ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ (ከበሰተ ግራ ሦስተኛ) በጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉ፣ ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ (ከበሰተ ግራ ሦስተኛ) በጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ሲያደርጉ፣  (ANSA)

ካርዲናል ባሴቲ፥ “ምዕመናን ቤተ ክርስቲያንን በኃላፊነት እንዲያገለግሉ ዕድል መስጠት ያስፈልጋል!”

የአገልግሎት ጊዜአቸውን የፈጸሙት የጣሊያን ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ፣ ከግንቦት 15-19/2014 ዓ. ም. በመካሄድ ላይ በሚገኝ የጳጳሳቱ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። በአገልግሎት ዓመታት ውስጥ ለተባበሯቸው በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። “ጨካኝ እና ኢ-ፍትሃዊ” በተባለው የዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተሰደዱትን በመርዳት ላይ ለሚገኙትም ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ጳጳሳቱ ቅድሚያን መስጠት ከሚኖርባቸው አገልግሎቶች መካከል፥ ለወጣቶች የሚቀርብ ሐዋርያዊ አገልግሎት እና በልጆች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን መከላከል እንደሆነ ተናግረዋል። እየተካሄደ ያለው ሲኖዶሳዊ ጉዞ ላስከተለው የአስተሳሰብ ለውጥ ምስጋናቸውን አቅርበው፣ ምዕመናን በንቁ ተሳትፎ ተጨባጭ ምርጫዎችን እንዲያደርጉ በማገዝ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አዲስ የሰላም ወቅት መጀመር

ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ ላለፉት ዓመታት የጉባኤው ፕሬዚደንት ሆነው እንዲያገለግሉ ለተጣለባቸው እምነት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስን አመስግነው፣ በዘለዓለማዊ ዕረፍት ላይ የሚገኙ ጳጳሳትን አስታውሰዋል። ቀጥለውም የዩክሬን ሕዝብ እና የስደተኞችን ስቃይ ለማቃለል ጥረት እያደረገ የሚገኘውን የጣሊያን ካቶሊካዊ በጎ አድራጊ ድርጅት አስታውሰው፣ ጦርነቱ አብቅቶ አዲስ የእርቅ፣ የፍትህ እና የሰላም ወቅት እንዲመጣ በማለት ጥሪያቸውን በድጋሚ አቅርበዋል። በደቡብ ጣሊያን፣ ባሪ ከተማ እ. አ. አ 2020 እና በሰሜን ጣሊያን ፍሎሬንስ በ2022 ዓ. ም. በተካሄደው ስብሰባ ከሜዲቴራኒያን ባሕር ጋር በሚዋሰኑ አገራት መካከል የተፈረመውን “የሜዲትራኒያን የሰላም ድንበር” ሰነድ ጥቅሰው፣ አገራቱ ስደትን በኅብረት ለመዋጋት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን አስታውሰዋል።  

ከኢየሱስ ጋር ያለ የማያቋርጥ ግንኙነት ማድረግ

መጪውን የኢየሱስን የዕርገት በዓል ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ከእነርሱ እየራቀ ሲሄድ ወደ ሰማይ እንደሚመለከቱ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አስታውሰው፣ በእውነተኛ የአብሮነት መንፈስ የሚደረግ የጳጳሳት ጉዞ እይታውን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያደረገ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል። አክለውም ጳጳሳቱ እውነተኛ ሐዋርያዊ አባቶች እና ምስክርነትን የሚሰጡ መሪዎች መሆን ከቻሉ ደስታ ሊሰማቸው ይገባል ብለዋል።

ወጣቶችን ማስተማር የሐዋርያዊ አባቶች ቀዳሚ ተግባር ነው

“የአዲሱ ትውልድ ዕጣ ፈንታ ሁልጊዜ ያሳስበኛል” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ የክርስትና ትምህርት አድጎ ለእውነተኛ ነፃነት በር ከፋች እንዲሆን ያስፈልጋል ብለዋል። “ሕይወትን በከንቱ ሳያባክኑ ለሌሎች አገልግሎት ማዋል ያስፈልጋል” ያሉትን የአባ ቶኒኖ ቤሎ አደራን ጠቅሰው፣ ዘንድሮ በተከበረው የፋሲካ በዓል ማግስት በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳጊ ወጣቶች በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የገለጹትን የጋለ ፍቅራዊ ስሜትን አስታውሰዋል። በዕድሜ አነስተኛ ለሆኑት እና ለጥቃት ለተጋለጡ አዳጊ ወጣቶች ደህንነቱ የተጠበቀ እና ተስማሚ አካባቢን መፈለግ እና ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ፣ ከዚህ ቀደም በሌሎች አጋጣሚዎች እንደተገለጸው ከሚደርስባቸው ጥቃት ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎችን ገምግሞ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ እና ግንዛቤን ለማስጨበጥ እቅድ መኖሩን አስታውቀዋል።

