት እና አገልግሎት የሚገኘው በዝቅተኛው የማኅብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ እንደሆነ እህት ፓትሪሲያ አስረድተው፣ ስለ ወቅታዊ የዓለማችን ችግሮች ውይይቱን ለተካፈሉ በርካታ እንግዶች፣ እንደ “ጎግል” ወይም “ዩኒሊቨር” ካሉ ትልልቅ ኩባንያ ተወካዮች ጋር ተነጋግረዋል። ገዳማውያት ከኅብረተሰቡ ታላልቅ ፈተናዎች ጋር በተጨባጭ መንገድ እንደሚጋፈጡ የገለጹት እህት ፓትሪሲያ፣ ይህም እንደ ጤና፣ ትምህርት፣ ለስደተኞች የሚደረግ ድጋፍ እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች የሚደረግ ዕእርዳታን እንደሚያጠቃልል አስረድተዋል። አክለውም፣ በሀገር ውስጥ፣ በአገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲደረግ እንደሚመኙ ገልጸው፣ አስፈላጊው ለውጡ የሚመጣ በኅብረተሰቡ መካከል ከተረሱ፣ ችላ ከተባሉት እና በእውቀት ዝቅተኛ ከሆኑት ሰዎች በኩል መሆን እንዳለበት አረድተዋል።

ትናንሽ ምልክቶች እና ትላልቅ ውጤቶች 

ደፋር መሪዎች ግልጽ ግብ እና ራዕይ አላቸው ያሉት እህት ፓትሪዚያ፣ ገዳማውያት እንደመሆናቸው መጠን እምነታቸው እና መላ ሕይወታቸው ለሌሎች መልካም ለመሆን እንደሆነ ሕንዳዊቷ ገዳማዊት እህት ማርያም ጆን አረጋግጠው፣ ስኬታማ እና ተጨባጭ ምሳሌ መሆን የሚችሉ ፕሮጀክቶች በመነኮሳት የተጀመሩ እና የ"እህት ፕሮጀክት" አካል መሆናቸውን ገልጸው፣ ትንንሽ ጥረቶች ቢሆኑም ትላልቅ ውጤቶች ማስገኘታቸውን አስረድተዋል። ባሁኑ ወቅት ቅድሚያን የሰጡት በዩክሬን ስለሚገኙ ሴቶች ሁኔታ እንደሆነ እህት ማርያም ጆን ከገለጹ በኋላ፣ የወንጌል ራዕያቸው እያንዳንዱ ሰው የተሟላ እና የተከበረ ህይወት እንዲኖር ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሆነ፣ “የእህት ፕሮጀክት” ሦስተኛው ተሳታፊ እህት ሩት ፒላር ዴል ሞራ፣ በዳቮስ በተዘጋጀው ውይይት ላይ ተናግረው፣ የሚሰጡት አገልግሎት ማንንም እንደማያገልል አስምረው፣ አመጽ እና ጦርንርት እንኳ ቢነሳ የሚያገለግሉትን ማኅበረሰብ ጥለው የማይሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።

"የቅርብነት" ምስክሮች

አንዳንድ ተጨባጭ ምሳሌዎችን የጠቀሱት እህት ፓትሪሲያ፣ እህት አን ሮዝ ኑ ታውን በምያንማር ውስጥ በወታደሮች ፊት ተንበርክካ ስትለምን በፎቶ ምስልመታየቷን፣ በሲሪላንካ የሚኖሩ እህቶች በመብራት፣ በነዳጅ እና በመድኃኒት አገልግሎት መቋረጥ የተነሳ ተቃውሟቸውን የሚገልጹ ሰዎችን ከሚደርስባቸው አደጋ መከላከላቸው፣ ኮሎምቢያዊቷ መነኩሲት ግሎሪያ ሲሲሊያ ናቫሬዝ በቻድ ከአምስት ዓመት እስራት በኋላ መፈታቷን አስታውሰዋል። ነገር ግን እነዚህ የደፋር መሪዎች አስገራሚ ምሳሌዎች ብዙውን ጊዜ ተደብቀው እንደሚኖሩ አስረድተዋል። ዓለም አቀፍ የገዳማውያት ጠቅላይ አለቆች ኅብረት ዋና ጸሐፊ እህት ፓትሪሲያ መሬይ ለውይይቱ ተካፋዮች የደረጉትን ንግግር ሲደመድሙ፥ ደፋር አመራር- ትህትናን፣ አዳዲስ ክስተቶችን ለመጋፈጥ ዝግጁ መሆንን፣ ውድቀትን ተቀብሎ እንደገና መጀመርን እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።

25 May 2022, 20:29