አስተሳሰብን መቀየር

በቅርቡ የሚከበረውን የጴንጤቆስጤ በዓል ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከናወነውን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ አስታውሰው፣ በእርሱ መመራት እና  እሱን ማዳመጥ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። በሲኖዶሳዊ ሂደት ላይ የምትገኝ የጣሊያን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ ​​መልካም እና ፍሬያማ የሆኑ የአሠራር ስልቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ላይ እንደሚትገኝ ገልጸው፣ አደራ የተጣለባቸው የቤተ ክርስቲያን አባቶች በእያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን ሂደት መጀመሪያ ደረጃ ላይ ሳይሆኑ ነገር ግን በጎ ፈቃድ ያላቸውን ብዙ ሌሎች ሰዎች በሚያሳትፍ መንገድ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል። “‘ሁሉም በጳጳስ እጅ’ የሚለውን የጋራ አስተሳሰብ እየቀየርን እንገኛለን” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ እያንዳንዱ ክርስቲያን በተጠራበት መንገድ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ በንቃት እና በኃላፊነት እንዲሳተፍ ዕድል መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ አክለውም፣ በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ሰነድ ውስጥ የተጠቀሰው እና ምእመናን በቤተ ክርስቲያ ተልዕኮ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኩል ጠንካራ ድጋፍን ያለው እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ መሆኑን አስረድተዋል

ቤተ ክርስቲያን የኅብረተሰቡ ርዕዮተ ዓለም ምንጭ ልትሆን ትችላለች

ምዕመኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊቀበለው የሚገባው ተግዳሮት እንዳለ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ባሴቲ፣ በፖለቲካዊ በጎ አድራጎት ላይ የሚደርስ አደጋ፣ ከባድ ምርጫዎች የሚያስከትሉ መሰናክሎች፣ ከሁሉ ዘንድ ያልቀረበ የውሳኔ አሰጣጥ ደካማነት፣ ቅራኔዎች እና ዘላቂነት ያላቸው አለመረጋጋቶ እና የእርስ በእርስ ግጭቶች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ክርስቲያን ፖለቲከኛ በግል ጉዳዩ መጠመድ እንደሌለበት እና የወንጌልን መልዕክት ወደ ማኅበራዊ ርዕዮተ ዓለም ከሚያሳንስ ከማንኛውም ዓይነት ጥምረት መራቅ እንዳለበት ተናግረዋል። ከዚህ ሃሳብ በመነሳት ፖለቲካው “ሕዝባዊ” ሆኖ መቀጠል እንዳለበት ተናግረው፣ በመቀጠልም በመንፈስ ቅዱስ የምትመራ ቤተ ክርስቲያን፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የፖለቲካ መሪዎችን መገሰጽ፣ የውይይት ደረጃን ከፍ በማድረግ ከኢኮኖሚያዊ አመክንዮ በመውጣት የእያንዳንዱን ሰው ሰብዓዊ ክብር ለማስጠበቅ የቆመች መሆኗን አስረድተዋል።  

በቤተ ክርስቲያን ስላለው የሴቶች ሚና ትኩረት መስጠት

የአገልግሎት ጊዜያቸውን የፈጸሙት ብጹዕ ካርዲናል ጓልቲዬሮ ባሴቲ፣ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ አስመልክተው ባሰሙት ንግግር፣ በተጨባጭ ምርጫዎች አማካይነት ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸው፣ ከትምህርተ ክርስቶስ መምህርነት እስከ በጎ አድራጎት ተግባር ድረስ ብዙ ሴቶች በተለያዩ አካባቢዎች የሚጫወቱትን ሚና ሕጋዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

25 May 2022, 14:42